ሰላም!
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሚያዚያ ፲፯፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? በፈቃደ እግዚአብሔር የጀመርነው ዐቢይ ጾም (ጾመ ክርስቶስ) ጨርሰን በዓለ ትንሣኤን እያከበርን ነው፤ በዓሉን እንዴት እያከበራችሁ ነው? የትንሣኤ በዓል ነጻነታችንን አግኝተን ትንሣኤ እንዳለን የተበሠረበት በዓላችን ነውና ታላቅ በዓል ነው፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣቱ ትንሣኤያችንን አበሠረን፤ ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለን ዐወቅን፡፡ ታዲያ በጾሙ ወቅት እናደርገው እንደነበረው በጸሎት መበርታትና በመንፈሳዊ አገልግሎት መሳተፍ አለብን፤
በዘመናዊ ትምህርታችን መበርታት እንዳለብንም መዘንጋት አይገባም፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ ትምህርቱ መገባደጃ ወቅት ስለሆነ ከፈተና በፊት በርትተን በማጥናት ዕውቀትን አግኝተን ከክፍል ክፍል በጥሩ ውጤት መሸጋገር ይገባናል፤ መልካም! ለዛሬ ከበዓለ ትንሣኤ ጋር በተያያዘ ስለ ሰላም እንማራለን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! “ሰላም” የሚለውን ኃይለ ቃለ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ላይ እንዲህ በማለት ያብራሩታል ሰላም ማለት ፍጹም ጤና፣ ዕረፍት፣ ዕርቅ ፍቅር፣ አንድት ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፰፻፷፮) አንድ ሰው “ሰላም አለው” ሲባል ጤነኛ እና ለሰዎች ፍቅር ያለው ኅብረትን አንድነትን የሚወድ ማለት ነው፡፡
ልጆች! ሰላም ለሰዎች ሁሉ አስፈላጊና መሠረታዊ ከሆኑ ነገሮችም አንዱ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ለማናወን ቅድሚያ ሰላም መሆን ግድ ይላል፤ በሕይወታችን ደስተኛ ሆነን ለመኖር አእምሮአችንን ከጭንቀት ነጻ ለማድረግ ለሰዎች መልካም ነገርን ለማሰብ እኛም ደግሞ ደስተኛ እና ጤነኛ ለመሆን ሰላማዊ መሆን አለብን፡፡
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ እንዲህ ይመክረናል፤ ‹‹…ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ…፡፡›› (ሮሜ ፲፪፥፲፰) ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር እኛ የሰላም ሰዎች ነገሮችን በትዕግሥት የምናልፍ ለሰዎች መልካም የምናስብ ልንሆን ይገባል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሰላም ከመንፈሳዊ ምግባራት ወይም ደግሞ ፍሬዎች አንዱ ነው፤ ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት …….. ›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ይነግረናል፡፡ (ገላ.፭፥፳፪) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ሲነሣ ቅዱሳን አባቶቻችንን ሐዋርያትን እንዲህ ብሏቸው ነበር፤ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡›› (ዮሐ. ፳፥፲፱)
ተጨንቀው በነበሩበት ሰዓት በመካከላቸው ተገኝቶ መጀመሪያ ያሰማቸው ቃል ሰላም የሚለውን ነበር፤ አስፈላጊና ዋንኛ ነገር በመሆኑ ፤ቀድሞም በዕለተ ዐርብ በሲኦል በመከራ ውስጥ ለነበሩ ነፍሳት ያሰማቸውም ቃል ‹‹ሰላም›› ለእናንተ ይሁን የሚለውን ነበር፡፡ ልጆች! ትምህርት ቤት ገብታችሁ ተምራችሁ ዕውቀት መቅሰም የምትችሉት ሰላም ሲኖር ነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰላም ከማስተማሩም በተጨማሪ እንዲህም በማለት ቅዱሳን ሐዋርያትን ነግሯቸዋል፤ ‹‹..ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላምን እሰጣችኋላሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም…›› (ዮሐ.፲፬፥፳፯) ቅዱሳን ሐዋርያትም ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን አብት አድርገው ምእመናንን ሲመክሩ ‹‹…በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ …›› በማለት ምእመናን ይመክሩ ነበር፡፡ (ሮሜ ፲፪፥፲፰)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሰላም ከየት ይገኛል፤ ሰላምን የሚሰጥ የሰላም ባለቤት እግዚአብሔር ነው፤ ፍጹም የሆነውን ሰላም ለማግኘት በፈቃዱ መኖር፣ ሕጉን ማክበር ያስፈልገናል፡፡ የሰው ልጅ ሰላሙን የሚያጣው፣ ለጭንቀት የሚጋለጠው ከእግዚአብሔር እቅፍ ሲርቅ ትእዛዝ ሲጥስ፣ ሕግን ሲያፈርስ ነው፡፡
ልጆች! ቅዱስ ሉቃስ በጻፈልን የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል ላይ ሁለት ልጆች የነበሩት አንድ ባለጸጋ ሰው ነበር፡፡ ታናሹ ልጅ ከአባቱ መውረስ የሚገባኝን ከሀብትህ ግማሹን ስጠኝ ብሎ ተቀብሎ ወደ ሌላ አገር ሄደ፤ ገንዘቡንም ጨረሰ በጣምም ተቸገረ፤ በዚህም የተነሣ ተጨነቀ፤ ተቸገረ፤ ሰላሙንም አጣ ወደ ልቡም ሲመለስ በሠራው ጥፋት ተጸጽቶ ወደ አባቱ ቤት ሊመለስ ፈለገ ከገባበት ጭንቀት መውጣት እንዳበት አስቦ ወደ አባቱ ቤት ተመለሰ፤ አባቱም ልጁ በመመለሱ ደስ አለው ትልቅ ዝግጅትም አደረገለት፡፡ (ሉቃ. ፲፭፥፲፩-፳፬)
የሰላም እጦት ከሚመጣባቸው መንገዶች አንዱ ከእግዚአብሔር ቤት መራቅ፣ የወላጆችን ምክር ባለመስማት፣ በራሳችን የተሳሳተ መንገድ በመሄድ ሰላማችንን እንድናጣ እንሆናለን፤
ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ሰላምን ላለማጣት ሕጉን ፣ሥርዓቱን ማክበር አለብን፡፡ በትንቢተ ኢሳይያስ ‹‹…እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድበትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር…›› (ኢሳ.፵፰፥፲፯) ሰላምን ለማግኘት ትእዛዙን ልናከብር ይገባናል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የሰላም ሰው እንዲሆኑ በትምህርቷ ሁሌም ሰላምን ትሰብካላች፤ ስለ ሰላም ትጸልያለች፤ የሰላም ጥሪዋን አድምጠን ሰላማዊ ሰዎች እንሁን አጠገባችን ከተጣላነው ሰው ይቅር በመባባል እንጀምር፡፡
ሁሌም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!
የሰላም አምላክ ሰላሙን ፍቅሩን ያድለን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!