ርደተ መንፈስ ቅዱስ

የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በዓል

መምህር ሙላት ደምሌ

ግንቦት፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

በዓለ ጰራቅሊጦስ (የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በዓል)፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዐረገ በዐሥረኛው ቀን፣ ከትንሣኤው ደግሞ በኀምሳኛው ቀን የሚከበር የቤተ ክርስቲያን ታላቅ በዓል ነው። “ጰራቅሊጦስ”  የጥንት ግሪክ ቃል ሲሆን “አጽናኝ፣ መካሪ፣ ጠበቃ” የሚል ፍቺ አለው፤ ይህም መንፈስ ቅዱስን ያመለክታል። ይህ በዓል መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበትን፣ የቤተ ክርስቲያን ልደት የታወጀበትንና የጌታ የተስፋ ቃል የተፈጸመበትን ዕለት የምናስብበት ነው።

መንፈስ ቅዱስና የሐዋርያት ተልእኮ

መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ በወረደ ጊዜ፣ የወንጌልን አገልግሎት በኃይልና በጥበብ እንዲወጡ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ጸጋዎችን አግኝተዋል፦

የድፍረትና የብርታት ጸጋ፦

ቀደም ሲል ጌታ ሲያዝ ፈርተው የተበተኑት ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ ስለ ክርስቶስ ያለ ፍርሃት መሰከሩ። (ማቴ. ፳፮፥፶፮) ጴጥሮስና ዮሐንስ በሸንጎ ፊት ቀርበው በድፍረት ተናገሩ (የሐዋ. ፬፥፲፫)። “ከጸለዩም በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፥ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ፡፡” (የሐዋ. ፬፥፴፩)

የጥበብና የማስተዋል ጸጋ፦

መንፈስ ቅዱስ የብሉይ ኪዳንን ትንቢቶች እንዲረዱና ከክርስቶስ፣ ሞትና ትንሣኤ ጋር እንዲያዛምዱ አእምሯቸውን ከፈተላቸው። የጴጥሮስ የበዓለ ኀምሳ ስብከት የዚህ ግልጽ ማሳያ ነው። (የሐዋ. ፪፥፲፬-፵፩)።

ተአምራትን የማድረግ ኃይል፦

ሐዋርያት በክርስቶስ ስም ድውያንን ፈወሱ፣ ሙታንን አስነሡ፣ አጋንንትንም አወጡ፤ ይህም የወንጌልን እውነተኛነት አረጋገጠ። ጴጥሮስ አንካሳውን ሲፈውስ “ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ” ያለው የዚህ ኃይል መገለጫ ነው። (የሐዋ. ፫፥፮)

በልዩ ልዩ ልሳናት የመናገር ጸጋ፦

በበዓለ ኀምሳ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ሲወርድላቸው፣ ከተለያዩ ሀገራት ለመጡ አይሁድ በየቋንቋቸው ወንጌልን እንዲሰሙ በተለያዩ ልሳናት መናገር ጀመሩ፡፡ (የሐዋ. ፪፥፬-፲፩)

የአንድነትና የፍቅር ጸጋ፦

መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያትና ሐዋርያት ባጠመቋቸው ምእመናን መካከል ጥልቅ የሆነ አንድነትንና ፍቅርን አሳደረ። “ያመኑትም ሕዝብ ሁሉ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው…ገንዘባቸውም ሁሉ የጋራ ነበር” እንዲል፡፡ (የሐዋ. ፬፥፴፪)

በአገልግሎት መመራት፦

መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያትን ወዴት መሄድ እንዳለባቸውና ምን ማድረግ እንዳለባቸው በቀጥታ ይመራቸው ነበር፡፡ (ለምሳሌ የሐዋ. ፲፫፥፪፤ ፲፮፥፮-፯)

የቤተ ክርስቲያን አበው ስለ ጰራቅሊጦስ

የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነትና ሥራ በሰፊው አስተምረዋል፡፡

አጠቃላይ አስተምህሮ፦

መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሠረጸ፣ ከወልድ ጋር በአንድነት የሚመለክና የሚከበር፣ ሕይወትን የሚሰጥ፣ ሁሉን የሚችል፣ በሁሉ ቦታ የሚገኝ እውነተኛ አምላክ ነው፡፡ (ጸሎተ ሃይማኖት) እርሱ አጽናኝ፣ መካሪ፣ የጸጋ ሁሉ ምንጭ፣ የቅድስና መገኛና የእውነት ገላጭ ነው።

ቅዱስ ያሬድ፦ በድጓው “ወረደ መንፈስ ቅዱስ ላዕለ ሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን” (መንፈስ ቅዱስ በጽርሐ ጽዮን በሐዋርያት ላይ ወረደ) እያለ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ፣ ሐዋርያትን ማጽናቱንና ለዓለም የወንጌል ብርሃን እንዲሆኑ ማብቃቱን በዜማ ያመሰግናል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፦

መንፈስ ቅዱስ ፈሪ የነበሩትን ሐዋርያት ደፋሮች፣ ያልተማሩትን ጥበበኞች፣ ዓሣ አጥማጆችን የሰዎች አጥማጆች እንዳደረጋቸው በስፋት ያስተምራል። “ጴጥሮስ፣ ያ የካደው፣ ያ የፈራው፣ መንፈስ ቅዱስ ከወረደለት በኋላ እንዴት በድፍረት እንደቆመ እዩ” በማለት የጰራቅሊጦስን ኃይል ያስረዳል።

ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ፦

መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የክርስቶስን ትምህርት እንዳስታወሳቸውና የመጻሕፍትን ምሥጢር እንደገለጠላቸው “አጽናኙ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል” የሚለውን ቃል በመጥቀስ ያብራራል።

ሐዋርያት የቤተ ክርስቲያን መሠረቶች ሲሆኑ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ሕይወትና ነፍስ ነው። ዛሬም ቤተ ክርስቲያን የምትመራውና የምትኖረው፣ ቅዱሳት ምሥጢራትም የሚፈጸሙት በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና መሪነት ነው።

በዓለ ጰራቅሊጦስን ለምን እናከብራለን?

ይህን ታላቅ በዓል የምናከብርባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች፦

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ የተፈጸመበት፣ (ዮሐ. ፲፬፥፲፮-፲፯፣ ፳፮፤ ፲፭፥፳፮፤ ፲፮፥፯-፲፭)።

መንፈስ ቅዱስ በግልጽ ወርዶ ሀብቱን ያደለበት

ቤተ ክርስቲያን በይፋ ተመሥርታ የሐዋርያት ስብከት በኃይል የተጀመረበት፣ (የሐዋ. ፪፥፵፩)።

መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያትን ለወንጌል አገልግሎት በማብቃት ያበረታታበትና ለእኛም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችና ፍሬዎች በር የተከፈተበት በመሆኑ ነው።

የበዓሉ ትርጒምና ተገቢ አከባበር

የጰራቅሊጦስ መታሰቢያ በዓል የመንፈስ ቅዱስ መውረድን፣ መለኮታዊ ምሪትንና የኃይል መገለጥን ያሳያል። ይህ በዓል ሲከበር በመንፈስ ቅዱስ በመሞላት፣ በፍቅር፣ በሰላምና በእውነት ሕይወትን በመምራት ሊሆን ይገባል። የጰራቅሊጦስን በዓል እያከበሩ በልዩነት፣ በጥላቻ፣ በሐሰት ሕይወት መመላለስና በሥጋዊ ምኞት መጠመድ ከበዓሉ መንፈስ ጋር የሚቃረን ነው። የመንፈስ ቅዱስን መውረድ ስናከብር፣ ሕይወታችን፣ ተግባራችንና ንግግራችን በመንፈስ ሊለወጥና ሊታደስ፣ የመንፈስ ቅዱስንም ፍሬዎች ሊያፈራ ይገባል። “በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቻለሁ” እያለ በፀብ፣ በይቅርታ ቢስነት ወይም በማታለል የተሞላ ሰው፣ ገና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታና ኃይል እንዳልተረዳ ያሳያል፤ (ገላ. ፭፥፳፪-፳፫) ለእርሱም የጰራቅሊጦስ በዓል ከስያሜ ያለፈ የሕይወት ለውጥና የመንፈስ መታደስን አያመጣም።

እኛ የዘመኑ ክርስቲያኖች ከሐዋርያት ምን እንማር?

የሐዋርያት ሕይወትና አገልግሎት ለእኛ ለዘመኑ ክርስቲያኖች የጸና መሠረትና ሕያው ምሳሌ ነው፦

ለእግዚአብሔር መታዘዝ፦

ሐዋርያት የክርስቶስን ትእዛዝ በመጠበቅ መንፈስ ቅዱስን እስኪቀበሉ በኢየሩሳሌም በትዕግሥት እንደጠበቁ (የሐዋ. ፩፥፬) እና የጌታን ትእዛዝ እንደፈጸሙ፣ እኛም የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተን በሕይወታችን ልንተገብረው ይገባል።

የመንፈስ ቅዱስን ኃይል መፈለግና በእርሱ መመራት፦

የሐዋርያት አገልግሎት በመላው ዓለም የተስፋፋው በራሳቸው ጥበብና ጉልበት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነበር። እኛም በጸሎት፣ በቅድስናና በትሕትና መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን እንዲሠራና እንዲመራን መትጋት አለብን። (የሐዋ. ፩፥፰፤ ገላ. ፭፥፲፮)

በጸሎትና በኅብረት መትጋት፦

ቀደምት ክርስቲያኖች “በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት እንጀራንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር” (የሐዋ. ፪፥፵፪)። ጠንካራ የጸሎት ሕይወትና ከአማኞች ጋር ያለን ቅዱስ ኅብረት ለመንፈሳዊ እድገታችን ወሳኝ ነው።

በትዕግሥት መከራን መቀበል፦

ሐዋርያት ስለ ወንጌል ብዙ መከራ ቢቀበሉም (፪ኛ ቆሮ. ፲፩፥፳፫-፳፰)፣ ከመመስከር አልተመለሱም። እኛም በእምነታችን ምክንያት ፈተና ሲገጥመን በአርአያነታቸው እንጽና (፪ኛ ቆሮ. ፩፥፯)።

ትሕትናና ለጌታ ክብር መስጠት፦

ሐዋርያት ታላላቅ ተአምራትን ቢያደርጉም፣ ክብርን ለራሳቸው አልወሰዱም። ጴጥሮስ አንካሳውን ከፈወሰ በኋላ “በገዛ ኀይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህን እንዳደረግን ለምን ትኵር ብላችሁ ታዩናላችሁ?” (የሐዋ. ፫፥፲፪) በማለት ክብርን ለእግዚአብሔር ሰጥቷል። እኛም በምናደርገው ሁሉ ትዕቢትን አስወግደን ክብርን ለእግዚአብሔር እንስጥ።

ማጠቃለያ

በዓለ ጰራቅሊጦስ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ፣ የቤተ ክርስቲያንን ልደትና የሐዋርያትን ለወንጌል አገልግሎት መታጠቅ የምናስብበት ታላቅና ቅዱስ በዓል ነው። ይህ በዓል ታሪካዊ ክስተትን ከማስታወስ ባለፈ፣ የመንፈስ ቅዱስ ሕያውና ቀጣይነት ያለው ሥራ በሕይወታችንና በቤተ ክርስቲያን እንዲገለጥ፣ ራሳችንን በቅድስና የምናዘጋጅበት ነው። መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያትን እንዳዘጋጃቸው፣ እንዳበረታቸውና እንደመራቸው ሁሉ፣ ዛሬም ከእኛ ጋር ነው። የእነርሱ ሕይወት፣ ትምህርትና መሥዋዕትነት ለእኛ ለዘመኑ ክርስቲያኖች የማይነጥፍ የመንፈሳዊ ጥንካሬና የእምነት መሠረታችን ነው።

ከእነርሱ ትሕትናን፣ መታዘዝን፣ በጸሎት መትጋትን፣ በመንፈስ ቅዱስ መመራትንና ስለ ክርስቶስ ያለፍርሃት መመስከርን እንማር። ስለዚህ የጰራቅሊጦስን በዓል ስናከብር፣ ሕይወታችን በመንፈስ ቅዱስ ተለውጦና አዲስ ሆኖ የፍቅር፣ የሰላም፣ የእውነትና የቅድስና ፍሬዎችን ሊያፈራ፣ ከልዩነትና ከሥጋዊ ምኞት በመራቅ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታና ኃይል መረዳታችንን በተግባር ልናሳይ ይገባል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!