ርክበ ካህናት
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
‹ርክብ› ወይም ‹ረክብ› የሚለው ቃል ‹ተራከበ፤ ተገናኘ› ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲኾን፣ ትርጕሙም ማግኛ፣ መገኛ፣ መገናኛ ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፰፻፴፩)፡፡ ‹ክህነት› የሚለው ስያሜም ከጵጵስና ጀምሮ እስከ ዲቁና ድረስ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን መዓርጋት የሚያጠቃልል ቃል ሲኾን ካህን (ነጠላ ቍጥር)፣ ካህናት (ብዙ ቍጥር) በአንድ በኩል ቀሳውስትን የሚወክል ኾኖ በሌላ በኩል ደግሞ የጳጳሳት፣ የኤጲስ ቆጶሳት፣ የቀሳውስት፣ የዲያቆናት የጋራ መጠሪያ ነው፡፡ ‹ርክበ ካህናት› የሚለው ሐረግም የካህናት መገኛ፣ መገናኛ፣ ጉባኤ (መሰባሰቢያ)፣ መወያያ፣ ወዘተ የሚል ትርጕም አለው፡፡ በአጭሩ ‹ርክበ ካህናት› ማለት – የአባቶች ካህናት ማለትም የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት (የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት) ጉባኤ ማለት ነው፡፡
በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል እንደ ተገለጸው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ተገልጦ ከዐሥራ አንዱ ቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ምሳ በልቷል፡፡ ከምሳ በኋላም ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ጠርቶ ‹‹ትወደኛለህን?›› እያለ ከጠየቀው በኋላ እንደሚወደው ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ በቅደም ተከተል ‹‹በጎቼን ጠብቅ፤ ጠቦቶቼን አሰማራ፤ ግልገሎቼን ጠብቅ፤›› በማለት የአለቅነት ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ይህ ምሥጢር ለጊዜው ጌታችን ሐዋርያትን፣ ሰብዐ አርድእትንና ሠላሳ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት በአጠቃላይ መቶ ሃያውን ቤተሰብእ እንዲጠብቅና እንዲከባከብ ቅዱስ ጴጥሮስን ማስጠንቀቁን፤ ለፍጻሜው ግን የቤተ ክርስቲያን አባቶች (ጳጳሳት) መምህራንንና መላው ሕዝበ ክርስቲያንን እንዲጠብቁና እንዲያስተዳድሩ በእግዚአብሔር መሾማቸውን የሚያስረዳ ምሥጢር አለው (ዮሐ.፳፩፥፩-፲፯)፡፡
ይህን የጌታችንን ትእዛዝና የሐዋርያትን ሥልጣነ ክህነት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ጉባኤ ያደርጋል፤ የመጀመሪያው ጉባኤ ጥቅምት ፲፪ ቀን (የቅዱስ ማቴዎስ በዓል) ሲኾን፣ ሁለተኛው ደግሞ ርክበ ካህናት ነው፡፡ በዓሉ (ርክበ ካህናት) ወሩና የሚውልበት ቀን የበዓላትንና የአጽዋማትን ቀመር ተከትሎ ከፍና ዝቅ ቢልም በየዓመቱ የትንሣኤ በዓል በተከበረ በ፳፭ኛው ቀን በዕለተ ረቡዕ ይውላል፡፡ የአጽዋማትና የበዓላት ቀመር ከመዘጋጀቱ በፊት ማለትም በቅዱስ ድሜጥሮስ አማካኝነት ዐቢይ ጾም ሰኞ፣ ስቅለት ዓርብ፣ ትንሣኤ እሑድ፣ ርክበ ካህናት ረቡዕ፣ ዕርገት ሐሙስ፣ ጰራቅሊጦስ እሑድ እንዲኾን ከመደረጉ በፊት ርክበ ካህናት ግንቦት ፳፩ ቀን ይውል ነበር (መጽሐፈ ግጻዌ፣ ግንቦት ፳፩ ቀን)፡፡
ከዚህ በኋላ በዓለ ትንሣኤ በዋለ በ፳፭ኛው ቀን፣ በበዓለ ኃምሳ እኩሌታ በዕለተ ረቡዕ ርክበ ካህናት እንዲዘከር የቤተ ክርስቲያን አባቶች ወስነዋል፡፡ በያዝነው ዓመት በ፳፻፱ ዓ.ም የትንሣኤ በዓል ከተከበረበት ዕለት (ሚያዝያ ፰ ቀን) ጀምሮ ብንቈጥር ፳፭ኛው ቀን ግንቦት ፪ ቀን ነው፡፡ በመኾኑም የዘንድሮው ርክበ ካህናት ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ይውላል ማለት ነው፡፡ ይህ በዓል (ርክበ ካህናት) ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሲመሩ የቆዩ አባቶቻችን በጋራ በመሰባሰብ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተቀላጠፈ አገልግሎት እንደዚሁም ለምእመናን አንድነትና መንፈሳዊ ዕድገት የሚበጁ መንፈሳውያን መመሪያዎችን የሚያስተላልፉበት ዕለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያደርገው ጉባኤ የሚተላለፉ መመሪያዎችና የሚጸድቁ ውሳኔዎች ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ ለምእመናን አንድነት፣ ለአገር ሰላምና ደኅንነት የሚጠቅሙ ይኾኑ ዘንድ ዅላችንም በጾም በጸሎት እግዚአብሔርን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡
አምላካችን ቤተ ክርስቲያናችንንና አባቶቻችንን ይጠብቅልን፤ እኛንም ለአባቶች የሚታዘዝ ልቡና፣ ሓላፊነታችንን የምንወጣበትን ጥበብና ማስተዋልን ያድለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡