ርእዮ ለይብኪ ዐይነ ልብ ዘቦ (ሰቈቃወ ድንግል)
ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን
አባ ጽጌ ድንግል ይህን ቃል የተናገረው የቅድስት ድንግል ማርያምን ስደቷን፣ በስደቷ ጊዜም የደረሰባትን መከራና ኃዘን አምልቶ በገለጸበትና አምላክን በኅቱም ድንግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና የወለደች ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ክፍሉ ነው። ሙሉ ቃሉን እንደሚከተለው እንመልከተው።
በስመ እግዚአብሔር ሥሉስ ሕፀተ ግጻዌ ዘአልቦ፤ ሰቈቃወ ድንግል እጽሕፍ በቀለመ ዐንብዕ ወአንጠብጥቦ፤ ወይሌ ወላህ ለይበል ዘአንበቦ፤ ከማሃ ኃዘን ወተሰዶ ሶበ በኵለሄ ረከቦ ርእዮ ለይብኪ ዐይነ ልብ ዘቦ፤ ከአካል ሦስትነቱ መጉደል ከመለኮት አንድነቱ መጨመር በሌለበት በእግዚአብሔር ስም ያነበበው ሁሉ ወዮ ይል ዘንድ የድንግል ማርያምን ልቅሶ በዕንባ ቀለም ነጠብጣብ እጽፋለሁ፤ ዐይነ ልቡና ያለው ሰው እንደ እርሷ ኀዘንና መከራ ቢደርስበት አስተውሎ ይላል።
በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ኃዘን ወይም ለቅሶ የሚገባና የማይገባ ተብሎ በሁለት ይከፈላል። የማይገባ ኃዘን ማለት እናት አባት ሞተብኝ፤ እህት ወንድም ወይንም ዘመድ የለኝም፤ ርስት ጉልት ተወሰደብኝ ብሎ ማዘን ወይም ማልቀስ ነው። ምክንያቱም እንደ እናት እንደ አባት ሥላሴ፣ እንደ እህት እንደ ወንድም መላእክት እንደርስት እንደ ጉልት የማታልፍ መንግሥተ ሰማያት አለችና።
የሚገባ ኃዘን ወይም ለቅሶ የሚባለው ደግሞ የራስን ኃጢአት እያሰቡ እንደ አዳም፣ እንደ ዳዊት እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ማዘን፣ የጓደኛን ኃጢአት አይቶ እንደ ሳሙኤል ማልቀስ ነው፡፡ የሳኦልን ኃጢአት እያሰበ ያለቅስ ነበር፡፡ ግፍዓ ሰማዕታትን እያሰቡ ማልቀስ፤ ወለ እስጢፋኖስሰ ነሥእዎ ዕደው ጻድቃን ወቀበርዎ ወላሐውዎ›› እንዲል፤ ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን እያሰቡ ማዘን እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ በጌታ የደረሰውን የዕለተ ዓርቡን መከራ እያሰበ ለሰባ ዓመታት ያህል ቍፁረ ገጽ ሁኖ ነሯል። (ሐዋ.፰፥፪፤ ማቴ. ፭፥፬ አንድምታ ትርጓሜ)
ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል የሰማዐታት እናት የተባለች አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች የድንግል ማርያምን መከራዋን በማየት ‹‹ዐይነ ኅሊና ያለው አይቶ ያልቅስ›› በማለት የገለጸው የሚገባ ኃዘን ነው።
የሚገባውን ከማይገባው ለመለየት ደግሞ ዐይነ ኅሊና ያስፈልጋል። በዐይነ ሥጋ የማይታየውን፣ በእዝነ ሥጋ የማይሰማውን፣ ማየትና መስማት የሚቻለው ዐይነ ኅሊና እዝነ ልቡና ሲኖር ነው። የደረሰባት መከራና እንግልት፣ ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያስቡት ቀላል ሊመስል ይችላል። በዐይነ ኅሊና ሲመለከቱት ግን እጅግ የሚያስለቅስ ነው። ለማዘንም፣ ለማልቀስም፣ ይህ ሁሉ መከራ የደረሰው ስለማን እና በማን ምክንያት ነው ብሎ ለማሰብም ዐይነ ኅሊና ስለሚያስፈልግ ዐይነ ኅሊና ያለው አይቶ ያልቅስ በማለት ያስረዳል።
ሊቁ እንዲሁ የእመቤታችንን ኃዘን በገለጸበት በዚሁ በሰቆቃወ ድንግል ድርሰቱ የሚከተለውን ይናገራል። ‹‹ብክዩ ኅዙናን ኀልየክሙ ስደታ፤ ወላሕዉ ፍሡሓን ተዘኪረክመ ብዝኃ ሠናይታ፤ ማርያም ተአይል ከመ ዖፍ ውስተ አድባረ ግብፅ ባሕቲታ፤ ተአወዩ በኃጢዖታ ሀገረ አቡሃ ኤፍራታ፤ ወደማ ሕፃናት ይውኅዝ በኵሉ ፍኖታ ባሕረ ማሕው ድንግል ትነብር ውስቴታ፤ ያዘናችሁ ሁሉ ስደቷን አስባችሁ አልቅሱ፤ ደስ ያላችሁም ሁሉ የበጎነቷን ብዛት አስባችሁ እዘኑ፤ ማርያምም በግብፅ በረሀዎች እንደ ብቸኛ ወፎች ትዞራለች፤ የአባቷን ሀገር ኤፍራታን በማጣቷ ታለቅሳለች፤ የሕፃናትም ደም በመንገዷ ሁሉ ይፈሳል።››
የድንግል ማርያም በጎነት፣ ርኅራኄ፣ ቸርነት ለሰው ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ ነውና የበጎነቷን ብዛት እያሰባችሁ አልቅሱ ተባልን።
በድጋሜም ሊቁ ‹‹አኮ ለሰብእ ባሕቲቱ ማርያም ሠናይት እስመ ርኅርኅተ ልብ አንቲ ለኵሉ ፍጥረት፤ ማርያም ሆይ አንቺኮ ርኅርኅት የሆንሽው ለሰው ብቻ አይደለም፤ ለፍጥረት ሁሉ ርኅርኅና ነሽ እንጂ›› በማለት እንደገለጸው ለውሻ የራራች እናት የሚያዝንላት አጥታ በግብፅ በረሀ ስትንከራተት ይህን የበጎነቷን ብዛት እና በርሷ ላይ የደረሰው ስቃይ እያሰባችሁ እዘኑ አለን። አባ ጽጌ ድንግል በድንግል ማርያም ኃዘን ልቡ ከመነካቱ የተነሣ የደረሰባቸውን ሁሉ ይጠራል።
በዘመኑ ለእስራኤል ሲያለቅስ የነበረ ኤርምያስንም እንዲህ በማለት ይጠራዋል። ‹‹ነዓ ኤርምያስ እምአናቶት ለወለተ ነቢያት ታስቆቅዋ በኃጢአ አብያት ዘተኅድር ለቁስቋም በውስተ በድዋ፤ ወበል አክይስት እጎሊሆን አጥበዋ፤ ሊተሰ አዋልደ ሕዝብየ ፄዋ፤ ከመ ሰገኖ በገዳም ሀለዋ፤ ኤርምያስ ሆይ ማደሪያ በማጣት በቍስቋም ምድረ በዳ (በረሀ) ያደረች የነቢያትን ልጅ ታላቅሳት ዘንድ ከአናቶት እና እባቦችም ግልገሎቻቸውን አጠቡ፤ በምርኮ ያሉ የወገኔ ሴቶች ልጆች ግን እንደ ሰጎን በዱር አሉ በል።›› (ሰቆቃወ ድንግል)
ማንኛውንም ነገር በትምህርት ብቻ ከሚያውቀው ሰው ይልቅ በተግባር ያለፈበት ሰው የተሻለ ይረዳዋል። እስራኤል በባቢሎናውያን በተማረኩ ጊዜ መከራቸውን እንዲረዳና እንዲያጸናናቸው ያለበደሉ የተማረከው ኤርምያስ ስለ እስራኤል መከራ አብዝቶ ያዝን ነበር። ያን ጊዜ የነበረውን ሕይወት በዐይነ ልቡና እየቃኘ ዛሬም ድንግል ማርያምን ታላቅሳት ዘንድ ከአናቶት እና እያለ ይጠራዋል። በእርግጥም በተግባር ያወቀውን፣ የኖረበትን፣ ያለፈበትን ኀዘን ዛሬም እያዘነ በኀዘን ልቧ የተሰበረውን የአምላክ እናት ማጽናናት የሚችለው ኤርምያስ ነውና ሊጠራ የሚገባው ሰው ነው። ይህ ጊዜ ስለ እመቤታችን ስደትና መከራ የምናዝንበት ብቻ ሳይሆን ስለ ሀገራችን፣ ስከ ቤተ ክርስቲያናችንና ስለወንገኖቻችንም የምናለቅስበት ነው፡፡
ሀገራችን፣ ቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ነገሮቿን ተነጥቃ በኃዘን በመከራ ላይ ትገኛለች። ወገኖቻችንም ስደተኞች ሁነው በረሀ ለበረሀ እየተንከራተቱ ነው። ቤተ ክርስቲያናችን የሚያዝንላት የሚራራላት፣ ከደረሰባት ችግር በአጠቃላይ ከገጠማት የጭንቅና የመከራ ወጥመድ የሚያወጣት ትፈልጋለች። በመሆኑም መከራዋን፣ ኀዘኗን፣ ስደቷን፣ እንግልቷን ወዘተ እያሰበ የሚያለቅስ ሰው ያስፈልጋታል።
በእውነትም ዐይነ ልቡና ያለው ለሀገር፣ ለወገን፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለምእመናን፣ ሊያለቅስ ይገባዋል። አግባብነት ያለው ሰው ኀዘን ችግርን ይፈታል። በታሪክ እንደምንረዳው እነ ሕዝቅያስ፣ እነ መርዶክዮስ፣ እነ አስቴር፣ የነነዌ ሰዎች ወዘተ ከልብ በመጸለይ፣ በማዘን፣ ምርር ብሎ በማልቀሳቸው የመጣባቸው ችግር ተወግዶላቸዋል። ስለዚህ ዐይነ ልቡና ያለው የቤተ ክርስቲያኗንና የምእመናኗን መከራ፣ ስቃይ፣ እንግልት ዐይቶ ያልቅስ። በእውነት ከልብ ወደ እግዚአብሔር በማልቀስ አምላካችን በነቢዩ ኢዩኤል አድሮ ‹‹በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ›› (ኢዩ.፪፥፲፪) እንዳለን ወደ እርሱ ተመልሰን የሚገባውን ኀዘን አዝነን ይህን ውስብስብ ያለ የችግርና የመከራ ዘመን አሳልፎን የሰላሙን ዘመን እንድናይ እግዚአብሔር በቸርነቱ ይፍቀድልን፣ ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ አትለየን፤ አሜን።