ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ
እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡ ዘመነ ማቴዎስም፣ ዘመነ ማርቆስም፣ ዘመነ ሉቃስም ሆነ ዘመነ ዮሐንስ በአራቱም ዘመናት አስቀድሞ ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ ይዘከራል፡፡ ዮሐንስ የስሙ ትርጉም «ጸጋ እግዚአብሔር» ማለት ነው፡፡ ዘመናት ዘመናትን እየወለዱ፣ ሰዓታት ደቂቃን ቅጽበትን /ሰኮንድን/ ሳይቀር እየሰፈሩ/እየቆጠሩ/ ዕለታት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራት ዓመታትን አሁን ላለንበት ዘመን ደርሰናል፡፡ ዓውደ ዓመት በግእዝ ሲሆን በአማርኛ የዘመን መለወጫ/ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕንቁጣጣሽ እየተባለም ይጠራል፡፡
የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱን በመረዳት የቤተክርስቲያን አበው የበዓላቱን ድንጋጌ በወሰኑበት ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ ርዕሰ ዓውደ ዓመት በሚሆን መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ አባቶች ደንግገዋል፡፡ / ድርሳነ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 1ጠ 3/ ይህንንም በዓል አባቶቻችን በርእሰ ዓውደ ዓመት ማክበር እንደሚገባ አስበው ያደረጉት ነው፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ያረፈበት ቀን ሆኖ አይደለም፡፡ ለአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወይም ርእሰ ዓውደ ዓመት «ቅዱስ ዮሐንስ» ይባላል፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር የዓመቱን መጀመሪያ /መስከረምን/ ሲያትት «ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው በማለት ያስረዳል፡፡ የዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12 ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ቀኑ እየጎደለ ይሔዳል፡፡
ከዚህ በመቀጠል በዓሉ በተለያየ ስያሜ ስለመጠራቱና ትርጓሜያቸውን እንመለከታለን፡፡
ዘመን መለወጫ
በመሠረቱ ዘመን ተለወጠ ሲባል የሚለወጡት ወራቱ ብቻ አይደሉም፡፡ በወቅቱ የሚከሰቱት/የተከሰቱት/ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር /ገጠመኝ/ ሲሆን ወራቶቹ ግን ያው በየዓመቱ እየተፈራረቁ ይመጣሉ፡፡ ዘመን መለወጫ ላይ የሰው ልጆች ሕይወት ሊለወጥ ይገባል፡፡ ተማሪው ተምሮ ወደቀጣዩ ክፍል /ደረጃ/ የሚለወጥበት፣ ገበሬው የክረምቱን ወራት በሚገባ ተጠቅሞ የሚቀጥለውን የበጋ ወራት የሚቀበልበት፣ ሠራተኛው የክረምቱን ዝናብ ታግሶ የፀሐይን ወራት የሚቀበልበት ሌላውም እንደዚያ ሆነው ወራቶቹ በዚያ ዘመን ያለው የተፈጥሮ ክስተቶች የሚለወጥበት ዘመን ተለወጠ እየተባለ ይነገራል፡፡
እንቁጣጣሽ
በዚህ በአዲሱ ዓመት የሁለተኛው ሺሕ ማብቂያና የሦስተኛው ሺሕ መግቢያ ላይ እንገኛለን፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሁለት ሺሕ ዓመተ ምሕረት ያሳለፈቻቸውን መልካም ሥራዎችና የደረሰባትን መጥፎ ሥራዎችን አልፋ አሁን ላለው ትውልድ ደርሳለች፡፡ ይሕ ትውልድ ደግሞ በሦስተኛው ሺሕ ዓመት እምነቷን፣ ሥርዓቷን፣ ትውፊቷን አውቆ ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ አደራ አለበት፡፡
ለዚህም የሚረዳውን ገዳማትና አድባራትን በማጠናከር ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ዘመናዊ አስተዳደር በመዘርጋት ከእኅት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ጥሩ ግንኙነት በማድረግ የበኩሉን ሊወጣ ይገባዋል፡፡
ሺሕ ዓመቱ ሲለወጥ በዋዜማው ላይ በምንገኘኝበት ወቅት በእነዚህ ነገሮች ላይ ተቀራርቦ በመሥራት የሰው ዘር በሙሉ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግን ገንዘብ ልናደርግ ይገባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር