ርእሰ ዐውደ ዓመት

እንኳን አደረሳችሁ!

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ጳጉሜን ፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ዐውድ የሚለውን ኃይለ ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላታቸው “ዙሪያ፣ ክበብ፣ ከዓመት እስከ ዓመት” በማለት ይተረጉሙታል፤ ዐውደ ዓመት የሚለው ጥምር ቃል ደግሞ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ዕለት በማለት ይገልጡታል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፮፻፹፰)
በአንድ ዓመት ውስጥ እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ጳጉሜን ጨምሮ ፲፫ ወራት፣ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናት፣ በአራት ዓመት አንዴ ደግሞ ሦስት መቶ ስልሳ ስድስት ቀናት አሉት፤ ይህ ተፈጽሞ ሌላ አዲስ ዓመት ሲተካ የመጀመሪያው ዕለት ርእሰ ዐውደ ዓመት ይባላል፤ አንዱ ዘመን አልፎ ሌላኛው ዘመን ሲተካ ያለው የአዲስ ዓመት መጀመሪያው ዕለት ነው፤ ዘመናቱን አራቱ ወንጌላውያን ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ በአራት ዓመት አንዴ እየተፈራረቁ ይገዙታል (ተሰይመውበታል)፡፡

በአንድ ዓመት ውስጥ ያለው ጊዜ የተፈጥሮ ክስተትን (ወቅቱን፣ ለውጥን) ተከትሎ በአራት ይከፈላል ክረምት፣ሐጋይ፣መጸው፣ ጸደይ በመባል ፺፩ ቀን ፺፩ ቀን ይገዛሉ፡፡ ከመስከረም ፳፭ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ያለው መጸው ይባላል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፮፻፭) በዚህ መጸው ሠልጥኖ፣ የከረመው ቁር ወደ ታች ተቀብሮ፣ የከረመ ዋዕይ ወደ ላይ ሲወጣ ከታች ሙቀቱ፣ ከላይ ጠሉ ሲሰማቸው አዝርእት አትክልት ያድጋሉ፤ይገዝፋሉ፤ያብባሉ፤ያፈራሉ፡፡

ከታኅሣሥ ፳፭ እስከ መጋቢት ፳፭ ቀን ያለው ወቅቱም ሐጋይ ( በጋ) ይባላል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፬፻፴፬) በዚህም በሐጋይ ሠልጥኖ፣ የቆየው ቁር ፈጽሞ ተቀብሮ፣ የከረመ ዋዕይ ጽናት የተነሣ አዝርእት አትክልት ይደርቃሉ፤ ታጭደው፣ ተወቅተው በጎተራ በሪቅ ይገባሉ፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ‹‹በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ…›› ተብሎ እንደተገለጸው በክረምቱ ዝናሙን ችሎ፣ ቁሩን፣ ተግሦ- አረሙን እያረመ እየተንከባከበ የነበረው ገበሬ የአምላክን ችሮታ(ስጦታ) ተቀብሎ በደስታ ከሪቅ ከጎተራው የሚከትበት ወቅት ነው፡፡ (መዝ.፻፳፭፥፭)

ከመጋቢት ፳፭ ጀምሮ እስከ ሰኔ ፳፭ ያለው ፀደይ ይባላል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፯፻፵፬ ) በዚህ ወቅት በጸደይ ሠልጥኖ፣ የባጀ ዋዕይ ወደታች ተቀብሮ የነበረ ቁር ወደ ላይ ሲል፣ ከላይ ሙቀቱ ከታች ጠሉ ሲሰማት ምድር ትለሰልሳለች፤ የዘሩባትን ሁሉ ታበቅላለች፡፡
ከሰኔ ፳፭ አስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ደግሞ ክረምት ይባላል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፭፻፵፰) በዚህም በክረምቱ ሠልጥኖ፣ የነበረ ዋዕይ ፈጽሞ ሲጠፋ፣ ተቀብሮ የነበረው ቁር ሲወጣ፣ ከውኃው ብዛት፣ ከምንጩ ጽናት የተነሣ ምድር “እፈርስ እፈርስ እናድ እናድ” ትላለች፤ ከዚህም በኋላ ጌታ ደመና ገልጦ፣ ፀሐይ አውጥቶ ምድርን ያረጋታል፤ ያጸናታል፡፡ የተዘራው ዘር ከቅጠልነት ወደ አበባነት ይለወጣሉ፤ ፍሬ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ያበሥራሉ፤ አምላኩን ተማምኖ ቅንጣት ዘርን በምድር ከርስ የቀበረውን የገበሬውን ተስፋውን ይፈነጥቃሉ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ‹‹ምድርን ጎበኘሃት፤ አጠጣኻትም፤ ብልጽግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ እንዲሁ ታሰናዳህና፤ ትልምዋን ታረካለህ፤ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፤ ቡቃያዋንም ትባርካለህ፤ በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፤ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል፤ የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፤ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ፤ ማሰማሪያዎች መጎንችን ለበሱ፤ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፤ በደስታ ይጮኻሉ፤ ይዘምራሉም…›› በማለት እንደ ገለጸው፡፡ (መዝ.፷፬፥፱-፲፫)

አምላካችን እግዚአብሔር ወቅትን በወቅት ቀይሮ፣ ቀንን በሳምንት፣ ሳምንትን በወራት፣ ወራትን በዓመታት እያፈራረቀ ከዘመን ዘመን ያሸጋግራል፡፡ የእንዚናዙ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ የእግዚአብሔርን ቅድምና በተናገረበት ድርሳኑ ‹‹…እግዚአብሔርን በጌትነት ከዘመን አስቀድሞ የነበረ ትክክል በሚሆኑ በሦስቱ አካላት እንዳለ እናውቀዋለን ፤ከዘመን አስቀድመው የነበሩ ዘመንን አሳልፈው የሚኖሩ ናቸውና፡፡›› (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ምዕራፍ ፷፥፲)

ለዘመኑ ጥንት ፍጻሜ የሌለው ጌታ የጨለማውን ጊዜ ክረምቱን አሳልፎ፣ ዘመንን በዘመን ተክቶ፣ ምድርን በእህል (በሰብል) ሸፍኖ፣ ድርቀቷን በአረንጓዴ ዕፅዋት አስውቦ፣ ብሩህ ተስፋን በሰው ልጆች ልቡና ያሠርፃል፤ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ሰዎች በአዲስ መንፈስና ዕቅድ በአዲስ ሰብእና፣ በዕድሜ ላይ በተጨመረው ሌላኛው ዘመን ዕቅዳቸውን ለማሳካት፣ ምኞታቸውን ለማስመር ታትረው ይነሣሉ፤ የወቅቱ መቀየር በራሱ አዲስ ነገር እንዲያስቡ ያነቃቃል፤ በአዲስ ዓመት መግቢያ (በርእሰ ዐውደ ዓመት) የአጽዋማት መግቢያ፣ የበዓላት መከበሪያ ቀንና ዕለት ይታወጁበታል፤ ባለፈው ዓመት ዘመኑን በስሙ ተሰይሞለት የነበረው ወንጌላዊ ለተረኛው ማስረከቡን ይበሠርበታል፡፡

ሊቃውንት በቅኔ በማኅሌቱ ከዋዜማው ጀምረው የዘመናት ጌታ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፤ በዕለቱ የሚታወሱ ቅዱሳንን ያዘክራሉ፡፡ ካፈለው ስሕተታችን ታርመን፣ ከድክመታችን በርትተን፣ ነገን ከዛሬ የተሻለ ሆኖ ለማግኘት በትጋት አደግድገን፣ ስንፍናን አርቀን፣ ቂምን በይቅርት ሽረን፣ ጥላቻን በፍቅር ተክተን፣ የሰማይ ጠል የምድርን ውበት እንዳስዋበው፣ በሰማነው ቃለ እግዚአብሔር ውስጠታችን ነጽቶ፣ ከኃጢአት ብለየት ታድሰን፣ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ተቀድሰን አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ ማንንት ለመቀበል እንነሣ!

መልካም አዲስ ዓመት!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!