ርእሰ ዐውደ ዓመት

እንኳን ለዘመነ ማቴዎስ አደረሰን!

እነሆ ለ፳፻፲፫ ዓ.ም. ዘመነ ማቴዎስ ዐውደ ዓመት እንደርስ ዘንድ የአምላካችን እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆነ፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በሥርዓቱ መሠረት የበዓላቱና የአጽዋማቱ መደብ የሚታወቅበትና የዘመናቱ ሂደት ተቀምሮ የሚታወጅበት ዕለት መስከረም አንድ ቀን ርእሰ ዐውደ ዓመትን ታከብራለች፡፡

ርእሰ ዐውደ ዓመት መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስንም ያወሳናል፤ የቅዱስ ዮሐንስ ዕረፍት (ምትረት ርእስ) የሚታሰበው መስከረም ሁለት ቀን ቢሆንም እንኳን ተግባሩ በዘመነ ወንጌልና በዘመነ ሐዲስ መካከል የነበረ መሸጋገሪያ ነው፡፡ መታሰቢያ በዓሉም የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ከሚሆነው ካለፈው ዓመት የሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ወደሚሆነው አዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ በሆነው በመስከረም አንድ ቀን ይከበራል፡፡

በቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ከመስከረም አንድ እስከ ስምንት ባሉት ዕለታት ክብረ ቅዱስ ዮሐንስን የሚያወሱ መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም የዘመን መለወጫን አዲስ ዓመት በዓል አስመልክቶ እንደነገረን ‹‹ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ፤ የዓመት በዓል ራስ ዮሐንስ መጥቅዕና አበቅቴን የምትወልድ ነህ›› እየተባለ ይዘመርለታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ያስተማረውን ትምህርትና ገድሉን የሚያመለክት ስብከት ይሰበካል፤ ትምህርቱም ይሰጣል፡፡

ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ ‹‹እነሆ÷ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፡፡ የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ የአዋጅ ነጋሪ ድምጽ፤ ዮሐንስም በምድረ በዳ ያጠምቅ ነበር፤ ኃጢአትንም ለማስተስረይ የንስሓ ጥምቀትን ይሰብክ ነበር፡፡ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ሁሉንም ያጠምቃቸው ነበር»  ብሎ ጽፎልናል፡፡

የካህኑ ዘካርያስ ልጅ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ላይ ተነስቶ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ›› እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት በምድረ በዳ እያስተማረና የንስሓ ጥምቀት እያጠመቀ በዘመነ ወንጌል መጀመሪያ ምዕራፍ ተገኝቷልና፡፡ እንዲሁም መጥምቁ ዮሐንስ በነቢያት መጨረሻ በሐዋርያት መጀመሪያ ተገኝቶ ዘመነ ሐዲስን እንደሰበከና ከዘመነ ብሉይ ወደ ዘመነ ሐዲስ መሸጋገሪያ ጊዜ ላይ ስለነበረ ያለፈውን ዘመን የምንሸጋገርበት የዘመን መለወጫ ቀን የቅዱስ ዮሐንስ መታሰቢያ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ (ማር.፩፥፪-፭)

በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ላይ ‹‹እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዱአቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም›› ብሎ ጌታችን ስለ ዮሐንስ በተነገረለት መሠረት የጻድቃን የሰማዕታት ርእስ እንደመሆኑ አዲስ ዓመትም የበዓላት ሁሉ በኩር ርእስ ነውና በስሙ ተጠርቷል፡፡ (ማቴ.፲፩፥፲፩)

የዘመን ቆጠራ ከጌታችን ልደት በፊት የነበረው ሃይማኖታዊ ፋይዳ የሰው ልጆች ሁሉ /በተለይ አበውና ነቢያት/ በተስፋ ይጠብቁት የነበረውን የጌታችንን መምጣት የቀረውን ጊዜ ለማወቅ ነበር፡፡ ተስፋው ከተፈፀመ በኋላ ደግሞ የዘመን ቆጠራ ዋና አገልግሎቱ በዓላትና አጽዋማት በዓመቱ የሚወሉበትን ዕለት ለማወቅ ነው፡፡ እነዚህ በዓላት እግዚአብሔር በተለያዩ ዘመናት ለሰው ልጆች ያደረጋቸው ድንቅ ነገሮችና ውለታዎች የሚታሰቡባቸው ናቸው፡፡ በመጀመሪያ እነዚህ በዓላት ሁሉ መጀመሪያ በተደረጉባቸው ቀናት ይከበሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ ስቅለት መጋቢት ፳፯፣ ትንሣኤ መጋቢት ፳፱፣ ልደት ታኅሣስ ፳፱፣ የቅዱስ ሚካኤል በዓል ኅዳር ፲፪፣ ወዘተ. . ማለት ነው፤ አጽዋማቱም እንዲሁ፡፡

የዘመን መለወጫ (ርእሰ ዐውደ ዓመት) ዕንቁጣጣሽ ተብሎም እንደሚጠራ ታሪክ ያወሳናል፡፡  ስያሜውም ለበዓሉ የተሰጠው በንግሥተ ሳባ ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡ ንግሥቷ ጠቢቡ  ሰሎሞንን ለመጎብኘት በሔደችበት ወቅት ጸንሳ ቀዳማዊ ምኒልክን በወለደች ጊዜ ሕዝቡ ንጉሥ ተወለደ ብሎ እልል እያሉ «አበባ ዕንቁ (አብረቅራቂ ድንጋይ) ጣጣሽ (ገጸ በረከት)» እያለ ገጸ በረከት ለንግሥቲቱ አበረከቱ፡፡ ያ የዘመን መለወጫ በዓልም ልጃገረዶች የአበባ ገጸ በረከት የሚያቀርቡበት ስለሆነ ዕንቁጣጣሽ ተባለ፡፡

ዕንቁጣጣሽ ግጫ ማለትም ነው፤ ግጫን (እርጥብ ሣርን) እንደስጦታ መስጠጥ የተጀመረው በኖኅ ዘመን ነው፡፡ ኖኅ የጥፋት ውኃ በጎደለ ጊዜ መጉደሉን ለማረጋገጥ ርግብን ልኳት የወይራ ቅጠል አምጥታለች፤ ይህ የሆነበት ወቅት የመስከረም ወር በመሆኑ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የዘመን መለወጫ ሆነ፡፡ በርግቧ አምሳልም ልጃገረዶች የተለያየ ዓይነት ሣርና አበባ በመያዝና በማደል በዓሉን ያከብራሉ፤ በሣሩ ስምም በዓሉ ዕንቁጣጣሽ ተባለ፡፡

 እግዚአብሔር አምላክ አዲሱን ዓመት የሰላም እና የጤና ያድርግልን፤ አሜን፡፡