ሥዕለ አድኅኖ

ክፍል አምስት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

ጥር ፳፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት አላችሁልን? ዘመነ አስተርእዮ ተብሎ በሚጠራው ወርኃ ጥር በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ብዙ በዓላትን አክብረናል፤ የጥምቀት፣ የቃና ዘገሊላ እንዲሁም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዕረፍቷ መታሰቢያ ዓመታዊ ክብረ በዓልና የቅዱሳን መላእክት፣ የቅዱሳን አባቶቻችን፣ እናቶቻችንን በዓላት አክብረናል፡፡ እንዴት ነበር ልጆች! በጣም ልዩ ነበር አይደል? ታዲያ እነዚህ መንፈሳዊ በዓላት ወደፊትም እንዲከበሩ የእናንተ ጉልህ አስተዋጽኦ ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም የነገዋን አገርና ቤተ ክርስቲያን የምትረከቡት እናንተ ስለሆናችሁ በዓሉን ከማክበራችሁ በተጓዳኝ ለምን እንደሚከበርና የአከባበበር ሥርዓቱን በመጠየቅ መረዳት አለባችሁ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ታዲያ ይህን አደራ ለመረከብ በመንፈሳዊውም፣ በዘመናዊው ትምህርት ጎበዞች መሆን አለባችሁ! በነገራችን ላይ ዘመናዊ ትምህርታችሁ የመንፈቀ ዓመት ፈተናችሁን እየተፈተናችሁ ያላችሁ፣ ለመፈተንም በዝግጅት ላይ ያላችሁም በርትታችሁ ማጥናት እንዳለባችሁ መዘንጋት የለበትም፡፡ ልጆች! ባለፈው ትምህርታችን በሥዕለ አድኅኖ ከተደረጉ ተአምራት ለአብነት ያህል ተመልክተን ነበር፤ ለዛሬ ደግሞ ቅዱሳን ሥዕላትን እንዴት አክብረን መያዝ እንዳለብን እንመለከታለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሥዕለ አድኅኖ (ቅዱሳት ሥዕላት) ለምን እንደሚሳሉ፣ ማን እንዲሣሉ እንዳዘዘ፣ እንዴት ደግሞ እንደሚሣሉና፣ ለቅዱሳት ሥዕላት የምንጠቀማቸውን ቀለማትና ምሥጢራዊ ትርጒማቸውን እንዲሁም በሥዕለ አድኅኖ (በቅዱሳት ሥዕላት) የተደረጉ ተአምራትን ተመልክተናል፤ ዛሬ ማጠቃለያውን እንመለከታለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱሳን አባቶቻችንንና እናቶቻችን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕለ አድኅኖ ፊት ተንበርክከው፣ ግንባራቸውን መሬት አስነክተው ሰግደው (ተደፍተው) በመጸለይ ሲማጸኗት እመቤታችን ተገልጣ ታናግራቸው ነበር፤ ለጥያቄአቸው መልስን ትሰጣቸው ነበር፡፡ውድ ልጆች! በሥዕለ አድኅኖ ፊት ቆመን፣ ተንበርክከን ወይም በግንባራችን ተደፍተን በእምነት ሆነን የምንጸልየው ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ “የእግዚአብሔር ዓይኖቹ ወደ ጻድቃኑ ጆሮዎቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸው” እንዳለው (መዝ.፴፬፥፲፭) በእነርሱ ላይ አድሮ የሚገለጠውን እግዚአብሔር አምላካችንን ለማመስገን፣ ቅዱሳንን እንደክብራቸው ለማክበር ብሎም ጸሎታችንን እና ልመናችን በእነርሱ አማካኝነት ወደ እግዚአብሔር አምላካችን እንዲደርስ እና እንዲወጣ ነው።

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በሌላም በኩል የቅዱሳኑ ሥዕላት የቅዱሱን ተጋድሎ፣ ግብራቸውን፣ የእምነት ጽናት አሳጥሮ ለማሳየት ይሣላሉ፤ ታዲያ ሥዕለ አድኅኖ በቤታችን ካለ ለጸሎት በተዘጋጀ (የጸሎት ቤት) በክብር መቀመጥ አለባቸው፤ እኛ ለሥዕለ አድኅኖ በሰጠነው ክብር ልክ እንከብራለን፤ ሥዕለ አድኅኖ (ሥዕለ ቅዱሳን) አምልኮን ለመፈጸም ይጠቅማሉ። ይኸውም ለእግዚአብሔር አምላክነቱን ከሃሌ ኩሉ (ሁላችን ቻይ) መሆኑን ፈጣሪነቱን እያሰብን የአምልኮ ምስጋና፣ ጸሎት፣ ልመና እናቀርባለን። ለቅዱሳን ደግሞ ስለተገባላቸው ቃልኪዳን የበረከት ተካፋይ ያደርጉን ዘንድ የቃል ኪዳናቸው ተሳታፊ ሆነን በምልጃቸው ጠብቆት ሥር እንሆን  ዘንድ ስለተሰጣቸው ጸጋ ብለን እናመሰግናቸዋለን፤ እንለምናቸዋለን።

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሥዕለ አድኅኖ የሥዕሉን ባለቤት የሚወክሉልን በመሆናቸው በክብር ልንይዛቸው ይገባል፤ ሥዕለ አድኅኖ ከሌሎች ሥዕላት፣ ከእኛ ፎቶግራፎች ይለያሉ፡፡ ሲሣሉም ሆነ፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አልያም በቤታችን ሲቀመጡ በተከበረ ሥፍራ፣ በመጋረጃ ተሸፍነው መሆን አለበት፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች!  በሥዕለ አድኅኖ ብዙ ተአምር ተደርጓል፤ ወደፊትም እንደ እምነታችን ጽናትና መንፈሳዊ ሕይወታችን ብስለት በሥዕለ አድኅኖ ድንቅ ተአምራትን ልንመለከት እንችላለን፤ ሰፊና ጥልቅ ከሆነው ስለ ሥዕለ አድኅኖ (ቅዱሳት ሥዕላት) ለተከታታይ አምስት ክፍላት ስንማር ቆይተናል፤ በርካታ ቁም ነገሮችን እንዳገኛችሁ እምነታችን ጽኑ ነው፤ይህን ትምህርት ከተማርንበት ሰዓት አንሥቶ ለሥዕለ አድኅኖ (ለቅዱሳን ሥዕላት) ክብር ልንሰጥ በአግባቡ ልንይዛቸው እንደሚገባ ተገንዝባችኋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ! ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!