ሥዕለ አድኅኖ
ክፍል አራት
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ታኅሣሥ ፳፯፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት አላችሁልን! እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ! ልጆች ዘመናዊ ትምህርታችሁስ እንዴት ነው? የዓመቱ አጋማሽ እየደረሰ በመሆኑ በርትታችሁ በማጥናት ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለባችሁ በዚሁ አጋጣሚ ልናሳስባችሁ እንወዳለን! ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ ደግሞ በሰንበት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መማርን፣ ማገልገልን እንዳትረሱ፤መልካም!
ባለፈው ስለ ሥዕለ አድኅኖ በተማርነው ትምህርት ሥዕለ አድኅኖ ሲሳሉ ምን ዓይነት ቀለማት መሆን እንዳለባቸውና የቀለማቱ ትርጒም (ምሳሌነት) ምን እንደሆነ በመጠኑ ተመልክተናል፡፡ በዚህ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ደግሞ በሥዕለ አድኅኖ የተደረጉ ተአምራትን እንማራለን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስለ ሥዕለ አድኅኖ ባለፈው ትምህርታችን ስንማር ሥዕል ማለት ምን ማለት እንደሆነ አይተናል አይደል? ታስታውሳላችሁ ብለን እናስባለን! ቅዱሳት ሥዕላት ሲሳሉ የምንጠቀማቸው ቀለማት ምሥጢራቸው ምን እንደሆነም በመጠኑ ስንማር ነበር፡፡ በክፍል አራት ደግሞ በሥዕለ አድኅኖ (ቅዱሳት ሥዕላት) ከተደረጉ ተአምራት የተወሰኑትን ለአብነት እንመለከታለን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ማርታ የምትባል መልካምና ደግ እንግዶችን በቤቷ የምታስተናግድ እመቤታችንን ከልቧ የምትወድ ሴት ነበረች፡፡ አንድ ቀን አባ ቴዎድሮስ የሚባል መነኩሴ ቤቷ በእንግድነት መጣ መስተንግዶ አድርጋለት ሊሄድ ሲል ወዴት እንደሚሄድ ጠየቀችው፡፡ ከዚያም መነኩሴው ቴዎድሮስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ነገራት፡፡ እርሷም ከኢየሩሳሌም አገር የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕል እንዲያመጣላት ጠየቀችው፡፡ እርሱም “እሺ” ብሏት ሄደ፡፡
ልጆች ይገርማችኋል! አባ ቴዎድሮስ ኢየሩሳሌም ደርሶ ሲመለስ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ምስለ ፍቁር ወልዳ (እመቤታችን ልጇ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ታቅፋ) ያለውን ሥዕል ገዛላትና ማርታ ወደምትኖርበት ጼዴንያ ወደሚባው አገር ሲጓዝ በሚያስፈራ ጫካ (ዱር) ውስጥ ወንበዴዎች አገኙት፤ ሊሸሽ (ሊሮጥ) ሲል ከሥዕሏ ‹‹መንገድህን ሂድ›› የሚል ቃል ወጣ፤ ሳይፈራ ቀጥ ብሎ ወደፊት ተጓዘ (ሄደ) ማንም የተከተለውም ሆነ ሊጎዳው የፈለገ ማንም አልነበረም፡፡ እንደገናም አንበሳ መንገድ ላይ አገኘውና ሊበላው ሲጮህ ከሥዕሏ አስፈሪ ድምፅ ወጣና አንበሳውን አባረረው፤ የዚህን ጊዜ አባ ቴዎድሮስ በሥዕሏ የተደረገውን ተአምር ሲመለከት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ለራሱ ሊያደርጋት ፈለገ፤ ‹‹ይህችን ተአምረኛ ሥዕል ወደ አገሬ እወስዳታለው ለማርታ አልሰጥም›› ብሎ በልቡ አሰበ ወደ ማርታ አገር ጸዴንያ መሄዱን ትቶ በሌላ መንገድ ለመሄድ ጉዞ ጀመረ፡፡
ልጆች! በሚገርም ሁኔታ ነፋስ ተነሣና የሚጓዝበትን መርከብ መንገዱን አቅጣጫውን አስቶ ወደ ጼዴንያ አገር ወሰደው፤ መሽቶም ስለነበር ወደ ማርታ ቤት ገብቶ አደረ፤ ማንነቱን ግን አልነገራትም፤ ሊነጋጋ ሲል ተነሣና ሊወጣ ሲል የመውጫው በር ጠፍቶበት ሲንከራተት ዋለ፤ ሲመሽ ገብቶ ተኛ አሁንም በሁለተኛው ቀን እንዲሁ አደረገ መሸበትና ገብቶ ተኛ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ሌሊት ተነሣና ማንም ሳያየው ሊወጣ ሲል በሩ ጠፋበት፤ ማርታ በየቀኑ ይህን የመነኩሴውን (አባ ቴዎድሮስን) ሁኔታ ትመለከት ነበር፤ ቀረብ ብላ ምን ሆነህ ነው? ሦስት ቀን ሙሉ ስትቅበዘበዝ ግራ ገብቶህ ከቦታ ቦታ ትመላለሳህ” ብላ ጠየቀችው፤ አባ ቴዎድሮስም ሥዕል እንዲገዛላት የላከችው ሰው እንደሆነ እና ሥዕሏን ገዝቶ ሲመጣ የተደረገውን ተአምራት ሁሉ ነገራትና ይቅርታ ጠይቆ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕል ሰጣት፡፡ የተጠቀለለበትን መጎናጸፊያ ሲፈታ ከሥዕሊቷ (ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል) ወዝ ሲንጠፈጠፍ (ደስ የሚል መዓዛ ሲወጣ) ተመለከቱ፡፡ ማርታም በጣም ደስ አላት፤ በጸሎት ቤት አስቀመጠጫት፡፡ (መጽሐፈ ሐፈ ሐ ስንክሳር መስረም ፲ ቀን የሚነበብ)
በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ከተደረጉ ተአምራት አንዱን ለአብነት ተመለከትን፤ ከዚህ ታሪክ በርካታ ትምህርት እናገኛለን፤ ለምሳሌ የእኛ ያልሆነውን ነገር መመኘት እንደማይገባ ከአባ ቴዎድሮስ እንማራለን፤ ምንም ቢያምረን ብንወደው የእኛ ያልሆነውን ነገር ለመውሰድ መመኘት አይገባም፤ ታማኞችና አደራን በአግባቡ የምንወጣ መሆን አለብን፡፡ ማርታ እመቤታችንን ከልቧ በመውደዷ እመቤታችን ድንቅ ነገር አደረገችላት፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው ደግሞ በቅዱስ ሚካኤል ሥዕል የተደረገውን ተአምር እንመልከት፤ አስተራኒቆስና አፎምያ የተባሉ ቅዱስ ሚካኤልን የሚወዱና በስሙ ዝክርን የሚዘክሩ ለችግረኞች (ለድሆች) የሚያባሉ የሚያጠጡ መልካም እና ደግ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ አስተራኒቆስ ለሚስቱ ለአፎምያ “ምን ላድርግልሽ?” በማለት በጠየቃት ጊዜ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ዐሥሎ እንዲያመጣላት ጠየቀችው፤ እርሱም ገዛላትና በጸሎት ቤቷ በክብር አስቀመጠችው፡፡
አስተራኒቆስም ታመመና ሞተ፤ አፎምያም በጾም በጸሎት ተወስና በእምነቷ ጸንታ፣ በመልካም ምግባር መኖር ጀመረች፡፡ በቅዱስ ሚካኤል ስምም ዝክር ትዘክርና ለችግረኞች ታበላ ነበር፤ በዚህ መልካም ምግባሯ ሰይጣን ቀናባትና ሊያሳስታት መጀመሪያ በሴት መነኮሳት ተመስሎ በመምጣት ጾም ጸሎት ማብዛት እንደሌለባት ነገራት፡፡ እርሷም ይህ ደግ ያልሆነ ምክር ነው፤ አልሰማችሁም አለቻቸው፡፡
በሌላ ቀን ደግሞ መልአክ መስሎ መጣና “እኔ ሚካኤል ነኝ” አላት፤ ቅድስት አፎምያም ስትመለከተው ምንም ነገር በእጁ አልያዘም፤ እርሷም “የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ በእጅህ የመስቀል ምልክት ለምን አልያዝክም” አለችው፤ “ቤቴ ያለው የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ጋር አይመሳሰልም” ብላ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ይዛ ስትመጣበት ያ ሰይጣን ከአጠገቧ ብን ብሎ ጠፋ፡፡ በሌላ ቀን ሊጎዳት ሲመጣ ቅዱስ ሚካኤል ደረሰና አዳናት፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ሰኔ ፲፪ ቀን የሚነበብ)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሕገ እግዚአብሔር እየጠበቅን መጽሐፍ ያዘዘንን እየፈጸምን በመኖር በቅዱሳን ቃል ኪዳን ታምነን ስንጸልይ እግዚአብሔር ቅዱሳንን በመላክ ከክፉ መከራ ይጠብቀናል፡፡ ቅድስት አፎምያ በቅዱስ ሚካኤል ቃል ኪዳን ስትታመን እንዳዳናት ከቅዱሳን መላእክት ሥዕላት ሥር ሆነን ስንማጸን በሥዕላቸው ድንቅ ተአምራት ይደረግልናል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕል የተደረገውን ተአምርም እንመልከት፤ ዑልያኖስ የተባለ ሰው በነገሠበት ዘመን ቅዱስ ባስሊዮስ ሊቀ ጳጳስ ነበረ፤ ይህ ንጉሥ የማይገባ ነገር ይሠራ ጀመር፤ ምእመናንን ሃይማኖታቸውን እንዲክዱ መከራ ሲያደርስባቸው ባገኘው ጊዜ መክሮ ከስሕተቱ ሊመልሰው ሲመጣ ቅዱስ ባስልዮስን አሠረውና ከምሄድበት ስለስ እገድልሃለው በማት ዝቶበት( አስፈራርቶት) ሄደ፡
በእሥር ቤት ውስጥም ቅዱስ መርቆሬዎስ በፈረስ ተቀምጦ በእጁ ጦር ይዞ የተሳለ ሥዕል ነበረ፤ ቅዱስ ባስልዮስ በሥዕሉ ፊት ሆኖ ሲጸልይ ሥዕሉ ከቦታው ለተወሰነ ጊዜ ተሠወረ (ታጣ)፡፡ ንጉሥ ዑልያኖስንም ገድሎት ትንሽ ቆይቶ ወደ ቦታው ተመለሰ፤ ቅዱስ ባስልዮስም ሥዕሉን ሲመለከት ጦሩ ላይ ደም ሲንጠባጠብ ተመለከተ፤ ከዚያም ‹‹ ዑልያኖስን ገደልከውን?›› አለው፤ የቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕልም ራሱን ዘንበል አደረገ፤ (አዎ እንደ ማለት ዘንበል ብሎ መለሰለት) ቅዱስ ባስልዮስም እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ኅዳር ፳፭ የሚነበብ)
ልጆች! በሥዕለ አድኅኖ ብዙ ተአምራት ተደርገዋል፤ አሁንም ይደረጋሉ ፤እኛ በእምነት ሆነን በቅዱሳን ሥዕላት ፊት ሆነን ስንጸልይ ቅዱሳን በሥዕላቸው ድንቅ ተአምራትን ያደርጋሉ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በሥዕለ አድኅኖ ብዙ ተአምራት ተደርገዋል፤ ወደፊትም እንደ እምነታችን ጽናትና መንፈሳዊ ሕይወታችን ብስለት በሥዕለ አድኅኖ ድንቅ ተአምራትን ልንመለከት እንችላለን፡፡ ለዛሬ ይቆየን፤ በሚቀጥለው ሥዕለ አድኅኖ (ቅዱሳት ስዕላትን) እንዴት አክብረን መያዝ እንዳለብን እንማራለን፡፡
ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ፤ ለወላጆቻችሁ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!
