ሥዕለ አድኅኖ

 ክፍል ሦስት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

ኀዳር ፴፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? እንኳን ለጾመ ነቢያት (የገና ጾም) አደረሳችሁ! ይህ ጾም የሚጾመው አባቶቻችንን ነቢያት እግዚአብሔር በሰጠን ተስፋ በገባልን ቃል ኪዳን መሠረት ከሰማያት ወርዶ እንዲያድነን “አቤቱ ውረድ፤ ተወለድ፤ አድነን” እያሉ የጾሙት ጾም ነው፤ እኛ ደግሞ ከሰማያት ወርዶ፣ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ አድኖናል እያልን ውለታውን እያስታወስን እንጾመዋለን፡፡ ከሰባቱ የዐዋጅ አጽዋማት አንዱ ስለሆነ እኛም እንደ አቅማችን ልንጾመው ይገባል! መልካም!

ትምህርታችሁንም በርትታችሁ ተማሩ! የመንፈቀ ዓመቱ ፈተናም እየተቃረበ ነው፤ በደንብ በማጥናት ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ አለባችሁ! በሰንበት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መማርን፣ማገልገልንም እንዳትረሱ።

ባለፈው ትምህርታችን ስለ ሥዕለ አድኅኖ በተማርነው ትምህርት ሥዕለ አድኅኖ እንዴት መሣል እንዳለበት በመጠኑ ተምረናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ሥዕለ አድኅኖ ሲሣል የምንጠቀማቸው ቀለማት (ከለር) ምን ዓይነት መሆን እንዳበቸውና ምክንያቱን የተወሰኑትን ለአብነት እንመለከታለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለቅዱሳት ሥዕላት የምንጠቀማቸውን የቀለማት ውክልና ከማየታችን በፊት ቀለም ምንድን ነው የሚለውን እንመልከት፤ ቀለም የሚለውን ሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የቃላትን ፍቺ (ምሥጢር) በተረጎሙበት መጽሐፋቸው ቀለም በቁሙ “ኅብር፣ ፈሳሽ፣ ዓይነት፣ መጣፊያ፣ ማቅለሚያ” ብለው አብራርተውታል፡፡ (ኪዳነ ወልድ መዝገበ ቃላት ገጽ ፯፻፺፫/793)

ቀለማት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሥዕለ አድኅኖ ሲሣሉ የሚያስተላልፉት መልእክትም አላቸው፤ የፈጣሬ ዓለማት የቅድስት ሥላሴ፣ የእመቤታችን ቅድስት ደንግል ማርያምን፣ ሥዕል ሲሣል የሚቀባው ቀለም ዓይነት የራሱ የሆነ ትርጒምና የሚያስተላልፈው ነገር አለው፤ የቅዱሳን መላእክትን፣ የቅዱሳን አበውን፣ የቅዱሳት እናቶችን ሥዕልም በሚሳልበት ጊዜ የተጋድሏቸውን ጽናት፣ የክብራቸውን ዓይነት፣ የመጠሪያ ስያሜአቸውን ለመለያነትም ያገለግላል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የቅዱሳን ሥዕለ አድኅኖ ሲሣል በሥዕሉ ባለቤት በራሱ           ዙሪያ በክብ ቅርጽ ጸዳለ ብርሃን (አክሊለ ብርሃን) ተደርጎ ይሣላል፤ በዚህም ለመግለጽ የተፈለገው ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን የቅድስና ማዕረግ እንደተሰጣቸው ለመግለጽ ነው፡፡

 ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ክቡ ቅርጽ በቅድስት ሥላሴና በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥዕለ አድኅኖ ላይ የሚደረገው ጸዳለ ብርሃን የእግዚአብሔር ቅድስና የባሕርይው መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ለቅዱሳን ሲደረግ ደግሞ አምላካችን የባሕርይ ቅድስናውን መልካም በመሥራታቸው በጸጋ (በስጦታ) ለቅዱሳን ቅድስናን እንደሰጣቸው ለመግለጽ የቅዱሳት ሥዕለ አድኅኖ ሲሣል በራሳቸው ዙሪያ በብርሃን ክብ ቅርጽ ይደረግላቸዋል፡፡

 ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት አብዛኛውን ጊዜ የምንጠቀማቸው ቀለማት ነጭ፣ ሰማያዊ፣  ቢጫ፣ አረንጓዴና ቀይ ሲሆኑ ቀለማቱ ራሱን የቻለ ምሥጢር ወይም ትርጒም አላቸው፡፡

 ነጭ፡- የድል አድራጊነት፣ የንጽሕና እና የፍጹምነት ምሳሌ ነው፡፡ ቅዱሳን ዓለምንና ምኞቱን ድል ያደረጉ ልበ ንጹሐን በመሆናቸው ነጭ ልብስ ለብሰው ይሣላሉ፡፡ እንዲሁም ደግሞ መለኮታዊ ክብርንም ያሳያል፡፡ ለምሳሌ በደብረ ታቦርና በትንሣኤ ሥዕሎች ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነጭ ልብስ ለብሶ ይሣላል፡፡ (ኦርቶዶክሳዊ ቅዱሳት ሥዕላት ገጽ ፸፬)

ሰማያዊ፡- ሥዕለ አድኅኖ ሲሣሉ ሰማያዊ ቀለምን መቀባቱ በመልካም ሥራው ሰማያዊውን ሀብት (መንግሥተ ሰማያትን) ገንዘብ ለማድረግ (ለመውረስ) አባቶቻችን ቅዱሳን በፈቃደ ነፍስ ለመመራት መልካም ሥራን ለመሥራታቸው፣ ኃጢአትን መጥላታቸውን ለሰዎች መልካምን ማድረጋቸውን ለማመልከት እንዲሁም በመንፈስ ፍሬዎች በተባሉ በትዕግሥት፣ በትሕትና፣በፍቅር፣ በደስታ፣ በእምነት፣ በቸርነት (ገላ. ፭፥፳፪) ፈቃደ ሥጋን (ክፉ ምኞቶችን ሁሉ ድል ማድረጋቸውን ለማመልከት ለሥዕለ አድኅኖ ሲሣሉ ይህንን ቀለም እንጠቀመዋለን፡፡ሌላው ደግሞ ከቁጣ፣ ከቂም፣ ከበቀል ርቀው በትሕትናን ለመኖራቸው ምሳሌ ነው፡፡

 ቢጫ፡- ይህ ቀለም እውነተኛነትንና ብርሃንነትን ይገልጻል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ ‹‹እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ …›› (ማቴ.፭፥፲፬) በማለት እንዳስተማረው በመልካም ሥራቸው ለሌላው ብርሃን የሆኑትን ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ማዕረግ ላይ የደረሱትን ቅዱሳን እውነተኞችና የዓለም ብርሃን ናችሁ ስትል በራሳቸው የብርሃን አክሊል በቢጫ አድርጋ ትሥላለች፡፡

አረንጓዴ፡- ከልምላሜና ከጸዳል ጋር ስለሚያያዝ መንፈሳዊ ትርጒሙ መታደስን አዲስ ሕይወት፣ ደኅንነትና ተስፋን ያሳያል፡፡ በዚህ መሠረት በትንሣኤ በአዲስ ሕይወት እንደምንኖር ያመለክትልናል፤ አረንጓዴነትና ሕይወት ተወራራሽ ይሆናሉ፡፡

 ቀይ፡- ሥዕለ አድኅኖ  ሲሣሉ በቀይ ቀለም መሳላቸው ሰማዕትነትን ያሳያል፤ ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከወ መልእክቱ ‹‹…በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፣ ተፈተኑ በመጋዝ ተሰነጠቁ፣ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ …›› (ዕብ.፲፩፥፴፮) በማለት እንደገለጸው ስለ ሃይማኖታቸው መከራ የተቀበሉትን ሰማዕት የሆኑትን ቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ሥዕለ አድኅኗቸው በቀይ ቀለም ይሣላል፤ ቅዱሳን ነፍሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን ብለው መስጠታቸውን ለማመልከት ይህንን ቀለም እንጠቀመዋለን፤ እንዲሁም ቀይ ቀለም የነጻ አውጪዎችም ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ሥዕለ አድኅኖ ሲሣል ምንን ዓይነት ቀለማት እንደምንጠቀም በመጠኑ ለአብነት ተመልክተናል፤ በቀጣይ በሥዕለ አድኅኖ የተደረጉ ተአምራት እንማራለን፤

ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!