ሥነ ፍጥረት
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
መጋቢት ፴፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? ዐቢይ ጾምን እንዴት እያሳለፋችሁ ነው? ባለፈው ትምህርታችን ዕድሜው ከሰባት ዓመት በላይ የሆነ ማንኛውም ክርስቲያን ጾምን መጾም እንዳለበት በተማርነው መሠረት እንደ ዓቅማችሁ እየጾማችሁ እንደሆነ ተስፋችን እሙን ነው!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በሰንበት ቀን ከወላጆቻችሁ ጋር በመሄድ አስቀድሱ በሰንበት ትምህርት ቤት በመግባትም ተማሩ! በዘመናዊ ትምህርታችሁም በርቱ! ሁለተኛውን የመንፈቀ ዓመት ትምህርታችሁን ከጀመራችሁ ወራቶች ተቆጥረዋል፤ ምን ያህል እውቀትን አገኛችሁ? ትናንት ከነበራችሁ ላይ የተለየ ነገር ምን ጨመራችሁ? ይህን ማስተዋል ይገባል፡፡ መልካም! አሁን ለዛሬ ወዳዘጋጀንላችሁ ትምህርት እናምራ፡፡ ባለፈው “የእግዚአብሔር ባሕርያት” በሚል ርእስ ተምረን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ እግዚአብሔር ስለፈጠራቸው ፍጥረታት እንማራለን!
ለዚህ ዓለም ፈጣሪ አስገኚ አለው፤ እርሱም እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር መኖሩን ከሚያስረዱን አንዱ ደግሞ ሥነ ፍጥረት ነው፡፡ ታዲያ የዚህ ዓለም ፈጣሪ እግዚአብሔር ምን ምን ፈጠረ? እግዚአብሔር የዚህ ዓለም ፈጣሪ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ጻድቁ ኢዮብ እንዲህ ሲል መስክሯል፤ ‹‹ አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ ያስተምሩህማል፤ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ ይነግሩህማል፤ ወይንም ለምድር ተናገር እረስዋም ታስተምርሃለች…፡፡›› (ኢዮ.፲፪፥፯) እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪ መሆኑን እንስሳትም እንኳን ምስክር ይሆኑናል፡፡
እግዚአብሔር ፍጥረታትን በዕለተ እሑድ መፍጠር ጀመረና እስከ ዕለተ ዓርብ ድረስ ፳፪ ( ሃያ ሁለት) ሥነ ፍጥረታትን ፈጠረ፤ ልጆች! ሃያ ሁለት መባሉ ብዙውን አንድ ላይ ስለተቆጠረ ነው፤ ለምሳሌ ቅዱሳን መላእክት በጣም ብዙ ናቸው፤ እነዚህን ሁሉ አንድ ብለን ነው እንቆጥራቸዋለን። በዓለማችን ላይ ብዙ ዓይነት ዕፀዋት አሉ፤ ታዲያ እነዚህንም ስንቆጥራቸው ሁሉንም አንድ ብለን “ዕፀዋት” በማለት ነው፡፡
በዕለተ እሑድ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ስምንት ፍጥረታትን ፈጥሯል፤ እነርሱም እሳት፣ነ ፋስ፣ ውኃ ፣ መሬት ከዚያም አምስተኛ ጨለማን ፈጠረ፤ በመቀጠልም ብርሃንን ፈጠረ፤ ቀጥሎም ሰባቱን ሰማያትን ፈጠራቸው፡፡ እነዚህም ጽርሐ አርያም፣ መንበረ መንግሥት፣ ሰማይ ውዱድ፣ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፣ ኢዮር ፣ራማ ፣ኤረር ይባላሉ፤ እነዚህ ሰማያት ሲቆጠሩ አንድ ተብሎ ነው፡፡ ሰማያትን ከፈጠረ በኋላ ብዙ የሆኑ ቅዱሳን መላእክትን ፈጠራቸውና በሦስቱ ሰማያት በኢዮር፣ በራማ፣ በኤረር ከተሞች አኖራቸው፤ በመጨረሻም በዕለተ እሑድ “ብርሃን ይሁን” አለና ብርሃንን ፈጠረ፤ እንግዲህ ይህ ሁሉ የሆነው በመጀመሪያው ቀን በዕለተ እሑድ ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” እያሉ ሲያመሰገኑት ይኖራሉ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በዕለተ ሰኞ ደግሞ አሁን ወደ ላይ ቀና ስንል የምንመለከተውን ፀሐይ ፣ጨረቃ፣ ክዋክብት የሚመላለሱበትን ሰማይን ( ሥዕለ ማይ የውኃ ሥዕል ማለት ነው) ፈጠረ፡፡ በነጋታው ማክሰኞ ደግሞ እግዚአብሔር አትክልትን (ድንች፣ጎመን፣ቲማቲም፣ካሮት)፣ ዕፀዋትን (ትላልቅ ዛፎች) አዝርዕት ( ስንዴ ፣በቆሎ፣ ጤፍ፣ ገብስ…) ፈጠረ ፤ እነዚህ ዓይነታቸው ብዙ ቢሆንም ብዙውን አንድ እያደረግን ስንቆጥራቸው ሦስት ይሆናሉ፤ እንግዲህ በአጠቃላይ በሦስት ቀን ውስጥ ዐሥራ ሁለት ፍጥረታት ተፈጠሩ፡፡ ከዚያም በዕለተ ረዕቡ ፀሐይ ፣ጨረቃና ክዋክብትን ፈጠረ፤ ፀሐይ ጠዋት ትወጣና ማታ ላይ ትጠልቃለች፤ ጨረቃና ክዋክብት ደግሞ በማታ ይወጣሉ፤ በሌሊት ሲያበሩ ይቆዩና እንደገና ቀን በፀሐይ ይተካሉ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አምላካችን እግዚአብሔር በቀጣዩ ቀን በዕለተ ሐሙስ ከውኃ (ከባሕር) የተገኙ ሦስት ፍጥረታትን ፈጠረ፤ እነዚህም በእግራቸው የሚሄዱ፣ በደረታቸው የሚሳቡ፣ በክንፋቸው የሚበሩ ናቸው፡፡
ከዚያም በነጋታው በስድስተኛው ቀን ዓርብ ልክ እንደ ሐሙስ ያሉ ሆነው ግን ከምድር የተፈጠሩ በደረት የሚሳቡ፣ በእግር የሚሄዱ፣ በክንፍ የሚበሩ ፍጥረታትን ፈጠረ።
በመጨረሻም ሁሉን ፍጥረት ከፈጠረ በኋላ ሴትና ወንድ አድርጎ ሰውን ፈጠረ፤ አባታችን አዳምን በዕለተ ዓርብ ሃያ ሁለተኛ ፍጥረት አድርጎ ፈጠረው፡፡ አዳምን ከፍጥረት ሁሉ እግዚአብሔር አክብሮ ፈጥሮታል፤ ከዚያም እናታችን ሔዋንን በአዳን ላይ እንቅልፍት ካመጣበት በኋላ ከጎኑ አጥንትን ወስዶ አስገኛት፡፡ አይደንቅም ልጆች! በቀደሙት ትምህርታችን ስለ ሃይማኖት፣ ከዚያም ስለ ዓለም ፈጣሪ እግዚአብሔር ባሕርያት ተማርን፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር ምን ፈጠረ የሚለውን ደግሞ አሁን ተማርን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የሥነ ፍጥረት ትምህርት ሰፊና ጥልቅ ነው፤ ለእናንተ ግን በመጠኑ ነገርናችሁ፤ ወደፊት ደግሞ በጥልቀት በስፋት ትማሩታላችሁ፡፡ ቸሩ ፈጣሪያችን ለእኛ ለሰው ልጆች የሚያስፈልገንን ሁሉ አሟልቶ በመጨረሻ የእኛን አባትና እናት ደግሞ( አዳምና ሔዋንን) ፈጠረ ፡፡ ለእኛ ያለው ፍቅር ልዩ ነው፤ ውለታውን ሳንረሳ ትእዛዙን በመጠበቅ እኛ ደግሞ ለእርሱ ያለንን ፍቅር እንግለጽ፡፡ ወላጆቻችን ለእኛ ብዙ ነገር እያደረጉልን በትምህርታችን ጎበዝ ስንሆን፣ በሥነ ምግባር ስንታነፅ ደስ እንደሚላቸው እኛም ፈጣሪ እግዚአብሔር ያዘዘንን ትእዛዝ በመፈጸም ለእርሱ ያለንን ፍቅር እንግለጥ ፡፡ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቀጣይ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ እንማራለን ! ቸር ይግጠመን !!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!