ሥርዓተ ጸሎት
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ጥቅምት ፲፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? የአዲሱ ዓመት የትምህርት ዘመን ከተጀመረ ሁለተኛውን ወር እያጋመስን ነው አይደል? ለመሆኑ ከተማርነው ትምህርት ምን ያህል እውቀት አገኘን? በትምህርታችሁ እየበርታችሁ ነውን? ትናንት ከነበራችሁ ላይ ምን አዲስ ነገር ጨመራችሁ? ይህን ሁሉ ለራሳችሁ መጠየቅና መበርታት አለባችሁ! ተጨማሪ ዕውቀትንና ጥበብን ልትቀስሙ ያስፈልጋል፡፡ ልጆች! ቤተ ክርስቲያን በመሄድም መንፈሳዊውን ትምህርት በመማር በሥነ ምግባር ልትታነጹ ያስፈልጋል፤ በዕለተ ሰንበት በመሄድ ማስቀደስ እንዲሁም መንፈሳዊ ትምህርት መማር አለባችሁ፤ መልካም !!!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ባለፈው ጊዜ ስለ አጽዋማት መማራችን ይታወሳል! አሁን ደግሞ ስለ ሥርዓተ ጸሎት እንማማራለን፤ ጸሎት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገርባት ነው! ጸሎት ሰው ስለተደረገለት ነገር የሚያመሰግንበት፣ ወደ ፊት ስለሚደረግለት ነገር ደግሞ ከእግዚአብሔር የሚለምንበት ነው፤ ሌላው ደግሞ ልጆች! ለጸሎት ስንቆም (ስንጸልይ) “የዚህ ዓለም ፈጣሪ አለ” እያልን የምንመሰክርበትም ነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በምንጸልየው ጸሎት ዓለምን ፈጥሮ ለሚገዛ፣ ፍጥረታቱን ለሚመግብ እኛን ከክፉ ለሚጠብቅ፣ የሚያስፈልገንን ሁሉ ለሚሰጠን አምላካችን ምስጋና የምናቀርብበት ነው፤ የእግዚአብሔርን ሥራ የምናደንቅበትም ነው፤ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹…አድርገህልኛልና ለዘለዓለም አመሰግንሃለው..›› በማለት እንደገለጸው እግዚአብሔር በሕይወታችን ስለሚያደርግልን ነገር ሁሉ ምስጋና የምናቀርበው በጸሎት ነው፤ (መዝ.፶፪፥፱) ሌላው ደግሞ ከክፉ እንዲጠብቀን ሁል ጊዜ በጸሎት ልንማጸን ያስፈልጋል፤ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹…በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር ጸልዩ..›› በማለት እንደመከረን ጠላታችን ዲያቢሎስ የሚያመጣብንን ፈተና በድል የምንወጣው ስንጸልይ ነው፡፡ (ኤፌ.፮፥፲፱)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጸሎትን መጸለይ እንዳለብን ያዘዘን (ያስተማረን) ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ጌታችን የጸሎትን ሥርዓት ያስተማረን ደግሞ በትምህርት ብቻ አይደለም፤ እርሱም ይጸልይ ነበር፤ ቅዱሳን ሐዋርያትንም እንዲጸልዩ ‹‹አባታችን ሆይ›› የሚለውን ጸሎት አስተምሯቸዋል፤ ‹‹…እናንተስ እንዲህ ጸልዩ…›› (ማቴ. ፮፥፱) እንግዲህ ልጆች! ጸሎት አስፈላጊ ነውና ልንጸልይ ያስፈልጋል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ጸሎት በሦስት ይከፈላል፤ የግል ጸሎት፣ የማኅበር ጸሎት፣ የቤተ ሰብ ጸሎት በመባል ይታወቃል፤ እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚጸልየው ጸሎት የግል ጸሎት ሲባል በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚጸለየው የሚደርሰው ምስጋና፣ ሰዓታቱ ጸሎት፣ የማኅሌቱ፣ የጸሎተ ቅዳሴው፣ ምህላው ጸሎት የኅብረት ጸሎት ይባላል፤ ሌላው ደግሞ በቤተ ሰብ ውስጥ የሚደረገው ጸሎት ደግሞ የቤተ ሰብ ጸሎት ይባላል፡፡ ልጆች! እንግዲህ ክርስቲያን የሆንን ሁሉ በግል ሕይወታችን፣ በቤተ ሰብ እና በማኅበር ጸሎት ልንሳተፍ ያስፈልጋል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የጸሎት አደራረግ የራሱ ሥራዓት አለው፤ ውጫዊ እና ውስጣዊ ዝግጅት ያስፈልጉታል፤ ጸሎት ከማድረጋችን በፊት ንጽሕናችንን በመጠበቅ ነጠላችንን መስቀልያ፣ መልበስ፣ መብራት (ሻማ፣ጧፍ) ማብራት፣ በቅዱሳት ሥዕላት ፊት ቀጥ ብሎ በመቆም መዘጋጀት አለብን፤ እነዚህን በዋናነት ገለጽን እንጂ ሌሎችም ዝግጅቶች ያስፈልጋሉ፡፡
ውስጣዊ ዝግጅት የሚባለው ደግሞ ስንጸልይ በፍቅር መሆን አለበት፤ የምንለምነው እንደሚፈጸምልን ጽኑ እምነት ሊኖረንም ያስፍልጋል፤ በውጣችን ደግሞ ቂም በቀል መያዝ የለብንም፤ ምክንያቱም ልጆች ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርት ‹‹ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ኃጢአታችሁን ይቅር ይላችኋልና›› በማለት እንዳስተማረን እኛ ‹‹ይቅር በለን›› ብለን ስንጸልይና ይቅርታን ስንለምን አስቀድመን ይቅርታ ማድረግ አለብን፡፡ (ማቴ.፮፥፲፬)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በጸሎት ጊዜ ያለመታከት (ያለመሰልቸት) እና ባለመቸኮል መጸለይ አለብን፤ እንግዲህ ሰፊ ከሆነው የጸሎት ትምህርት ለግንዛቤ በማለት ጥቂቱን ብቻ ነገርናችሁ፤ ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ ልብ ማለት ያለብን ነገር በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የጸሎት ጊዜያትም እንዳሉ ነው፤ በምን በምን ሰዓት ለጸሎት መቆም እንዳለብን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንማራለን፤ በቀጣይ ጊዜ እነዚህን የጸሎት ጊዜያትና ለምን እንደተወሰኑ እንመለከታለን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አባቶቻን በትምህርታቸው ‹‹ጸሎት የሕይወታችን አጥር ነው›› ይላሉ፤ የቤት አጥር ቤት በሌባ ከመዘረፍ እንደሚከልል ክርስቲያኖችም ደግሞ በሕይወታችን ጠላታችን ዲያብሎስ የሚያመጣውን ፈተናና መከራ የምንከላከልበት አጥር ነው፤ አባቶቻችን በጸሎት ጠላትን ድል አድርገዋል፤ ስለዚህ ጠዋት ስንነሣ ምንም ተግባር ከማድረጋችን በፊት መጸለይ አለብን፤ ውለን ወደ ቤት ስንገባ መጸለይ አለብን፤ ምግብ አቅርበን ከመመገባችን በፊት እንዲባረክልን መጸለይ አለብን፤ የሰጠንን አምላክ በጸሎት ማመስገን ያስፈልጋል፤ እንዲሁም ደግሞ ተመግበን ስንጨርስ (ስብሐት በማለት) ተመስገን ማለት አለብን፤ ማታም ከመተኛታችን በፊት መጸለይ ያስፈልጋል፤ ሌላው ከምንም በላይ በአሁን ጊዜ አገራችን ሰላም እንዲሆን፣ ፍቅርን እንዲሰጠን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቅ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አንዱ ከሆኑት ስለ ጸሎት ጥቂት ተገርናችሁ፤ እኛም እንደ አቅማችን ልንጸልይ ያስፈልጋል፤ ለዛሬ በዚህ አበቃን፤ በቀጣይ ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ስለ ጸሎት ጊዜያት እንማማራለን፤ አምላካችን የምንጸልየውን ጸሎት በጎ ምላሽ ከእርሱ የምናገኘኝበት ያድርግልን፤ በቸርነቱ ይጠብቀን!
ይቆየን !!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!