ሥርዓተ አምልኮ

ክፍል ዐራት
የካቲት ፫፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ፍጥረት ሁሉ እንዲያመልከውና እንዲመሰግነው ነው፤ በአርአያውና በአምሳሉ የተፈጠርን ሰዎች ብቻም ሳይሆን በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀሱ እንስሳት ሳይቀር ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፡፡ በተለይም በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን ሰዎች የምናመልክበት የቅድስና ሕይወት ሰጥኖናል፡፡ ሕጉን ጠብቀን በሥርዓቱ ለምንኖር ለእኛ እርሱ ምሕረቱ የበዛ በመሆኑ በሕይወታችን ውስጥ ሊኖር ይወዳል፤ በቤቱም ስንገኝ ደስ ይሰኛል፡፡ እርሱን በዓይን ለማየት ባይቻለንም መኖሩን የምናውቀበትና የምናመሰግንበት፣ ለእርሱም የአምልኮት ስግደት የምናቀርብበትና የምናዜምበት በአጠቃላይ የምናመልክበት መንገድ ፈጥሮልናል፡፡ ለዚህም የከበረ ተግባር መፈጸሚያ ባርኮና ቀድሶ ንዋያተ ቅድሳትን ሰጥቶናል፡፡

ንዋያተ ቅድሳት

የቤተ ክርስቲያናችን ታላቁ ሊቅ ኪዳኔ ወልድ ክፍሌ የቃሉን ትርጉም በመጽሐፋቸው እንዲህ ብለው አስቀምጠውታል፤ “ንዋየ ማለት “ገንዘብ፣ ጥሪት፣ ቅርስ፣ ወርቅ፣ ብር፣ ከብት” ነው፡፡ (መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ ፮፻፴፪) ቅዱሳት ማለት ደግሞ “ቅድስና፣ ክብር፣ ንጽሕና፣ ጸጋ” ነው፡፡ (ገጽ ፯፻፹፬)
ንዋያተ ቅዱሳት የቤተ ክርስቲያን መገልገያዎች ናቸው፤ አገልግሎታቸውም እንደ ዓይነታቸውና እንደ ስያሜያቸው ይለያያል፡፡ ስለዚህም በቅደም ተከተል እንመለከታቸዋል፡፡

፩. ታቦት፡- የልዑል እግዚአብሔር ማደሪያ ነው፡፡ በኦሪት ዘፀአት ተመዝግቦ እንደምናገኘው አምላካችን እግዚአብሔር ነቢዩ ሙሴን ታቦቱን ከግራር፣ ከእንጨትና ከወርቅ እንዲሠራ ባዘዘው መሠረት ሠርቶታል፡፡ (ዘፀ.፳፭፥፩-፳፪፣፵፣፳) ርዝመቱንና ቁመቱንና መጥኖ እንደሠራው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል፡፡

ጽላት “ሰሌዳ ወይም መጸለያ” ማለት ነው፤ የመጀመሪያዋ ጽላት በግብር አምላካዊ የተገኘች ሁለት ክፍሎች ያሏትና ዐሥሩ ትእዛዛት የተጻፈባት እንዲሁም ነቢዩ ሙሴ በደብረ ሲና ከአምላካችን የተቀበላት በኋላም እስራኤል ለጣዖት ሲሰግዱ አይቶ ቢደነግጥ ከእጁ ወድቃ የተሰበረችው የዕንቁ ጽላት ናት፡፡ (ዘፀ.፴፣፲፭-፳)
ሁለተኛዋ ጽላት ደግሞ ነቢዩ ሙሴ በፊተኛዋ አምሳል መሠረት በግብር አምላካዊ ዐሥሩ ትእዛዛት የተጻፈባት በቤተ መቅደስ በታቦቱ ላይ ሆና ብዙ ተአምር ያደረገች ናት፡፡ (ዘፀ. ፴፬፥፩-፳፰) “ታቦተ ጽዮን” ብለን የምንጠራት ዐሥርቱ ቃላት የተጻፈባት ጽላትና በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በአክሱም ከተማ፣ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በክብር ተቀምጣ ትገኛለች፡፡ በእርግጥ ከተቀመጠችበት ቤተ መቅደስ ስለማትወጣ ማንም መግባትም ሆነ ታቦቱን ማየት አይችልም፡፡ ሆኖም ግን ታቦቷ ወደ ሀገራችን በገባችበት ዕለት በኅዳር ፳፩ ምእመናን ከየክፍለ ሀገራቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመምጣት ለታቦተ ክብሩ ይሰግዳሉ፡፡ አምላካቸውንም ያመሰግናሉ፡፡

ይህ ብቻም አይደልም፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታቦተ ጽዮንን ምሳሌ በማድረግ በክፍለ ሀገራቱ ለሚገኙ ምእመናን አምልኮተ እግዚአብሔርን ይፈጽሙ ዘንድ ታቦታትን ቀርጻ በክብር ቤተ መቅደስ ውስጥ ታስቀምጣለች፡፡ በእርግጥ የሚሠሩት በወርቅ የተሠሩ ባይሆኑና መጠናቸውና ስፋታቸውም ባይተካከልም በአምልካችን እግዚአብሔር፣ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ በመላእክት፣ በቅዱሳን፣ በሰማዕታት ዓመታዊ ክብረ በዓላት ላይ ይከበራሉ፤ ይሰገድላቸዋል፤ ይዘመርላቸዋልም፡፡

፪. መንበር፡– የታቦት ማስቀመጫ መንበር ነው፤ የሚገኘውም በቤተ መቅደስ በክብር ታቡቱን ይዞ ነው፡፡ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከብረት ወይም ከእንጨት ይሠራል፡፡ መንበሩን ከማስቀመጥ በተጨማሪም ጸሎት ይጸለይበታል፤ መሠዋዕት ይሠዋበታል፤ በመንበሩ ላይ በመደበኛነት የሚቀመጡ ንዋያተ ቅድሳት ታቦት /ጽላትና/ ሥዕለ ማርያም፣ ምስለ ፍቁር ወልዳ ሲሆኑ በቅዳሴ ጊዜ ሥጋውን ደሙን ለመፈተት የምንገለገልባቸው ጻሕል፣ ጽዋዕ፣ ማኀፈዳት፣ ዕረፈ መስቀል፣ መስቀል፣ ዕጣን ይቀመጡበታል፡፡

ከቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ቀሳውስቱ ውጪ መንበሩን የሚዳስስና የሚገለገልበት የለም፡፡ ዲያቆናት ግን ከበውት መቆም ይችላሉ፡፡ መንበር የታቦት፣ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ የመንበረ ጸባዖት፣ ልዑካን የሠራዊተ መላእክት ምሳሌ ነው፡፡

፫. አትሮንስ፡- ቀሳውስትም የሚጸልይበቱና መጽሐፈ ቅዳሴ የሚያስቀምጡበት ነው፡፡ አትሮንስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን፣ መጽሐፍ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መጽሐፍ ምሳሌ ነው፡፡

፬. ቅዱሳት ሥዕላት
ቅዱሳት ሥዕላት የአንድን ቅዱስ ምስል የሚገልጹ፣ ገድላቸውና ተአምራቸውን የሚገልጹ በመሆናቸው ይሰገድላቸዋል፤ ይህም የጸጋ ስግደት ነው፡፡ ሆኖም ግን ለእግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ ሥዕል የሚደረግ ስግድት የአምልኮት ስግደት ነው፡፡ ስለዚህም በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሌሎች ቅዱሳት ስፍራ የአምላካችን ሥዕላት ፊት ቆመን ለእርሱ በመስገድና በፍጹም ትሕትና መማጸን፣ ማመስገንና ማምለክ ተገቢ ነው፡፡

፭. አልባሰ ቅዳሴ፡- ካህናት ሥጋ ወደሙን በሚፈቱቱ ጊዜ የሚለብሱት ነጭና የአገልግሎት ልብስ በመሆኑ ከንዋያተ ቅድሳት መካከል ይመደባል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ነቢዩ ሙሴን ባዘዘው መሠረት አሮን ይለብሰው የነበረው ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ የተሠራና ዐሥራ ሁለት የወርቅ ሻኩራዎች ያሉት ልብስ ነው፡፡ (ዘፀ.፴፱፥፩-፳፭) እርሱም አልባሰ ቅዳሴ ለብሶ ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ ከሻኩራዎች ድምፅ ይሰማ ስለነበር በድምፁም ምክንያት ሕዝቡ ከያዛቸው በሽታ ይፈወሱ ነበር፡፡ (ዘፀ.፳፰፥፴፭)

፮. አክሊል፡- በዘመነ ኦሪት ካህናት አክሊል ያደርጉ ነበር፤ ይህም ከጥሩ ወርቅ የተሠራና “ቅድስና ለእግዚአብሔር” የሚል ቃል የተጻፈበት ማዕተብ ያለው የተቀደሰ ነው፡፡ (ዘፀ. ፴፱፥፴) በሐዲስ ኪዳን ሥርዓትም በቅዳሴ ጊዜ ካህናቱ አክሊል ማድረጋቸው ይህን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን በአክሊሉ ላይ የሚቀረጸው መስቀል ነው፡፡ የክብር ምልክት ስለሆነም ለሥጋና ደሙ ክብርም አክሊል ይደፋሉ፡፡ (፩ኛቆሮ.፱፥፳፭)

፰. ዕጣን፡– በቅዳሴ ሰዓት እንዲሁም በሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ጊዜ የሚቀርብ መባዕ ነው፤ መዓዛው እጅግ ደስ የሚል ነው፤ ንጹሕና ነውር የሌለበትም ሊሆን ይገባል፡፡ (ዘፀ.፴፥፴፭) “ለእግዚአብሔር የተመረጠውን መልካም ዕጣን ከመቅደስ ውጪ ለግል መጠቀም አልተፈቀደም” እንዲል፡፡ (ዘፀ.፴፥፴፯-፴፰)

፱. ጽንሓሕ፡– የዕጣን ማጠኛ ማሻታቻ ጽንሓሕ ይባላል፡፡ የሚሠራውም ከብረት ወይም ከናስ ወይም የወርቅና የብር መልክ ካላቸው እንዲሁም እሳት በቀላሉ ከማይጐዳቸው ማዕድናት ነው፡፡
ይህም ቤተ ክርስቲያናችንና ካህናቱ በጸሎተ ኪዳን፣ በማኅሌተ ጽጌ እና በቅዳሴ ጊዜ በቤተ መቅደሱና በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመመላለስ ለዕጣን ለማጠኛ ይጠቀሙበታል፡፡ የኦሪት ጽንሓሕ -ሸምሸር ሸጠን ከሚባል ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸና በወርቅ የተለበጠ ያለው ነበር፡፡ (ዘሌ.፲፮፥፲፪፣ ዕብ.፱፥፬) በሐዲስ ኪዳን ግን ከንጹሕ ወርቅ ማዘጋጀት አይችልምና ከላይ በተገለጸው መሠረት ተሠርቶ ለአገልግሎት ይውላል፡፡

፲. መጻሕፍት፡- ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቅዱሳ ቃል የተጻፈባቸው የተቀደሱ መጻሕፍት ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓትም በርካታ ጥቅም አላቸው፡፡ ሆኖም ግን ለአምልኮት የምንጠቀምባቸው ጊዜ ማለት በጸሎተ ኪዳንና በቅዳሴ ጊዜ ወንጌል የሚነበብት መጽሐፍ ቅዱስና የምስባክ መዝሙር የሚገኝበት መጽሐፈ ግጻዌ ናቸው፡፡ መጽሐፈ ጸሎተ ዕጣን ተጠቃሽ ነው፡፡

፲፩. መስቀል፡-ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የክርስትናችን ማኅተም በመሆኑ በቤተ መቅደስም ሆነ በቅዱሳት ስፍራ ተምሳሌቱ የተገለጸ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በቅዳሴ ጊዜ ካህናቱ የእጅ መስቀል ዲያቆናት ደግሞ ባለመጾር መስቀል ይይዛሉ፡፡ ይህም ምሳሌነቱ ጌታችን በዕለተ ዓርብ መስቀሉን ተሸክሞ እየወደቀ አየተነሣ ቀራንዮ የመውጣቱ ነው፡፡

ስለዚህም በመስቀል ላይ ተሠውቶ ፍቅሩን ለገለጸልን ለጌታችን ውለታ ምስጋናና ክብር ይገባልና በፍጹም ትሕትናና ክብር እንሰግድለታለን፤ እናመሰግነዋለንም፡፡ በዘወትር ጸሎታችንም “ዓለምን ሁሉ ለማዳን ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት መስቀልም እሰግዳለሁ” በማለት እንሰግዳለን፡፡

፲፪. መሶበ ወርቅ፡- መሥዋዕት ማክበሪያ ነው፤ ዲያቆን በራሱ ተሸክሞ መሥዋዕቱን ከቤተልሄም ወደ መቅደሱ ያቀርብበታል፡፡ ይህም ተምሳሌቱ ከቤተልሔም ወደ መቅደስ መምጣቱና ጌታ ነቢያት በተናገሩለት ትንቢት መሠረት በቤተልሐም ተወልዶ በቀራኒዮ የመሠዋቱ ምሳሌ ነው፡፡

፲፫. ጻሕል፡- ይህ ጐድጐድ ያለ ወጭት ሲሆን ከሸክላ ወይም ከናስ ከብረት ወይም ከወርቅ ከብር የሚሠራ ነው፡፡ በኦሪት ዘመን ኅብስተ ገጽ ይቀርብበት ቢሆንም በሐዲስ ኪዳን ግን ከመንበሩ ላይ ሆኖ የጌታችን ሥጋ ይቀመጥበታል፤ ምሳሌነቱም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ነው፡፡

፲፬. ጽዋዕ፡– ኩባያ፣ ዋንጫ፣ የመጠጥ መሣሪያ፣ የሸክላ፣ ከእንጨት፣ ከቀርን፣ ከማዕድን የሚሠራ ነው፡፡ የደሙ ማቅረቢያ ሲሆን የጌታችን መቃብር መላእክት ከጌታችን ጐን የፈሰሰውን ደም ተቀብለው በዓለም ሁሉ የረጩበት የብርሃን ጽዋ ምሳሌም ነው፡፡

፲፭. ማኀፈድ፡– ከተመረጠ ጨርቅ የሚሠራ የሥጋውና የደሙ መሸፈኛ ሲሆን አምስት ማኅፈዳት አገልግሎት ይሰጥባቸዋል፤ አንድ ጻሕሉ ላይ ይነጠፋል፤ ሦስቱ ኀብስተ ቁርባኑ ይሸፈንባቸዋል፤ አንዱ የጽዋዕ መሸፈኛ ነው፡፡ የጌታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡

፲፮. ተቅዋም፤ መቅረዝ፡– የመብራት መስቀያ ወይም ማስቀመጫ ነው፤ ከኦሪት ዘመን ጀምሮ እንደነበረው ሥርዓት መቅረዝ የሚሠራው ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸ፣ በወርቅ የተለበጠ፣ እንደ ጽዋዕ እግርና ሰባት ቅርንጫፎች ያሉት ነው፤ አገልግሎቱም ተመሳሳይ ነው፡፡ በመካከለኛ የተቀዳው ዘይት በስድስቱ ሁሉ ተሞልቶ፣ መብራቱም ሙሉ ሌሊት ያበራ ነበር፡፡ (ዘፀ. ፳፭፥፴፩-፵፣፳፯፥፳፣ዕብ.፱፥፪)

ይቆየን!

ምንጭ፡ ቤዛ ብዙኃን መዝገብ ምሕረት የሰንበት ትምህርት ቤት