ሥልጠናው የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ
ታኅሣሥ 17 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ማኅበረ ቅዱሳን ከታኅሣሥ 6-11 ቀን 2005 ዓ.ም. ከ65 በላይ ለሚሆኑ የገዳማት አበመኔቶች፣ እመምኔቶችና ተወካዮች “የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማሳካት የገዳማት ድርሻ” በሚል መሪ ቃል የግማሽ ቀን ዐውደ ጥናትና በዩኒቨርስቲ ምሁራን፤ በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት መምሪያ እንዲሁም በተጋባዥ ምሁራን ለአምስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቀቀ፡፡
ሥልጠናው ያተኮረው፡-
-
ገዳማት ያላቸውን ልዩ ልዩ ሀብታት ምንድናቸው? እንዴትስ ጥቅም ላይ ይውላሉ?
-
የአካባቢ ጥበቃ /ከብዝሃ ሕይወት ጋር በተያያዘ/
-
የሥራ ፈጠራ ክህሎትና የገቢ ማስገኛ እቅድ ዝግጅት
-
የቅርስ አጠባበቅ፣ ገዳማት ከቅርስ ጉብኝት እንዴት ተጠቃሚ ማድረግ ይችላል?
-
የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ ለማሳካት የገዳማትና የመነኮሳት ድርሻ
-
የገዳማት አስተዳደር ለማጠናከር የሰው ኀይል አጠቃቀም
-
የመረጃ ልውውጥና የውሳኔ አሰጣጥ
-
የሀብት ቁጥጥርና አስተዳደር ምን መምሰል ይኖርበታል?
-
የፕሮጀክት ጥናትና የፕሮጀክት ትግበራ . . . ወዘተ በሚሉ ዋና ዋና ርዕሰ ጉደዮች ላይ በስፋት ሥልጠናው ተሰጥቷቸዋል፡፡
በሥልጠናው ላይ የቡድን ውይይት በማድረግ፣ ገዳማት ከገዳማት ተሞክሮና ልምድ ልውውጥ፣ እንዲሁም የእርስ በርስ የመተዋወቅ ሥራዎች ለመሥራት ተችሏል፡፡
በሥልጠናው ላይ ያገኙትን ግንዛቤ ለመገምገምም በቅዱሳት መካናት ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የተዘጋጀ ፈተና የተሰጣቸው ሲሆን በውጤታቸው መሠረት ብልጫ ላመጡ 3 መነኮሳት የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገድል ተሸልመዋል፡፡ ሥልጠናውንም ወስደው በማጠናቀቃቸው ሁሉም ሰልጣኞች ከብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት እጅ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡
በመዝጊያ መርሐ ግብሩ ላይ ሥልጠናውን የወሰዱት የገዳማት አበምኔቶች፤ እመምኔተችና ተወካዮች ሥልጠናው ከፍተኛ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው በመግለጽ የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በአቋም መግለጫቸውም፡-
-
ገዳማውያንና ገዳማውያት ገዳማት ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም እራሳቸውን ችለው ሌላውን እንዲረዱ፤
-
በገዳማት የሚገኙ ቅርሶችን በአግባቡ በመያዝና በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ እንዲችሉ፤
-
የቁሪት ገዳማት ወደ አንድነት ገዳማዊ ሥርዓት እንዲመጡ /እንዲገቡ/ የሚደረግበት መንገድ እንዲመቻች፤
-
ገዳማውያን እና መነኮሳት ለተልዕኮ ከገዳማቸው በሚወጡ ጊዜ ተልዕኮአቸውን ፈፅመው እስኪመለሱ ድረስ የሚቆዩበት ማረፊያ ቤት በወረዳ በዞን እና በአዲስ አበባ ላይ እንዲመቻች ቢደረግ፤
-
በየገዳማቱ የሚገኙ ነገር ግን ያልታተሙ የቅዱሳን አባቶች የገድል መጻሕፍት እንዲታተሙ ቢደረግ
-
በኢትዮጵያ ያሉ ገዳማት ወጥ በሆነ አንድ ሥርዓተ ገዳም እንዲተዳደሩ ቢሆን፤
-
ያለ በቂ ሥራ ወይም ምክንያት ከገዳም ወደ ገዳም በመዘዋወር እና ከተማ በመምጣት እና በመቀመጥ ስም የሚያጎድፉ መነኮሳት በሚመለከተው አካል ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ቢደረግ፤
-
ቅድሳት ስዕላትን እና መስቀል ይዘው በየመንገዱ በቤተ ክርስቲያን ስም መለመኑ እንዲቆም እንዲደረግ፤ ያለ አግባብ ለዚሁ ጉዳይ ፈቃድ የሚሰጡ አካላትም እንዲታቀቡ እንዲደረግ፤
-
በየገዳማቱ ያሉት የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲጠናከሩ እና ባልተቋቋሙባቸው ገዳማት የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲቋቋም ቢደረግ፤
-
የኢትዮጵያ ገዳማት በገዳማት መምሪያው አማካይነት ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ እንድንሰበሰብ እና እንድንወያይ ቢደረግ፤
-
የገዳማውያን ጉዳይ በገዳማውያን አባቶች እንዲታይ ቢደረግ፤
-
ገዳማት ከሚሠሩት የልማት ሥራ ለመንግሥት ከሚከፍሉት ግብር ነፃ የሚሆኑበት መንገድ ቢመቻች፤
-
በመጨረሻም ከመመሪያው ሥር ሆኖ ስለገዳማት መጠናከርና ለችግሮቻቸው መፈትሔ የሚሰጥ 12 አባላት ያሉት አንድ ዐቢይ ጉባኤ /ኮሚቴ/ የመረጥን ስለሆነ እንዲፀድቅልን በማለት በአንድ ድምፅ ተስማምተን አቋም ይዘናል፡፡ በማለት የአቋም መግለጫቸውን አሰምተዋል፡፡
በማቅኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር ዲ/ን አእምሮ ይሔይስን የሥልጠናውን ውጤት በማስመልከት ጠይቀናቸው ሲመልሱም “ሥልጠናው ወደፊት በገዳማት ላይ ለምንሠራቸው ሥራዎች በር የከፈተ ነው፡፡ ከመነኮሳቱ ግብረ መልስ እንደተረዳነው ሥልጠናው ጥሩ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው አመላክቶናል፡፡ በተሻለ ሁኔታና ባቀድነው መሠረት ተከናውኗል፡፡ ወደፊትም አሠልጥነን የምንለቃቸው ሳይሆን ለመነሻ የሚሆን ከየገዳማቱ ምን ሊሠራላቸው እንደሚፈልጉ ከሰጡን መረጃ ተነሥተን ጥናቶችን በማጥናት እገዛ እናደርጋለን፤ ክትትላችንንም እንቀጥላለን፡፡” በማለት ገልጸዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡
ከመርሐ ግብሩ መጠናቀቅ በኋላ በሥልጠናው ስላገኙት እውቀትና የተሰማቸውን ስሜት እንዲገልጹልን ገዳማውያን አባቶችን የጠየቅናቸው ሲሆን የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
ስለ ሥልጠናው ከገደማውያን አባቶች አንደበት
- “ለገዳማት ልማት ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ እስከ ዛሬ እንደዚህ ዓይነት ሥልጠና አጋጥሞን አያውቅም፡፡ እስከ ዛሬ እንዴት ናችሁ? ብሎ የሚጠይቀን አልነበረም፡፡ አሁን የሚጎበኘን አካል ያገኘንበት ነው፡፡ ከሥልጠናው ጠቃሚ እውቀት አግኝተናል፡፡”
አባ ወ/ገብርኤል ንጋቱ ከሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ወገራ የቅድስት ማርያም ወአቡነ ምእመነ ድንግል አንድነት ገዳም አበምኔት
- “በዚህ ሥልጠና ለየት ያለ እውቀት አግኝቻለሁ ፤ ያላወቅሁትን እንዳውቅ የራሴንም ገዳም እንድመለከት አድርጎኛል፡፡ የተማርኩተን ለገዳማውያኑ በማሳወቅ የልማት ሥራዎችን እንዴት መተግበር እንደሚቻልና ገዳማችንን እንዴት መሳደግ እንደምንችል ተገንዝቤያለሁ፡፡”
አባ ኢሳያስ ወልደ ሰንበት የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅድስ ገዳም አበምኔት
- “ማኅበረ ቅዱሳን ፋና ወጊ የሆነና ገዳማትን ያሰባሰበ ጉባኤ በማዘጋጀቱ ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል፡፡ በገዳማችን እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች አሉ፡፡ በልማት ራሳችንን የቻልንበት ሁኔታ ላይ ነን፡፡ የገዳማት አንድነትና ትስስር የሚያጠናክርና መፃያትን ጊዜያት እንድንመለከት አስችሎናል፡፡”
አባ ተክለ ሥላሴ ገብረ ሕይወት የምሥራቅ ሸዋ ጮባ በዓታ ለማርያም ገዳም አበመኔት
- “ገዳሙ የአንድነት ገዳም ነው፡፡ ብዙ መጻሕፍትንና ቅርሶችን አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡ አምስት ጳጳሳትን የፈራ ገዳም ነው፡፡ በሥልጠናው መካፈሌ ለቅርሶቻችን አያያዝ ጠቃሚ መረጃ አግኝቼበታለሁ፡፡”
አባ ዘመንፈስ ቅዱስ ረዳ ከትግራይ አክሱም ጭህ ሥላሴ የአንድነት ገዳም አበምኔት
- “በገዳማችን 5 መነኮሳትና 6 ዲያቆናት ብቻ ነን ያለነው፡፡ ገዳሙ ጥንታዊ ነው፡፡ ያገኘነው እውቀት የሚያስደስት ነው፡፡ ውኃ አለን፡፡ በመስኖ ተጠቅመን የልማት ሥራዎችን ለመሥራት ያበረታታናል፡፡ እስካሁን በመስኖ ተጠቅመን ያከናወነው ነገር የለም፡፡”
መምህር ገብረ ማርያም ግደይ የትግራይ ተንቤን እንዳጨጌ ደብረ ፅጌ ኪዳነ ምሕረት ገዳም አበምኔት
- “ከሥልጠናው በየበኩላችን በየገዳማቱ በልማትም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወት ለውጥ የምናመጣበትና የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት በጠበቀ መልኩ እንዴት መለወጥ እንዳለብን አስገንዝቦኛል፡፡ ለገዳሙ መነኮሳት የተማርኩትን አስተምራለሁ፡፡ አደራ ተሸክሜአለሁና፡፡”
አባ ወልደ ሠማዕት አብርሃም ከዋልድባ አብረንታት ቤተ ሚናስ ማኅበር የገዳሙ አርድዕትና ተወካይ
- “እየወሰድን ያለው ሥልጠና ቤተ ክርስቲያናችን በፍቅርና በሰላም በልማት ላይ ትኩረት አድርጋ እንድትኖር የሚያመላክት ትጥቅ ነው የገበየሁት፡፡ ይህንን ተሞክሮ የቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት መምሪያ የኢትዮጵያ ገዳማትን ሁሉ አሰባስቦ ጠንካራ ሥራ መሥራት ይገባል፡፡”
አባ አብርሃም ወልደ ኢየሱስ የምድረ ከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም አበምኔት
- “ሥልጠናው ገዳማት እርስ በርሳችን እንድንተዋወቅ አድርጎናል፡፡ እንደ 120 ቤተሰቦች ነው የሆንነው፡፡ ገዳማት ከገዳማት መተዋወቅ የአንዱን ተሞክሮ ሌላው መስማትና መመልከት መቻሉ ለወደፊት የተሻለ ነገር እንድንሠራ ያደርገናል፡፡”
ቆሞስ ደሴ ዓለም የጎጃም ደጋ ዳሞት ደብረ ፀሐይ ዋልጣ ቅድስት ማርያም ገዳም አበምኔት
ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን መርሐ ግብር በሚያካሒድበት ወቅት ከገዳማውያን አባቶች በረከት ያገኙ ዘንድ በመስተንግዶ እንዲራዱ ለማኅበራትና ለምእመናን ባደረገው ጥሪ መሠረት መንፈሳዊ ማኅበራትና በጎ አድራጊ ምእመናን ምላሻቸውን በመስጠት የመነኮሳቱንና መነኮሳይያትን እግር በማጠብ፤ የምግብና መጠጥ ወጪ በመሸፈንና በማስተናገድ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ማኅበራትና ምዕመናን ላበረከቱት ድጋፍ ማኅበሩ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡