ሥላሴ በአብርሃም ቤት
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ሐምሌ ፯ ቀን እግዚአብሔር አምላክ በአብርሃም ቤት የገባበትና ሣራ ይስሐቅን እንደምትወልድ የተናገረበት ዕለት ነው፡፡ ይህ የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል በቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ታሪኩም በአጭሩ እንዲህ ነው፤
አባታችን አብርሃም ከተመሳቀለ ጐዳና ላይ ድንኳን ሠርቶ መንገደኞችን ዅሉ በእንግድነት እየተቀበለ ሲያስተናግድ ይኖር ነበር፡፡ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን ለተንኮል አያርፍምና ይህንን መልካም ግብሩን ለማሰናክል አሰበ፡፡ አስቦም አልቀረ፤ የተጐዳ ሰው መስሎ ከጐዳና ቆሞ አብርሃም እንግዳ መቀበል እንደ ተወ፤ እርሱ ሊበላ ሊጠጣ ከቤቱ ቢሔድ ራሱን ፈንክቶ፣ ደሙን አፍሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ልብሱን ገፎ እንደ መለሰው ወደ አብርሃም ቤት ለሚሔዱ ሰዎች ይናገር ጀመር፡፡ በዚህ የተነሣም እንግዳ ወደ አብርሃም ቤት አልመጣ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አብርሃምም ማዕደ እግዚአብሔርን ያለ ምስክር (ያለ እንግዳ) አልመገብም ብሎ ሦስት ቀን ሳይመገብ ጾሙን አደረ፡፡ በሦስተኛው ቀን ይህን ደግነቱን እግዚአብሔር ተመልክቶ በሦስት ሰዎች አምሳል አንድም በሥላሴው (በሦስትነቱ) ከአብርሃም ቤት ገብቷል (ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ ፬፥፴፪)፡፡
በኦሪት ዘፍጥረት ፲፰፥፩-፲፱ ተጽፎ እንደምናገኘው በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በሦስት ሰዎች አምሳል በመምሬ አድባር ዛፍ ተገልጦለታል፡፡ አብርሃምም ሦስት ሰዎች ቆመው ባየ ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ወደ እነርሱ ሮጠ፡፡ ወደ ምድርም ሰገደና ‹‹አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባርያህን አትለፈኝ?›› ብሎ ተማጸነ፡፡ በመቀጠል አብርሃም ‹‹ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፤ እግራችሁን ታጠቡ፤ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፡፡ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፤ ልባችሁንም ደግፉ፡፡ ከዚያም በኋላ ትሔዳላችሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ባርያችሁ መጥታችኋልና›› ሲላቸው እነርሱም ‹‹እንዳልህ አድርግ›› ብለውታል፡፡
የኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ እንደሚያስረዳው አብርሃም ሥላሴን ‹‹ጌቶቼ ከቤት ገብታችሁ ዕረፉ›› ሲላቸው ‹‹ደክሞናልና አዝለህ አስገባን›› አሉት፡፡ እርሱም እሺ ብሎ አንዱን አዝሎ ቢገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ (በአምላካዊ ጥበብ) ከቤቱ ገቡ፡፡ አብርሃምም ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ሔደና ‹‹ሦስት መሥፈሪያ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፤ ለውሺውም፤ እንጎቻም አድርጊ›› አላት፤ እርሷም እንዳዘዛት አደረገች፡፡ አብርሃምም ወይፈን አርዶ አወራርዶ አዘገጅቶላቸው ተመግበዋል፡፡ ወይፈኑም ተነሥቶ ‹‹ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ፤ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድ ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፤›› ብሎ እግዚአብሔርን አመስገኗል፡፡
ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› አለው፡፡ አብርሃምም ከድንኳኑ ውስጥ እንዳለች ነገረው፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች›› ብሎ ለአብርሃም አበሠረው፡፡ ሣራ ይህንን ቃል በሰማች ጊዜ ባለቤቷም አርጅቶ፤ እርሷም የሴቶች ግዳጅ ትቷት ነበርና ‹‹‹ሲያረጁ አምባር ይዋጁ› እንዲሉ ‹‹እስከ ዛሬ ድረስ ቆንጆ ነኝን? ጌታዬ አብርሃምስ ገና ጐረምሳ ነውን?›› ብላ በማሰቧና መውለዷን በመጠራጠሯ ሳቀች፡፡ እግዚአብሔርም ምሥጢሩን በአጽንዖት ለማስረዳትና አስረግጦ ለመንገር አብርሃምን ‹‹ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› አለው፡፡ ሣራም ስለፈራች ‹‹አልሳቅሁም›› አለች፡፡ እግዚአብሔርም መሳቋን እንዳወቀባት ከነገራት በኋላ በድጋሜ በዓመቱ ወደ አብርሃም ቤት እንደሚመጣና ሣራ ወንድ ልጅ (ይስሐቅን) እንደምትወልድ አብሥሯቸዋል፡፡
በዚህ ትምህርት ብዙ ምሥጢራት ይገኛሉ፤ ጥቂቶቹን በመጠኑ ለማስታወስ ያህል፦ ‹‹… ሦስት ሰዎች … ሊቀበላቸው … ወደ እነርሱ …›› የሚሉትና ሌሎችም በብዙ ቍጥር የተገለጹ ተመሳሳይ ሐረጋት የእግዚአብሔርን ሦስትነት፤ ‹‹… በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባሪያህን አትለፈኝ? …›› የሚለው ዐረፍተ ነገር ደግሞ አንድነቱን ያመለክታል፡፡ ሣራ ዳቦ ያዘጋጀችበት ሦስቱ መሥፈሪያ የሦስትነቱ፤ ዳቦው አንድ መኾኑ ደግሞ የአንድነቱ ምሳሌ ነው፡፡ ሥላሴ አብርሃም ያዘጋጀውን እንስሳ ተመገቡ ተብሎ መነገሩም በሰው አምሳል ስለ ተገለጡና ለአብርሃም የበሉ መስለው ስለ ታዩት ነው እንጂ ለሥላሴ መብል መጠጥ አይስማማቸውም (አይነገርላቸውም)፡፡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን ሥላሴ ምግብ በሉ (እግዚአብሔር ምግብ በላ) ማለት ቅቤ ከእሳት ገብቶ አልቀለጠም እንደ ማለት ነው፡፡ መብላት፣ መጠጣትን የመሰሉ የሥጋ ተግባራት የመለኮት ባሕርያት አይደሉምና፡፡ ከዚህ በተለየ ምሥጢር ሥላሴ ‹‹ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› ብለው ከጠየቁበት ኃይለ ቃል መካከል ‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› የሚለውን እመቤታችንን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት ‹‹ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል?›› (ሉቃ. ፩፥፴፯) ብላ በጠየቀችው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ደግሞ መናገሩ የእግዚአብሔር ቃል በዘመን ብዛት የማይለወጥ ሕያውና እውነተኛ መኾኑን ያጠይቃል፡፡
እግዚአብሔር አብርሃምን ‹‹ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል መጠየቁም ያለችበት ጠፍቶበት ሳይኾን የሚነግራት ታላቅ የምሥራች እንዳለ ለማጠየቅ ነው፡፡ ሰውን ያለበትን ጠይቆ፣ ጠርቶ፣ አቅርቦ አስደሳች ዜና መንገር የተለመደ ነውና፡፡ ይኸውም ‹‹አዳም ወዴት ነህ?›› ከሚለው ጥያቄ ጋር ተመሳሳይነት አለው (ዘፍ. ፫፥፱)፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አባታችን አዳምን ‹‹ወዴት ነህ?›› ሲል የጠየቀው ያለበትን ዐላውቅ ብሎ ሳይኾን ቃል በቃል ሊያነጋግረው፣ ‹‹ከልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚለውን የድኅነት ቃል ኪዳን ሊሰጠው ፈቅዶ ነበር፡፡ እንደ አዳም ዅሉ ለሣራም ለጊዜው ይስሐቅን እንደምትወልድ፤ ለፍጻሜው ደግሞ ከአብርሃም ዘር ከምትኾን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ሥጋ ለብሶ እንደሚገለጥና ዓለሙን እንደሚያድነው ለመንገር አብርሃምን ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል ጠይቆታል፡፡ ከዚያም የይስሐቅን መወለድ አብሥሯቸዋል፡፡ ይኸውም አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም እግዚአብሔር ከአብርሃም የልጅ ልጅ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ተወለደ (በአካለ ሥጋ ወደ ምድር እንደ መጣ)፤ በዚህ ጊዜም በሣራ የተመሰለች ወንጌል በይስሐቅ የሚመሰሉ ምእመናንን እንዳስገኘች ማለትም ሐዲስ ኪዳን ተመሥርታ ብዙ ክርስቲያኖችን እንዳፈራች የሚያመለክት ምሥጢር አለው፡፡
የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንደ ተረጐሙልን የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን ምሳሌ ነው፤ ‹‹ተናግዶቱ (ተአንግዶቱ) ለአብርሃም፤ ለአብርሃም የሃይማኖቱን (የእንግዳ ተቀባይነቱን) ዋጋ የምታሰጪው አንቺ ነሽ፤›› እንዳሉ አባ ሕርያቆስ፡፡ በአብርሃም ድንኳን አላፊ አግዳሚው ይመግብበት፣ ያርፍበት እንደ ነበረ ዅሉ በእመቤታችንም አማላጅነትም መንገደኞች ማረፍያ፤ እንግዶች መጠለያ፤ ስደተኞች ተስፋ ያገኛሉና፡፡ ከዅሉም በላይ የነፈስ የሥጋ መድኀኒት፤ የዘለዓለም ማረፍያ፤ እውነተኛ መብልና መጠጥ የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች እርሷ ናትና በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡ ቀትር በኾነ ጊዜ ማለትም በስድስት ሰዓት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ወደ አብርሃም ድንኳን እንደ ገቡ ዅሉ፣ አምስት ሺሕ አምስት መቶው ዓመት ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዓመት እግዚአብሔር አብ ለአጽንዖ፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፤ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ለመልበስ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አድረዋልና እመቤታችን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡ ‹‹በስድስተኛው ወር ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እመቤታችን ተላከ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሉቃ. ፩፥፳፮)፡፡ በዚህ ቃለ ወንጌል ‹‹ስድስተኛው ወር›› የሚለው ሐረግ አምስት ሺሕ አምስት መቶው ዘመን ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዘመን ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ለብሥራት መላኩን ያመለክታል፡፡
በአብርሃም ቤት (በድንኳኑ) ውስጥ ወይፈኑ ‹‹ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ›› ብሎ እንዳመሰገነ ዅሉ እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን በተወለደ ጊዜም ቅዱሳን መላእክትና የሰው ልጆች ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ፤ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይኹን፤ ሰላምም በምድር፤ ለሰውም በጎ ፈቃድ›› እያሉ እግዚአብሔርን በአንድነት አመስግነዋል (ሉቃ. ፪፥፲፬)፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም የይስሐቅን መወለድ እና በሥጋ ማርያም መገለጡን ከነገረው በኋላ ተመልሶ ሔዷል፡፡ ‹‹ሔዷል›› ስንልም ሥላሴ ከአብርሃም ቤት በሰው አምሳል ሲወጡ መታየታቸውን ለማመልከት እንጂ እግዚአብሔር መሔድ መምጣት የሚነገርለት ኾኖ አይደለም፡፡ እርሱ በዓለሙ ዅሉ ሰፍኖ የሚኖር አምላክ ነውና፡፡ ነገር ግን በልዩ ልዩ ምሳሌ እየተገለጠ ጸጋውን፣ በረከቱን ማሳደሩን ለመግለጽ መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ እየተባለ ይነገርለታል፡፡
ትምህርታችንን ለማጠቃለል ያህል ሐምሌ ፯ ቀን እግዚአብሔር በአብርሃም ቤት ተገኝቶ የይስሐቅን መወለድና የእግዚአብሔርን ሰው መኾን የተናገረበት ዕለት ከመኾኑ ሌላ የአብርሃምን ዘሩን እንደሚያበዛለትና አሕዛብ ዅሉ በእርሱ እንደሚከብሩ ማለትም ከአብርሃም ዘር በተገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ አሕዛብ እንደሚቀደሱ፤ ይህንን ምሥጢርም እግዚአብሔር ከወዳጁ ከአብርሃም እንደማይሠውር ቃል ኪዳን የገባበት ቀን ነው፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር በኀጢአታቸው ብዛት የተነሣ ሰዶምንና ገሞራን ያጠፋው፤ አብርሃምም በአማላጅነት በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ የተማጸነው በዚሁ ዕለት ነው፡፡
ቅዱሳን በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ዘወትር ስለ ሰው ልጅ ድኅነት እንደሚጸልዩ እና እንደሚያማልዱ፤ እንደ አብርሃም ልቡናቸው ቅን በኾነና በለጋሾች ማለትም ምጽዋትንና እንግዳ መቀበልን የዘወትር ተግባራቸው አድርገው በሚኖሩ ሰዎች ቤት እግዚአብሔር እንደሚገኝ፤ እግዚአብሔር በረድኤት ወደ ሰው ቤት ሲገባም የተዘጋ ማኅፀን እንደሚከፍትና ቤቱን በበረከት እንደሚሞላ፤ እንደዚሁም የተሠወረ ምሥጢር እንደሚገልጽ ከዚህ ታሪክ እንረዳለን፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም እግዚአብሔር አምላክ በአንድነቱም በሦስትነቱም እየታየ አምላክነቱን ለዘመናት እንደሚገልጥና የቸርነቱን ሥራ እንደሚሠራም ከታሪኩ እንማራለን፡፡
በአጠቃላይ ይህ የእግዚአብሔር በአብርሃም ቤት የመገለጥ ትምህርት በአንድ ወቅት ብቻ የተፈጸመና ‹‹ነበር›› እየተባለ የሚነገር ያለፈ ታሪክ ሳይኾን፣ ለዘለዓለሙ ሲነገርና ሲፈጸም የሚኖር ሕያው ቃል ነው፡፡ ይህንም እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ በልዩ ልዩ መንገድ እየተገለጠ ለዘመናት በሚያደርገው ድንቅ ሥራና ተአምር መገንዘብ እንችላለን፡፡ ዛሬም ሀብት ንብረት ያለን ምእመናን በትሩፋት ሥራ በመሠማራት ማለትም እንግዶችን በመቀበል፣ ለተራቡ በማብላት፣ በመመጽወት እና በመሳሰለው ተግባር ከኖርን፤ በቂ ንብረት የሌለን ደግሞ ልቡናችንን ንጹሕ ከማድረግና ከኀጢአት ከመለየት በተጨማሪ ለተቸገሩ በመራራት፣ በደግነት፣ በቀና አስተሳሰብ ከተጓዝን እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ያድራል፡፡ አድሮም ይባርከናል፤ ይቀድሰናል፡፡ እርሱ ያደረበት ሰውነት ይባረካል፤ ይቀደሳልና፡፡ ደግሞም ልጅ ለሌለን ልጅ፤ ዘመድ ላጣን ዘመድ በመስጠት ዘራችንንም ይባርክልናል፡፡ በጥቅሉ የልባችንን መሻት ዐውቆ የምንሻውን መልካም ነገር ዅሉ ይፈጽምልናል፡፡ ይህ ዅሉ የእግዚአብሔር ጸጋ ይበዛልን ዘንድ እኛም በርትዕት የተዋሕዶ ሃይማኖት እንጽና፤ በክርስቲያናዊ ምግባርም እንትጋ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡