ምጽዋት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ግንቦት ፳፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? እንኳን ለብርሃነ ዕርገቱ እንዲሁም ለበዓለ ኀምሳ አደረሳችሁ! ለአባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የወረደበትን በዓለ ሃምሣ ባከበርን ማግሥት ጾመ ሐዋርያት ይገባል፡፡ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ከተቀበሉ በኋላ ጥበብ ማስተዋሉን አግኝተው በእምነት ጸንተው የምሥራቹን ወንጌል ለማስተማር ከመሄዳቸው በፊት ጾምን ጾመዋል፡፡ ይህን ጾም ሁል ጊዜ ከበዓለ ኀምሳ ማግሥት ጀምሮ እስከ ሐምሌ አምስት ድረስ እንጾመዋለን፡፡

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዐዋጅ ከሚጾሙ ሰባቱ አጽዋማት አንዱ ይህ ጾመ ሐዋርያት ወይም በተለምዶ የሰኔ ጾም እየተባለ የሚጠራው ነው፤ እኛም በአቅማችን ይህንን ጾም ልንጾም ይገባናል፤ ከአባቶቻችንን ቅዱሳን ሐዋርያት በረከትን ለማግኘት፣ ጾሙን እንጽም፤ በዘመናዊ ትምህርታችን ትምህርት ጨርሰን የማጠቃለያ ፈተና የምንፈተንበት ወቅት ነውና በርትተን እናጥና ፤ በመጪው ክረምትም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመገኘት መንፈሳዊ ትምህርትን ለመማር ከአሁኑ እናቅድ (እንዘጋጅ) መልካም! ውድ ልጆች! ለዛሬ የምንማረው ስለ “ምጽዋት” ነው፡፡

ምጽዋት ማለት “ማዘን ፣መራራት፣ ለተቸገረ ሰው መስጠት” ነው፤ ምጽዋትን ለመስጠት የልብ ርኅርኄ እና ምሕረት ያስፈልጋል፤ ለሰዎች እንድንራራና ካለን ላይ እንድናካፍል ያዘዘን እግዚአብሔር ነው፡፡ ‹‹…ድሆች በምድር ላይ አያልቁምና ስለዚህ እኔ በአገርህ ውስጥ ላከው ደሀ ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ዘርጋ ብዬ አዝዝሃለሁ፡፡ ›› (ዘዳግም ፲፭፥፲፩)

ውድ ልጆች! ካለን ለተቸገረው ስንሰጥ እግዚአብሔር በምድር በረከቱን በኋላም ደግሞ መንግሥቱን ያወርሰናል፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዳግም ምጽአቱ ባስተማረበት ትምህርት ካላቸው በማካፈል የተራበውን ያበሉ፣ የተጠማውን ያጠጡ፣ የታረዘውን  የተራቆተውን ያለበሱ፣ ያዘነውን ያጽናኑትን እንዲህ የሚል የሕይወት ቃልን ያሰማቸዋል፡፡ ‹‹…ኑ ዓለም ከተፈጠረች ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ…፡፡›› (ማቴዎስ ፳፭፥፴፬)  ይህንን የምሥራች የሕይወት ቃል የሚሰሙ ሰዎች ካላቸው ላይ ለሌላቸው ያካፈሉ ችግረኞችን የረዱ ናቸው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለመስጠት (ለመራራት) ለማካፈል የግድ ሀብታም መሆን  አይጠበቅም፡፡ ትርፍ ነገር ያለን መሆን የለበትም ካለን ላይ ምንም ለሌላቸው ካካፈልን ይህ ራሱ ለሰዎች ማዘን ነውና ዋጋው  ታላቅ ነው ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በመራራት፣ በማዘን ካላቸው ላይ በማካፈል በምድርም በረከቱን ያገኙ በኋላም ዘለዓለማዊውን መኖሪያ መንግሥተ ሰማያትን የወረሱ ብዙ ቅዱሳን አሉ፤ ለአብነት እንዲሆነን አንድ ታሪክ እንመልከት፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኩ መልካም ሥራው ተመዝግቦ የምናገኘው እግዚአብሔርን የሚያመልክ  ለችግረኞች የሚራራ፣ ካለው ለሌላቸው በማካፈል ድሆችን ይመግብ የነበረ ጦቢት የተባለ ሰው ነበር፡፡ ጦቢት ጦቢያ የተባለ ልጅም ነበረው፤ ምጽዋትን ይሰጥ (ችግረኞችን ያበላ ያጠጣ ነበር)፤ ልጆች! እኛም በአቅማችን ካለን ለሌላቸው ጓደኞቻችንን በማካፈል መስጠትን መለማመድ አለብን፤ገና ከልጅነታችን ጀምሮ በትንሹ ነገር መስጠትን፣ መለገስን፣ ለሰዎች ማዘንን መለማመድ አለብን፡፡

ይገርማችኋል ልጆች! ጦቢት ሁል ጊዜ ምግብ አቅርቦ ከመመገቡ በፊት ልጁ ጦቢያን ከመንገድ የተቸገረ የተራበ ካለ እንዲጠራ ያደርግና አብሮ ይበላ ነበር፤ የተራቆቱትንም ያለብስ ነበር፤ አያችሁ ልጆች! መልካም ሥራ የሚጀመረው መስጠት የሚጀመረው ካን ነገር ነው! ጦቢት ከሚበላው ያበላ ፣ከሚለብሰውም ያለብስ ነበር፡፡

ታዲያ አንድ ጊዜ ዓይኑን ታመመና የሚረዳው ሰው ፈለገ፤ ከዚያ ምን ሆነ መሰላችሁ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል በሰው አምሳል ተገለጠና እንደሠራተኛ አገለገለው፤ በመጨረሳም የሠራበትን ዋጋ ሊከፍለው ሲል ለካስ በሰው ተመስሎ ያገለግለው የነበረው  የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነበር፡፡

ከዚያም እንዲህ አለው፤ ‹‹ምጽዋት ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ ታድናለችና ከኃጢአት ሁሉ ታነጻለችና፡፡›› (ጦቢት ፲፪፥፱) በማለት ስለ ምጽዋት ጥቅም ነገረው ታሞ የነበረ(  ማየት የማይችለውንም) ዓይኑን አበራለት ( አዳነው)፡፡

ውድ ልጆች! መልካም መሥራት ጥቅሙ ለራስ ነው፤ ለቸገረው ሰው መስጠት መርዳት በችግር ጊዜ እግዚእብሔር ደግሞ እኛን ይረዳናል፡፡

ምጽዋት ስንሰጥ ምን ማድረግ እንዳብን እንመልከት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ምጽዋትን ስንሰጥ ለቸገረው ስንረዳ፣ ካለን ላይ ስናካፍል በትሕትና መሆን አለበት፡፡ ምክንያም የምንሰጠው እግዚአብሔር ከሰጠን ላይ ነውና፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ንጉሥ ዳዊት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሥሪያ ወርቁን ብሩን ከሰጠ በኋላ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ “ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና ከእጅህ የተቀበልነውን ሰጥተንሃል ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው?” ፡፡ (፩ኛ ዜና.፳፱፥፲፬) ስንሰጥ ራሳችንን ከፍ አድርገን ማየት የለብንም፤ የምንሰጠው እግዚአብሔር ከሰጠን ላይ መሆኑን ማመን አለብን፡፡

ሌላው ደግሞ በፍቅር ፣ደስ ብሎን መስጠት ይገባናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ ስጦታችን በፍቅር በደስታ መሆን እንዳለበት እንዲህ ያስተምረናል፡፡  “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።”  (፪ኛ ቆሮንቶስ ፱፥፯)

ያለግብዝነት በትሕትና መለገስ አለብን፤ ሰዎች እንዲያሞግሱን፣ ሳይሆን ሰዎች እንዲያዩን ሳይሆን እግዚአብሔር ዋጋ ይከፍለኛል በማለት በትሕትና ልንመጸውት፣ ሰዎችን ልንደግፍ ካለን ልናካፍላቸው ያስፈልጋል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ምጽዋት ባስተማረው ትምህርት እንዲህ በማለት አስተምሮናል፤ እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በሥውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በሥውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” እንዲል፡፡ (ማቴ.፮፥፩-፬)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሰፊ ከሆነው ከምጽዋት ትምህርት ለእናንተ በሚረዳ መልኩ በአጭሩ ነገርናችሁ እንግዲህ የምጽዋት ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ የተቸገሩትን ይረዳል፤ ጉልበት ያለው የደከሙትን ይደግፋል፤ ዕውቀት ያለዋ ያላወቁትን ያሳውቃል፡፡

እኛም ወደፊት ስናድግ ይህን በጎ ምግባር ለመሥራት ከአሁኑ ለሰዎች መስጠትን  መልመድ አለብን፡፡

ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ! ለወላጅ መታዘዝን፣,ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!