ምድር እስከ መቼ ታለቅሳለች?

ክፍል አንድ

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

ኅዳር ፳፭፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

መሬት/ምድር/ባዕል-ባለ ጸጋ ናት፡፡ ብዕል (ሀብት) ሁሉ ይገኝባታል፡፡ ‹‹ወበረከተ ምድር እንተ ባቲ ኩሉ፤ በበረከት የተሞላች ምድር›› እንዲል ጌታ እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹ሁሉ የተገኘ ከርሱ ነውና ባዕል ነኝ›› ሲል መሬትን/ምድርን ፈጠረ፡፡ ይህችን ምድር የፈጠራት ዕፅዋቱን፣ አዝርዕቱን፣ አትክልቱን አብቅላ ለሰውና ለእንስሳት ለፍጥረት ሁሉ የሚበጀውን ምግበ ሥጋ ምግበ ነፍስ አስገኝታ፣  እንድትመግብ ልብስም ጉርስም መጠለያም ሆና እንድታገለግል ለበጎ ዓላማ ነበር፡፡ (ዘፍ.፩፥፩ ትርጓሜ)

አምላካችን እግዚአብሔር ምድርን ለበጎ ዓላማ እንደ ፈጠራትና ‹‹ምድርሰ ሀለወት ዕራቃ እምትካት፤ ምድርም ባዶ ነበረች›› ከክፋት፣ ከችግር፣ ከክፉ ነገር ሁሉ ባዶ ንጹሕ አድርጎም እንደ ፈጠራት፣ ምድርን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሥነ ፍጥረት በየወገናቸው በጎ መልካም አድርጎ እንደ ፈጠራቸው፣ እርሱም ከፈጠራቸው በኋላ በጎና መልካም እንደሆኑ ማየቱን ‹‹ወርእየ እግዚአብሔር ከመ ሠናይ፤ እግዚአብሔርም መልካም እንደሆነ አየ በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡ (ዘፍ.፩፥፰)

ጉዳያችን ጋር ስንመለስ ይህች የዕለተ እሑድ ክብርት ፍጥረት፣ ይህች የብዕል መከማቻ፣ መገኛ፣ ብዕሏ ለሰው ልጅና ሕይወት ላለው ፍጥረት ሁሉ፣ በሰማይ ለሚበሩ፣ በምድር ለሚሽከረከሩ፣ በባሕር፣ በየብስ ላሉ ሁሉ የሕይወት ምንጭ የመኖር የሕልውና ምክንያት የሆነች ለሕያዋን ሁሉ ልብስና ጉርስ ብሎም መጠለያና መከለያ፣ ውበትና ጌጥ የሆነች ምድር በሰዎች ጣልቃ ገብነት፣ ባልተገባ ሥራቸውና ክፋታቸው ምክንያት እያለቀሰችና እየደማች፣ እያዘነችና እያነባች ነው፤ በዚህ በሰዎች ክፋት ምክንያት “እስከ መቼስ እያለቀሰች ትኖራለች?” የሚለውን ጥያቄ ነቢዩ ኤርምያስ በምሬት ቃል ይጠይቃል፡፡

‹‹ምድር ለምን ታለቅሳለች?›› እንዲሁም ‹‹ለቅሶዋ ምክንያቱ ምንድን ነው?›› የሚለው ነገር ነው መሠረታዊው ጥያቄ ነው፡፡ ምድር ለምን እንደምታለቅስ፣ ይህ ልቅሶዋስ ለምን እንደዚህ መቋጫና ማብቂያ እንዳጣ፣ እስከ መቼስ እንደሚዘልቅ እጅግ የሚያሳዝን ጥያቄ ነቢዩ ይጠይቅና ምክንያቱንም ራሱ ይናገራል፡፡ ‹‹ምድር እስከ መቼ ታለቅሳለች? በርሷም በሚኖሩ ሰዎች ክፋትም የምድረ በዳው ሣር ደረቀ አዕዋፍና እንስሳትም አለቁ›› በማለት ምክንያቱን ያስቀምጣል፡፡ (ኤር.፲፪፥፬)

ግብረ ሕማማት የተባለው መጽሐፋችን በበኩሉ ይህንኑ የነቢዩን ጥያቄ የሚመልስልን ‹‹ጻድቁን ሰው ኑ እንግደለው አሉ፤ ለእኛ ጭንቅ ሆኖብናልና ሥራዎቻችንም ይቃወማቸዋልና አሉ›› በማለት ነው፡፡

በመቀጠል ‹‹ከዚህ ዓለም በጎ ሰው ጠፍቷልና፤ ከዚህ ዓለም ፍርድ የሚያቀና ሰው የለምና ሁሉም ባልንጀራውን ያስጨንቃል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ወዳጆቻችሁን አትመኗቸው፤አለቆቻችሁንም ተስፋ አታድርጓቸው፤ አጠገብህ ከምትተኛ ሚስትህም ተጠበቅ፤ ልጅ አባቱን ያዋርዳል፤ ሴት ልጅም በእናቷ ላይ በጠላትነት ትነሣለች›› በማለት ያብራራዋል፡፡ (ግብረ ሕማማት ዘዓርብ ነግህ)

‹‹የተባረከች፣ ሁለመናዋ እንጨቶችን የተመላች ምድር›› ብሎ ሄኖክ የጠራት ምድር ለምን እንደምታለቅስ አሁን ግልጽ ነው፡፡ የዝናብ ውኃ እየጠጣች፣ የበረሃውን ሣር፣ ዕፅዋቱን፣ አዝርእቱን፣ አትክልቱን እንድታበቅል፣ እንድታለመልም፣ ያማረውን፣ የተወደደውን ፍሬም አፍርታ ለሰው ለእንስሳ ምግብና መኖሪያ እንድትሆን፣ በበረከት ተሞልታ  ‹‹ወበረከተ ምድር እንተ ባቲ ኩሉ›› ተብላ የተፈጠረች መልካም ምድር፣ ከሰዎች ክፋት የተነሣ አለቀሰች፡፡ (ሄኖክ ፯፥፴፩)

በበረከቷ በጠገቡና በርሷ ላይ በሚኖሩባት ሰዎች ምክንያት፣ እርሷን በልተውና ጠጥተው፣ለብሰውና ተጫምተው በሚኖሩ ሰዎች ክፋት ምክንያት አለቀሰች፡፡ በዚህም የተነሣ የምድረ በዳው ሣር ደረቀ፤ አዕዋፍና እንስሳት ሁሉ አለቁ፤ ምድር ጸጋዋንና ልብሷን አጣች፤ በውኃ ፈንታ በዝናቡ ፈንታ የሰውን ደም እንድትጠጣ ተገደደች፡፡

ለዚያውም የንጹሑን ሰው ደም የጻድቁን ሰው ደም፣ በክፋታቸው መንገድ ያልሄደውን፣ ክፉ ግብራቸውን የተቃወመውን ንጹሑንና ጻድቁን እንግደለው ተባባሉ፡፡ ገድለውም ጣሉ፤ ደሙንም አፈሰሱ፤ ምድርም የጻድቁን ሰው ደም ጠጣች፤ ስለዚህም በዚህ ዓለም በጎ ሰው ጠፍቷልና፤ፍርድንም የሚያቀና የለምና፤ ሁሉም በወዳጁ በባልንጀራው ላይ አስጨናቂ ሆኗልና፤ የሚታመን ወዳጅ፣ ተስፋ የሚደረግ አለቃም የለምና፤ አካል የተባለች ሚስት በባሏ ላይ፣ የአብራክ ክፋይ የምትሆን የሚሆን ልጅ በወላጁ ላይ በጠላትነት ተነሥተዋልና ለአባት ለእናትም ውርደት ኀፍረት ሆነዋልና ምድር አልቅሳለች፡፡

ምድር ስለምን አለቀሰች? የጻድቁን ሰው ደም ሳትፈልግ በመጠጣቷ እግዚአብሔር ተቆጥቷታልና፡፡ (፩ኛ መቃ.፳፰፥፳፫) በቃኤል ምክንያት የአቤልን የጻድቁን ደም ስለ ጠጣች፣በየዘመኑ የነቢያቱን የቅዱሳኑን ሁሉ ደም ስለ ጠጣች እግዚአብሔር ተቆጥቷታል፤ ምድር አለቀሰች፡፡ ‹‹ከእግዚአብሔር ቁጣ የተነሣም ምድር ተንቀጠቀጠች ፤ተናወጠችም፤ የተራሮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፤ እግዚአብሔር ተቆጥቷልና ተንቀጠቀጡ›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት ከቁጣው ትኩሳት የተነሣ ስለምትናወጥ፣ ስለምትንቀጠቀጥ፣ ስለምትነቃነቅ፣ ስለምትጨነቅ ዘወትር ታለቅሳለች፡፡ (መዝ.፲፯፥፯)

ምድር ስለምን አለቀሰች? ቅዱሳንም ሁል ጊዜ ይከሷታልና ታለቅሳለች፡፡ ቅዱሳን ዘወትር ‹‹ምድር ሆይ ደሜን አትክደኝ፤ ለጩኸቴም ማረፊያ አይሁን፤ አሁንም እነሆ ምስክሬ በሰማይ አለ፡፡ የሚመሰክርልኝም በአርያም ነው›› ይሏታልና ምድር ታለቅሳለች፤ ያለማቋረጥም  ታነባለች፡፡ (ኢዮብ ፲፮፥፲፰)

ምድር ዛሬም እያለቀሰች ነው፡፡ ግን እስከ መቼ ታለቅሳለች? ሰዎችስ ከክፋታቸው የሚመለሱት መቼ ነው? የምድረ በዳው ሣርስ እስከ መቼ ደርቆ ይቀጥላል? አዕዋፋትና እንስሳትስ እስከ መቼ ያልቃሉ? እግዚአብሔርስ ምድርን እስከ መቼ ነው የሚቆጣት? ቅዱሳንስ ስለ ደማቸው እስከ መቼ ምድርን ይካሰሷታል? ነቢዩ ኤርምያስ የሚጠይቀውን ጥያቄ አሁንም እኛ እንጠይቃለን፡፡

ምድር እስከ መቼ ታለቅሳለች?

ይቀጥላል….