‹‹ምድር በውስጧ የሚኖሩትን ታስደነግጣቸዋለች›› (ዕዝራ ሱቱኤል ፬፥፳፬)
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ጥር ፲፫፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
አምላካችን እግዚአብሔር ምድርን እንዴት በውኃ ላይ አጽንቶ እንደፈጠራት ማሰብ እጅግ ያስገርማል፡፡ ‹‹ምድርን በውኃ ላይ አጸና›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት አጽንቶ ለሕያዋን ሁሉ የሕይወትና የደስታ ምንጭ የሆነች ግሩም ድንቅ ሥራው አድርጎ ፈጥሯታልና፡፡ (መዝ.፻፴፭፥፮)
አንድ ሰው ከፍ ያለ ፎቅ ላይ ቢሆን፣ ወይም ትልቅ ዛፍ ላይ ቢንጠለጠል፣ ወይም ከፍ ያለ አልጋ ላይ ቢተኛ፣ ብቻ በማናቸውም ሁኔታ ከመሬት ከፍታ ካለው ነገር ላይ ቢሆን እንዳይወድቅ በመፍራት ብዙ ይጠነቀቃል፤ ብዙ ይጨነቃልም፡፡ መሬት ላይ የቆመ ሰው ወይም የተቀመጠ ወይም የተኛ ሰው ግን ከዚህ ሥጋት ሁሉ ነጻ ነው፡፡ ምክንያቱም ከምድር ወዴትም አይወድቅምና፡፡ ምድር ወይም መሬት የእግዚአብሔር የቻይነቱ፣ የትዕግሥቱ፣ የሆደ ሰፊነቱ ማሳያ ምሳሌ ሆና ሁሉን ችላ የምትኖር መሆኗ ሲገለጽ ‹‹እግዚአብሔርና ምድር የማይችሉት የለም›› ይባላል፡፡
ይሁን እንጂ አሁን አሁን ግን ምድር ራሷ የሚተማመኑባት መቆሚያም፣ መቀመጫም፣ መተኛም መራመጃም ላትሆን ይመስላል፡፡ መሠረቶቿ እየተገለባበጡ፣ ዓለቶቿ ቀልጠው እንደ ውኃ እየፈሰሱ፣ በሆዷ ታቅፋው፣ አምቃው የኖረችውን እንፋሎት እየተፋችው፣ የማናውቀው ማንነቷ እየተገለጠ በእርሷ ላይ የሚኖሩ ሕያዋንን ሁሉ የምታስደነግጥ፣ የምታስጨንቅ ወደ መሆን ተሻግራለችና፡፡
በእርግጥ መጻሕፍትን ስለማንመረምር፣ ስለማናስተውል፣ ቃሉን ስለማንሰማ፣ ሰምተንም፣ ስለምንዘነጋ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህም ነገር ነግሮን ነበር፡፡ ዕዝራ ሱቱኤል እንዲህ ይናገራል፤ ‹‹በእነዚያም ወራቶች ወዳጆች ከወዳጆቻቸው ጋራ እርስ በራሳቸው እንደ ጠላት ይጣላሉ፡፡ ምድርም በውስጧ የሚኖሩትን ታስደነግጣቸዋለች፡፡›› (ዕዝራ ሱቱኤል ፬፥፳፬)
ቅዱሱ ራእይ የሚነግረን ፍቅር ከሰው ልጆች ሲርቅ፣ ወዳጅነት በጠላትነት ሲተካ፣ ወዳጆች ጠላቶች ሲሆኑ፣ ክፋትና ምቀኝነት፣ ጠብና ክርክር በሰው ልጆች መካከል ሲነግሥ፣ አለመተማመን በሰዎች መካከል ሲሰፋ፣ የሰዎች ፍቅር ሽንገላ ሲሆን፣ የመንግሥታት ወዳጅነት በሴራ ሲሞላ፣ ከመደጋገፍ ይልቅ በመጠላለፍ ላይ ሲመሠረት በእነዚያ ወራቶች በልዩ ልዩ መቅሠፍቶች ምድር እንደምትሞላ፣ በውስጧ የሚኖሩባትን ሁሉ እንደምታስደነግጣቸው ነው፡፡
በአሁን ጊዜ ግን እግዚአብሔር ኃጢአተችንን ታግሦ፣ ታግሦ በምድርም ላይ ቁጣውን እያሳየን ነው፡፡ ሰማይም ምድርም የእርሱ ሥራዎች ናቸውና ምድር ብትንቀጠቀጠቀጥ፣ ብትናወጽ፣ ሰማያት ቢያጉረመርሙ፣ ዓለቶች ቢሰነጣጠቁ፣ እንደሰምም ቀልጠው እንደ ውኃ ቢፈሱ፣ ውቅያኖሶች በማዕበል ቢናጡ፣ ነፋሳት ለትውልዱ ሁሉ መዓትን ቢያመጡ፣ እሳት ርጥቡን፣ ደረቁን በጭካኔ ቢያቃጥል ተፈጥሯቸው ሆኖ ሳይሆን የፈጠራቸው እግዚአብሔር ተቆጥቶና ከቁጣው ትኩሳት የተነሣ መሆኑን መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ ሲራክ ይህንን ሲያስረዳ ‹‹ተራሮችንና የምድርም መሠረትን በመዓት ባያቸው ጊዜ ይንቀጠቀጣሉ፤ ይነዋወጣሉ›› እንዳለው ነው፡፡ (ሲራ.፲፮፥፲፱)
‹‹ምድር መላዋ የእግዚአብሔር ናት›› እንደተባለ እግዚአብሔር ሲቆጣ የቁጣው በትር ሆኖ የማያገለግል ፍጥረት የለምና፡፡ (መዝ.፳፫፥፩) በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች ቢበድሉ እግዚአብሔርም ቢቆጣ ውኃ የቁጣው በትር ሆኖ ሰብአ ትካትን አጥፍቷል፡፡ ሰዶምና ገሞራ ቢበድሉና እግዚአብሔር ቢቆጣ እሳት በትር ሆና ታዝዛ የሰዶምን ሰዎች በልታለች፤ ምድርም አፏን ከፍታ በመዋጥ ታዛለች፡፡ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ ‹‹በዙሪያው ብዙ ዐውሎ አለ፤ በላይ ያለውን ሰማይን ምድርንም በሕዝቡ ለመፍረድ ይጣራል›› እንደተባለ፡፡ (መዝ.፵፱፥፬)
ዛሬ የምድር መሠረቶች እየተናወጡ ነው፡፡ ሕይወት ያለውን ፍጡር ሁሉ መድረሻና ጥግ ያሳጣ ፈተና በምድር ላይ እየታየ ነው፡፡ ምድር እንደ ዛፍ የምትወዛወዝበት፣ እሳት የምትተፋበት፣ ሊቆሙባት፣ ሊተኙባት የምታስጨንቅና የምታስደነግጥ ሆናለች፡፡ ይህም በሰው ልጆች ዓለም ውስጥ አስጨናቂው ጊዜ ነው፡፡ ሰዎች ከፍተዋል፤ ተፈጥሮም ከፍታለች፤ ሰዎች ፈጣሪንና ተፈጥሮን በድለዋል፤ እግዚአብሔርና ተፈጥሮ ደግሞ የቁጣቸውን ጅራፍ አንሥተዋል፡፡ ይህም የዘመኑ ፍጻሜ ስለመድረሱ አመላካችም እንደሆነ መልአኩ እንዲህ ሲል ነግሮታል፡፡ ‹‹ተነሥተህ በእግርህ ቁም፤ ጩኸት የተሞላበትን ቃል እነግርሃለሁ፡፡ መነዋወጥ አንተ የቆምህበት ቦታ ቢነዋወጽ መነዋወጹ የኅልፈት ምልክት ነውና፡፡ ያን ጊዜ የምድር መሠረቶች የኅልፈትን ምልክት ያስረዳሉ›› በማለት፡፡ (ዕዝ.፬፥፲፬)
እነዚህ ሁሉ ምልክቶች የኅልፈተ ዓለም ምልክቶች መሆናቸውን ዕዝራ ነግሮናልና እንዘጋጅ፡፡ ከዚህ የበለጠ ማስጠንቀቂያ ሊሰጠን፣ ከዛሬ የተሻለ የማንቂያ ደወል ሊደወልልን አይችልምና፡፡ ጌታችንም በወንጌል ይህንኑ ምልክት ሰጥቶን እንድንዘጋጅም ሲያስሳስበን ‹‹ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፡፡ የሰው ልጅ በማታስቡት ሰዓት ይመጣልና›› በማለት ነግሮናል፡፡ (ማቴ.፳፬፥፵፬)
ለመሆኑ መዘጋጀት ማለት ምን ማለት ነው? መዘጋጀት ማለት ስንቅ መቋጠር ነው፤ ትጥቅን ማጥበቅ ነው፡፡ ትጥቁም ንስሐ ስንቁም ሥጋውና ደሙ ነው፡፡ ንስሐ ካልገባን ሥጋውን ደሙን ካልተቀበልን፣ ዕለት ዕለት በሰው ልጅ ላይ እየመጣ ያለው ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ መዓት ትምህርት ሰጥቶን ወደ ቀልባችን ካልተመለስን በነፍስም በሥጋም ፍጻሜያችን ሞት ነው፡፡
ከሞተ ሥጋ አይቀርም፤ ከሞተ ነፍስ ግን ይጠብቀን፤ አሜን!