ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሰኔ ፳፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? በተለምዶ የሰኔ ጾም እየተባለ የሚታወቀው ጾመ ሐዋርያት ሰኔ ፲፯ (ዐሥራ ሰባት) ቀን ተጀምሮ እስከዚህ ዕለት ደርሷል፡፡ ይህ ጾም ከሰባቱ የዐዋጅ አጽዋማት አንዱ ሲሆን አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ከተቀበሉ በኋላ አገልግሎታቸውን በጸሎትና በጾም ጀምረዋል፤ እኛም እነርሱን አብነት አድርገን በዓለ ጰራቅሊጦስ ከተከበረበት ማግሥት አንሥቶ እስከ ሐምሌ አራት ቀን ድረስ እንጾመዋን፡፡ከዚያም በኋላ ሐምሌ አምስት ቀን የጾሙ ፍቺ ይሆናል፡፡ በዚህም ቀን የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስ የዕረፍት በዓል ነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በሰንበት (በዕረፍት ጊዜያችሁ) ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ማስቀደስ እንደሚገባ፣ መጾም መጸለይ እንዳለብን መዘንጋት የለብንም! በዘመናዊ ትምህርታችሁም ሁለተኛው የመንፈቀ ዓመት ትምህርት ተፈጽሞ ውጤት ተቀብላችኋል አይደል! መቼም በጥሩ ውጤት ከክፍል ክፍል እንደ ተሸጋገራችሁ ተስፋችን እሙን (የታመነ) ነው!
ባሳለፍነው የትምህርት ዘመን ደከም ያለ ውጤት ያስመዘገብን ደግሞ ለሚቀጥለው ዓመት በርትተን ተምረን ጎበዝ ተማሪ ለመሆን ከአሁኑ ማቀድ አለብን! በክረምቱ የዕረፍት ጊዜያችን በማጥናት መጻሕፍትን በማንበብ ልንበረታ ያስፈልጋል! መልካም! አሁን ለዛሬ ወዳዘጋጀንላችሁ ትምህርት እናምራ! ባለፈው ምሥጢረ ቁርባንን ተምረን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ የምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ትምህርት እንማራለን፡፡ ተከታተሉን!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ትንሣኤ ማለት “መነሣት፣ መውጣት፣ ብቅ ማለት፣ መታደስ፣ መብቀል፣ አዲስ ሕይወት ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፮፻፵፪) ቃሉ ብዙ ትርጉም (ፍቺ) ቢኖረውም እኛ የምንማማረው ከሞት በኋላ አዲስ ሕይወት እንዳለ የሚገልጸውን ነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሰው ሙቶ ከፈረሰ ከበሰበሰ በኋላ አካል ሠርቶ ነፍስ ዘርቶ ሕያው ሆኖ ይነሣል፤ ሥጋና ነፍስ በመጨረሻ ዘመን እንደገና ተዋሕደው ዳግመኛ በማይፈርስና በማይበሰብስ ሥጋ የሚነሡ መሆናቸውን የሚገልጸው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ትንሣኤ ሙታን ይባላል፡፡ (ዐምደ ሃይማኖት በመምህር ብርሃኑ ጎበና ገጽ ፹፭)
ሰው ከሞተ በኋላ ሥጋው በመቃብር ውስጥ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ፈርሶ በስብሶ ይቆይና በዕለተ ምጽዓት ግን ሥጋው አጥንቱ ጅማቱ የራስ ቅሉ ከያለበት ተሰብስቦ ከሕያዊት ነፍስ ጋር ተዋሕዶ እንደገና ይነሣል፡፡ (ዐምደ ሃይማኖት በመምህር ብርሃኑ ጎበና ገጽ ፹፭) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ያመኑ ሁሉ የክብር ትንሣኤ እንደሚነሡ ነግሮናል፤ ‹‹እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ባልኩ ጊዜ ሁሉን ወደ እኔ እስባለው›› በማለት በሰጠን በዚህ ተስፋ መሠረት በዕለተ ምጽአት ተነሥተን ለዘለዓለም በሕይወት በክብር እንኖራለን፡፡ (ዮሐ.፲፪፥፴፪)
የትንሣኤያችን በኩር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱሰስ ክርስቶስ ነው፤ ለእኛ ሲል በመስቀል ላይ ተሰቅሎልን ከሞተ በኋላ በመቃብር ውስጥ ሦስት ቀንና ሌሊት ቆይቶ ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፤ የእኛንም ትንሣኤ አበሠረን፤ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላሲስ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹…እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ መጀመሪያ ከሙታንም በኩር ነው…›› በማለት ገልጾናል፤ (ቆላ.፩፥፲፰) አባታችን ቅዱስ ኤጲፋንዮስም እንዲህ አስተምሯል፤‹‹አንድ ሆነው የሚነሡትን ትንሣኤ ዛሬ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሙታን ትንሣኤያቸው በኩር ነው፤ እንግዲ ወዲህም ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ የተነሣ እርሱ ነው፤ ዳግመኛ ሞት አያገኘውም፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ ምዕራፍ ፶፯ ቁጥር ፭)
ውድ እግዚአብሔር ልጆች! በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ ሞቶ በስብስ አይቀርም፤ የክብር ትንሣኤን ያገኛል፡፡ ጌታችን መደኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹…ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል…›› በማለት በአማናዊ ቃሉ ነግሮናልና፡፡ (ዮሐ.፲፩፥፳፭)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስለ ትንሣኤ ሙታን አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን የተነገረ ትንቢት የተመሰለ ምሳሌ ነበር፤ ጥቂቶችን ብንመለከት ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ እንዲህ ብሎ ተናግሯል፤‹‹ሙታንም ሕያዋን ይሆናሉ፤ሬሳዎችም ይነሣሉ፡፡ በምድር የምትኖር ሆይ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፣ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም፡፡›› (ኢሳ.፳፮፥፲፱) ነቢዩ ዳንኤልም ሞተን እንደማንቀር ትንሣኤ እንዳለን ትንቢትን ተናግሯል፤ ‹‹በምድር ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኩሌቶቹም ወደ ዘለዓለም ሕይወት፣ እኩሌቶቹም ወደ ዕፍረትና ዘለዓለም ጉስቁልና፡፡›› (ዳን.፲፪፥፪)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስለ ትንሣኤ ሙታን ማስረጃ የሚሆኑ በምሳሌ ከተነገሩት እንመልከት፤ ‹‹…ከታጨደ ከተቆረጠ በኋላ በእርሻ የሚዘራ ዘር የትንሣኤን ነገር ያስረዳናል፤ ከዚህ ዓለም በሞት እንድንለይ በምድር ላይ ይዘራል፤ ከተዘራ በኋላ ዳግመኛ ይበቅላል፤ ሰውም ከተቀበረ በኋላ ይነሣል፤ አንበጣ ከሞተ በኋላ አካሉ ከተገኘበት ከእንቁላሉ በመወለድ ከምድር ይነሣል፤ ፍሬዎችም ይዘራሉ፤ አስቀድመውም በምድር ውስጥ ይፈርሳሉ፤ ይበሰብሳሉ፤ ከብዙ ቀንም በኋላ ምድር የዘሩባትን ታበቅላለች፤ ካልፈረሱም አይበቅሉም…›› (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ ምዕራፍ ፶፰ ቁጥር ፭ ገጽ ፻፺፭)
ውድ እግዚአብሔር ልጆች! በተወሰነ መልኩ ስለ ትንሣኤ ሙታን ተመለከትን፤ ጌታችን ዳግም ለፍርድ በመጨረሻው ቀን ለፍርድ ይመጣል፤ ‹‹እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመጣል›› ተብሎ እንደተገለጸው በትንሣኤ ሙታን ጊዜ የሰው ልጆች ሁሉም ይነሣሉ፤(የሐዋ.፩፥፲፩) ኃጢአት የሠሩ፣በእግዚአብሔር ያላመኑ ተፈርዶባቸው ወደ ገሃነመ እሳት ሲገቡ በእግዚአብሔር አምነው በምድር ላይ መልካም ሥራ ሠርተው የነበሩ ደግሞ የክብር ትንሣኤን ተነሥተው የተዘጋጀላቸውን ዘለዓለማዊ ርስት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡
ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይመሰክርልናል፤ ‹‹ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እናንተ የአባቴ ቡሩካን ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ››፡፡ ካለ በኋላ በግራው ያሉትን ደግሞ በወቀሳ ቃል እንዲህ ይላቸዋል፡፡ ‹‹እናንተ ርጉማን ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደተዘጋጀላቸው ወደ ዘለዓለም እሳት ከእኔ ሂዱ፡፡… እነዚያም ወደ ዘለዓለም ቅጣት ጻድቃን ግን ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይሄዳሉ፡፡›› (ማቴ.፳፭፥፴፪-፵፮)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ትምህርት በጣም ሰፊና ጥልቅ ነው፤ እኛ ግን ለትምህርት እንዲሆን በጣም ጥቂቱን ተመለከትን፤ የሰው ልጅ በክብር ለክብር ተፈጥሮ ነበር፤ ነገር ግን በበደል ምክንያት ሞት መጣብን፤ ይህም ሞት በትንሣኤ ድል ተነሥቶልን በመጨረሻው ቀን እንነሣለን፡፡ ታዲያ የክብር መንግሥቱን ለመውረስና ‹‹ኑ እናንተ አባቴ ብሩካን..›› የሚለውን የሕይወት ቃል ለመስማት በምድር ላይ ስንኖር በእምነታችን መጽናት አለብን፡፡
ከዚህም ጋር ያመነውን በሥራ በመግለጥ (መልካም በመሥራት) ትእዛዙን በመፈጸም ሕጉን በማክበር በጎ ምግባራትን በመሥራት ልንኖር ያስፈልጋል፡፡መልካም ሥራ የሚጀምረው ደግሞ ከቤታችን ነው፤የወላጅን ምክር በመፈጸም፣ በመታዘዝ፣ ሥርዓትን ይዘን በመኖር ከዚያም ከፍ እያልን ስንመጣ እንደ አቅማችን የቅድስናን ሥራ በመሥራት ልንኖር ይገባናል፡፡ ቸር ይግጠመን! በእምነት ጸንተንና በምግባር ጎልብተን በመገኘት የክብር መንግሥቱን ወራሽ እንድንሆን ይርዳን! አሜን!!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!