ምሥጢረ ቊርባን  

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

ሰኔ ፲፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን! በዓለ ሃምሳ ተብሎ የሚታወቀውን ወቅት እንዴት አሳለፋችሁት? እንኳን ለብርሃነ ዕርገቱ እንዲሁም ደግሞ ለበዓለ ጰራቅሊጦስ አደረሳችሁ! አሁን ደግሞ በተለምዶ የሰኔ ጾም እየተባለ የሚታወቀው ጾመ ሐዋርያት ሰኔ ፲፯ (ዐሥራ ሰባት) ቀን ይጀምራል፡፡ ከወዲሁ እንኳን አደረሳችሁ እንላለን!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች!  በሰንበት (በዕረፍት ጊዜያችሁ ሄዳችሁ) ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ማስቀደስ እንደሚገባ፣ መጾም መጸለይ እንዳለብን መዘንጋት የለብንም! በዘመናዊ ትምህርታችሁም ሁለተኛውን መንፈቀ ዓመት ጨርሳችሁ የማጠቃለያ ፈተና የተፈተናችሁ አላችሁ! እንዲሁም ደግሞ እየተፈተናችሁም ያላችሁ ትኖራለችሁና በርትታችሁ ማጥናት ሥሩ! መልካም! አሁን ለዛሬ ወዳዘጋጀንላችሁ ትምህርት እናምራ፤ ባለፈው ምሥጢረ ጥምቀትን ተምረን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ የምሥጢረ ቊርባንን ትምህርት እንማራለን!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቊርባን ማለት የሱርስት ቃል ሲሆን “መብዓ፣ ስጦታ፣ አምኃ” ማለት ነው፤ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የተሰጠን ያለዋጋ ሳይገባን እንዲሁ በችሮታ (በስጦታ) ነውና ስጦታ ተብሏል፡፡

ሌላኛው ትርጉሙ ደግሞ በጽርዕ (በግሪክ) ቋንቋ አምላካዊ ሱታፌ፣ አምላካዊ ደስታ ይባላል፤ ደስታን የምናገኘው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ስንቀበል ስለሆነ ነው፡፡ (ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ገጽ ፵፰ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎርጎሬዎስ ካልዓይ)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቊርባን ስንል የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ነው፤ ምሥጢረ ቊርባንን የመሠረተልን ጌታችን ነው፤ አስቀድሞ  ለአባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በትምህርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፤ ‹‹…ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻ ቀን አስነሣዋለው፡፡ ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና…፡፡›› (ዮሐ.፶፮፥፶፬)

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ  በብሉይ ኪዳን ለአያሌ ዓመታት በትንቢት በምሳሌ ሲነገር የኖረ ነው፤ ለምሰሌ አንዱን እንመልከት፤ ‹‹ደሙ ምልክት ይሁንላችሁ›› ተብሎ እንደተነገረ እስራኤል ከግብጽ ሊወጡ ሲሉ የበጉን ሥጋ በልተው ደሙን በቤታው መቃን ላይ ቀብተው (ረጭተው) በግብጽ ከወረደው መቅሠፍት የዳኑበት በግ የመሲሕ (የጌታችን ኢየሱስ ክረስቶስ) መሥዋዕትነት ምሳሌ ነው፡፡ (ዘጸ.፲፪፥፲፫) ልጆች! ይህንን ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የጌታችን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ምሳሌ እንደሆነ ነግሮናል፤ ‹‹ …እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደተዋጃችሁ ታውቃላችሁ›› እንዲል፡፡ (፩ኛ ጴጥ.፩፥፻፱፰) በነቢያቱም ትንቢት ሲነገር ነበር፡፡ (ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ገጽ ፵፱ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎርጎሬዎስ ካልዓይ)

በተለያየ ዘመናት በምሳሌ ሲያስመስል፣ በትንቢት ሲያናግር የነበረውን በአዲስ ኪዳን ደግሞ በምሴተ ሐሙስ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመፈተት ለቅዱሳን ሐዋርያት አቀበላቸው፤ ‹‹….ኢየሱስም እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፤ ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ፤ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡›› (ማቴ.፳፮፥፳፯)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ (በቅዱስ በቁርባን) እኛ ሁላችንም እንከብር ዘንድ ለሚያምኑ ሁሉ መንጻት ሥርየት ኃጢአት ክብር ሕይወት የሚገኝበትን አንዲት መሥዋዕት ለዘለዓለም የማትሻር የማትለወጥ አድርጎ ሥጋውንና  ደሙን ሰጥቶናል፡፡ ይህ የአዲስ ኪዳን መሥዋዕት የተመሠረተውም በራሱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ በቤተ አልዓዛር ነው፡፡ የዘለዓለም ሕይወት የሚሰጥ የሕይወት ምግብ ነው፡፡የምንበላ (የምንቆርብ) ክርስቲያኖችም ዘወትር ሞቱንና ትንሣኤውን እንድናስብ ታዝዘናል፡፡ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉ አምነው የተጠመቁ ናቸው፤ መከራ መስቀሉን እያሰብን ልንቀበል (ልንቆርብ) ይገባል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን (ቅዱስ ቊርባን) ለመቀበል ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ማመን ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ንስሓ የገባ ሰው መሆን ይገባዋል፡፡ ዐሥራ ስምንት ሰዓታትን ከምግብና ከውኃ ተከልክሎ (ሳይበላ፣ ሳይጠጣ) መቆየትም አለበት፤ እንዲሁ ሳይዘጋጁ ንስሓ ሳይገቡ፣ ሳይጾሙ፣ ሳያምኑ ቢቀበሉ ዕዳ በደል ይሆንባአዋል እንጂ ለሕይወት አይሆንላቸውም፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳወሎስ በ፩ ቆሮ. ፲፩፥፳፮ መልእክቱ ‹‹ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት፡፡ ሰው ግን ራሱን ይፈትን አንደሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና ይጠጣልና›› በማለት እንዴት ወደ ቅዱስ ቁርባን መቅረብ እንዳለብን ተናግሯል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሳይገባው›› በማለት የተናገረው ኃይለ ቃል ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል የሚገባቸውና የማይገባቸው ሰዎች መኖራቸውን ይገልጥልናል።

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በተቀበልን (በቆረብን) ጊዜ ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች አሉ፤ ከተቀበልን (ከቆረብን) በኋላ መታጠብ፣ ጥፍርን መቁረጥ፣ ፀጉርን መላጨት አይገባም፡፡ ምክንያቱም ከሥጋ ወደሙ መለኮት ተለይቶታል ያሰኝብናልና፡፡ (ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ገጽ ፶፪ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎርጎሬዎስ ካልዓይ)

እንዲሁም ደግሞ ለቅዱስ ቊርባኑ ክብር ስንል ሩቅ ጐዳና መሄድ አይገባም፤ ድካም ያስከትላልና፤ ክርክር መግጠም መጨቃጨቅ (መጣላት) አይገባም፤ ክፈ ነገር ወደ መናገር ያደርሳልና፤ ስንመገብ በመጠን መሆን አለበት፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እጅግ ጥልቅና ሰፊ ከሆነው ከምሥጢረ ቊርባን ትምህርት በመጠኑ ተመልክተናል፤ እንግዲህ ሥነ ምግባርን በመፈጸም ልንቆርብ ያስፈልጋል፤ መልካምነት የሚጀምረው ከቤታችን ነው፤ ክርስትናን ልንጠራባት ሳይሆን ልንኖራት ነውና የተቀበልናት፣መልካም ሥነ ምግባር ያለው ታዛዥና ጎበዝ፣ አስተዋዮች መሆን አለብን፡፡ ቸር ይግጠመን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!