ምሥጢረ ሥላሴ
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሚያዚያ ፲፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? የዐቢይ ጾምን ከጀመርን እነሆ ሰባተኛው ሳምንት ደረስን! በፍቅር አስጀምሮና አበርትቶ ለዚህ ያደረሰን እግዚአብሔር ይመስገን! እናንተስ በትጋት እየጾማችሁ እየጸለያች ነው አይደል? በርቱ!
ልጆች! በሰንበት ትምህርት ቤት በመግባትም ተማሩ፤ አገልግሉ፤ በቤተ እግዚአብሔር ማደግ መታደል ነው! ሌላው ድግሞ በዘመናዊ ትምህርታችሁም በርቱ! ሁለተኛውን የመንፈቀ ዓመት ትምህርት እየተገባደደ ነው! ምን ያህል ዕውቀትን እንዳገኛችሁ ራሳችሁን መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡ ትናንት ከነበራችሁ ላይ የተለየ ነገር ምን እንጨመራችሁ ሁል ጊዜ ራሳችንን ልትጠይቁ ይገባል፤ ምክንያቱም ወላጆቻችንን እኛን ለማስተማር በዕውቀት፣ በጥሩ ሥነ ምግባር ታንጸን እንድናድግ ብዙ መሥዋዕትነትን እየከፈሉልን ነው፤ ታዲያ የዚህ ሁሉ ድካማቸውና ምኞታቸው እኛ ጥሩ ቦታ እንድንደርስ ስለሚፈልጉ ነው፤ ስለዚህ ለማወቅ ለመለወጥ በርቱ፡፡ መልካም! አሁን ለዛሬ ወዳዘጋጀንላችሁ ትምህርት እናምራ፤ ባለፈው “ሥነ ፍጥረት” በሚል ርእስ ተምረን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ምሥጢረ ሥላሴን ስለምንማር ተከታተሉን!
ምሥጢር “አመሠጠረ ፣አራቀቀ፣ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ስውር ፣ረቂቅ” ማለት ነው፤ ምሥጢረ ሥላሴ ደግሞ ሦስትነት (ሦስት መሆን) ልዩ ሦስትነት ማለት ነው፤ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፮፻፷፱) ሦስትነት ማለት አንድነት ያለበት ሦስትነት ነው፡፡ ምሥጢር መሰኘቱ ደግሞ ለሚያምን ብቻ የሚነገር የሚገለጥ ስለሆነ ነው፤ረቂቅ የሆነ የአንድነት ምሥጢር ስላለው ምሥጢር ተብሏል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ፈጣሪያችን ቅድስት ሥላሴ አንድም ሦስትም ናቸው፤ ቅድስት ሥላሴ በስም በግብር በአካል ሦስት ናቸው፤ በአገዛዝ፣ በሥልጣን፣ በመለኮት፣ ይህንን ዓለም በመፍጠር ደግሞ አንድ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የሚለው የአንድነት ስም፣ሥላሴ ደግሞ የሦስትነት ስም ነው ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስም ሦስትነት ማለታችን “አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ” ነው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባቶቻችንን ቅዱሳን ሐዋርያትን እንዲያስተምሩ ሲልካቸው እንዲህ ብሏቸዋል፤ ‹‹… ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡›› (ማቴ.፳፰፥፲፱) የአካል ሦስትነት ደግሞ “ለአብ ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ ፣ፍጹም ገጽ አለው፤ ለወልድም ፍጹም አካል ፣ፍጹም መልክ ፣ፍጹም ገጽ አለው፤ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ ፣ፍጹም ገጽ አለው” ማለት ነው፡፡
ውድ እግዚአብሔር ልጆች! “መልክ፣ አካል፣ ገጽ” የሚባሉት ምን መሰላችሁ? ገጽ ማለት ከአንገታችን በላይ ያለው የሰውነታችን አካል የሚጠራበት ነው፤ መልክ ስንል ደግሞ እያንዳንዱን የሰውነታችንን ክፍል ማለት ነው፤ አካል ማታችን ደግሞ ከራስ ፀጉራችን እስከ እግራችን ጥፍር ድረስ ያለውን መላ ሰውነታችንን ያጠቃልላል፡፡
የቅድስት ሥላሴ የግብር ሦስትነት ግብር ማለት ሥራ ማለት ነው፤ የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረፅ ነው ፤ ወልድን ይወልደዋል፤ መንፈስ ቅዱስን ደግሞ ያሠርፀዋል፤ የወልድ ግብሩ መወለድ ሲሆን ከአብ ይወለዳል፤ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ ደግሞ መሥረፅ (መውጣት) ነው፤ ከአብ ይሠርፃል፡፡ ታዲያ ልጆች! “አብ ወልድን ወለደው፤ መንፈስ ቅዱስን አሠረፀው” ስንል ከእነርሱ ቀድሞ አልተገተኘም፤ ሦስቱም መቀዳደም የለባቸውም፡፡
ቅዱስ ጎርጎርዎስ የተባለ አባት እንደዚህ ያስተምረናል፤ ‹‹ለአብ የአባትነት ስም፣ የአባትነት ክብር አለው ፤ ለወልድም በባሕርይ ክብሩ ከአብ ሳያንስ የልጅነት ስም የልጅነት ክብር አለው፤ መንፈስ ቅዱስም እንዲህ በክብር አይለይም፤ ነገር ግን ተለውጦ አብ ወልድ አይባልም፤ በዚህ ጊዜ ተገኘ አይባልም፤ በመለኮት እንደ አብ እንደ ወልድ ነው እንጂ እስትንፋሳቸው ነውና ሦስቱም ትክክል ነቸው፡፡›› (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ምዕ. ፷፥፫)
የቅድስት ሥላሴን አንድነትና ሦስትነት በምሳሌ እንመልከት፤ በሥነ ፍጥረት ትምህርታችን በዕለተ ረቡዕ የተፈጠረችው ፀሐይ ሦስት ነገር አላት አካል አላት (የምናየው ክብ)፤ ከዚያ ደግሞ ብርሃን አላት፤ ሌላው ደግሞ ሙቀት አላት፤ ታዲያ ልጆች ፀሐይ ጠዋት ከምሥራቅ ስትወጣ አካሏም፣ ብርሃኗም፣ ሙቀቷም እኩል ነው የሚገኘው፤ ልክ እንደዚያም አብ ወልድን ወለደ ስንል መንፈስ ቅዱስን አሠረፀ ስንል ቀድሞ አልተገኘም አንድ ናቸው ማለት ነው፤ ይህ ረቂቅ የሆነ በሥጋዊ ዕውቀት ተመራምረን የማንደርስበት ምሥጢር ነው፤ ለዚህም ነው በመግቢያችን ላይ ምሥጢር ረቂቀቅ፣የማይመረመር ያልነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የቅድስት ሥላሴን አንድነት ደግሞ እንመልከት፤ ቅድስት ሥላሴ “በአገዛዝ፣ በሥልጣን፣ በመለኮት፣ ይህንን ዓለም በመፍጠር አንድ ናቸው፤” ቅዱስ አትናቴዎስ የተባለው አባታችን ፣ ‹‹አብ አምላክ ነው፤ ወልድ አምላክ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው፤ ግን ሦስት አማልክት አይባሉም፤ አንድ አምላክ እንጂ›› በማለት በሥልጣን አንድ መሆናቸውን አስተምሮናል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አትናቴዎስ ምዕ.፳፭፥፬፣፬)
ሌላው ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የተባለው አባታችን እንዲህ መስክሯል፤ ‹‹አንድ አምላክ ብለን የምንሰግድላቸው ሥሉስ ቅዱስ በባሕርይ በመለኮት አንድ እንደሆኑ እናምናለን፤ እሊህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ እሊህም ሦስቱ አካላት በገጽ ፍጹማን እንደሆኑ በሥልጣን በባሕርይ፣ከዘመን አስቀድሞ በመኖር፣ በጌትነት፣ በመፍጠር፣ ሳይለወጡ በመኖር አንድ እንደሆኑ እናምናለን፤›› (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ምዕ.፶፪፥፩)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ሰፊና ጥልቅ ነው፤ ለእናንተ ግን በመጠኑ ጻፍንላችሁ፤ በቀጣይ ደግሞ ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ እንማራለን፤ ቸር ይግጠመን !!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!