ምሥጢረ ሆሣዕና
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
መጋቢት ፳፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
የዐቢይ ጾም ስምንተኛው ሳምንት ‹‹ሆሣዕና›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ተቀምጦ በክብር፣ በምስጋና፣ በዝማሬ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱን የምንዘክርበት በዓል ነው፡፡ በዚህ ዕለት ከዋይዜማው ጀምሮ በመንፈቀ ሌሊት፣ በነግህ እና በሠርክ ጌታችን ወደ ኢሩሳሌም የመግባቱን ምሥጢር፣ ከሕዝቡ የቀረበለትን ምስጋና እንደዚሁም ኢየሩሳሌም በግርማው መደንገጧን የሚያስረዳ ቃለ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያናችን በሰፊው ይነገራል፡፡
ይህ ምሥጢርም በቅዱሳት መጻሕፍት በልዩ ልዩ መንገድ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በዚህ ዝግጅት፣ በማቴዎስ ፳፩፥፩-፲፩፤ በማርቆስ ፲፩፥፩-፲፤ በሉቃስ ፲፱፥፳፰-፵ እና በዮሐንስ ፲፪፥፲፪-፲፭ በተጻፈው ኃይለ ቃል መሠረት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጁትን አንድምታ ትርጓሜ መነሻ በማድረግ ምሥጢረ ሆሣዕናን (ጌታችን በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም የመግባቱን ምሥጢር) የሚያስገነዝብ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን ትከታተሉ ዘንድ በአክብሮት ጋበዝናችሁ!
ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በልዩ ልዩ አገሮች እየተዘዋወረ ቃሉን በማስተማር ሕገ ወንጌልን መሥርቷል፤ ብዙዎችንም ለመንግሥቱ አቅርቧል፡፡ ቃሉን ለመስበክ ከተዘዋወረባቸው ቦታዎች አንዷ ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት፡፡ የመሲሑን መምጣት ማለትም የእግዚአብሔርን ሰው መኾን የሰሙና ያመኑ እስራኤላውያን ክርስቶስን በዓይነ ሥጋ ለማየት ይጓጉ፣ መምጣቱንም ይጠባበቁ ነበር፡፡
አመጣጡ ግን እነርሱ በጠበቁት ልዩና ተአምራዊ መንገድ ሳይኾን በትሕትና ተፈጸመ፡፡ ሲወለድ በከብት በረት፤ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባም በአህያ ተቀምጦ ለእስራኤል ተገለጠ፡፡ ሰማይ ዙፋኑ፣ ምድር የእግሩ መረገጫ የኾነ ጌታ መላእክቱን አስከትሎ፣ በመባርቅትና በነጐድጓድ ታጅቦ ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ የትሑታን ጌታ መኾኑን ለማጠየቅ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በዚህ ጊዜ ኢየሩሳሌም ተረበሸች፤ ደነገጠች፡፡ አምላክን ባልጠበቀችው አኳኋን ተገልጦ አይታዋለችና፡፡
ወደ ጥንተ ነገሩ እንመለስና ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ በተቃረበ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱን በፊታቸው ወደሚገኝ አገር ሔደው ከውርንጫዋ ጋር ታሥራ የሚያገኟትን አህያ ፈተው እንዲያመጡለት አዘዛቸው፡፡ የሰው ልጅ ከማዕሠረ ኀጢአት (ከኀጢአት ማሠሪያ) የሚፈታበት ጊዜ ደርሷልና፡፡ ይኸውም አምላካችን የመጣው የዓለምን ኀጢአት ለማስወገድ መኾኑን የሚያጠይቅ ነው፡፡ ‹‹ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢአተ ዓለም፤ የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ እነሆ የእግዚአብሔር በግ!›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዮሐ. ፩፥፴፮)፡፡
አህያዋንና ውርንጫዋን ‹‹ለምንድን ነው የምትፈቷቸው?›› ብሎ የሚጠይቅ ካለም ‹‹‹ጌታቸው ይሻቸዋል› በሉ፤ ያንጊዜ ያሰናብቷችኋል (ይተዋችኋል)›› አላቸው፡፡ በተፈጥሮ ጌታቸው ነውና ማለትም ፈጥሯቸዋልና ‹‹ጌታቸው›› አለ፡፡ ደግሞም እርሱ እናቶችን ብቻ ሳይኾን ልጆችን ጭምር ወደ ቤቱ ማቅረብ ይፈልጋልና፡፡ ይህም ጌታችን በኀጢአት ማሠሪያ የተያዙ ኀጢአተኞችን ለመፍታት ከፈቀደ ‹‹ለምን ይህን ታደርጋለህ?›› ብሎ የሚቃወመው አለመኖሩን ያስገነዝባል፡፡
አህያዪቱንና ውርንጫዋን በተመለከተ ማቴዎስ ሁለቱንም፤ ማርቆስ ደግሞ ውርንጫዋን ብቻ ነው የጠቀሱት፡፡ የማቴዎስን አጻጻፍ መከተል ለታሪኩ እንደሚያመች፣ ይህም እንደማይጣላና የምሥጢር ተፋልሶ እንደማያመጣ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ይተረጕማሉ፡፡ ለዚህ ማስረጃ ሲያቀርቡም ማርቆስ አንድ ማለቱ (ውርንጫዋን ብቻ መጠቀሱ) ለመናገር በቂ ነው ብሎ በማሰቡ እንደ ኾነ፤ አንድም ማቴዎስ የሕዝብም (ያመኑ) የአሕዛብም (ያላመኑ) መምህር በመኾኑ ሁለቱንም (አህያዬቱንና ውርንጫዋን) እንደ ጠቀሰ፤ ማርቆስ ግን የአሕዛብ እንጂ የሕዝብ መምህር ስላልኾነ የአሕዛብን ምሳሌ ብቻ (ውርንጫን) እንደ አወሳ ሊቃውንቱ ያስረዳሉ (ማር. ፲፩፥፫)፡፡
ይህ ዂሉ የተደረገውም ማለት ጌታችን በአህያዪቱና ውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት የፈቀደውም ‹‹አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ኾኖ በአህያም፥ በአህያዪቱም ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፤›› ተብሎ የተነገረው ቃለ ትንቢት የሚፈጸምበት ጊዜ ስለ ደረሰ ነው (ዘካ. ፱፥፱)፡፡ ትርጓሜ ወንጌል በሐተታው ወለት (ልጅ) የተባለች እስራኤል፤ ጽዮን ደግሞ ኢየሩሳሌም መኾኗን ያብራራል፡፡ አንድም ወለትን (ልጅን) እንዳለ መስሎ ጽዮን የተባለች ሕግ መኾኗን ይጠቅሳል፡፡ የምሳሌዉን ትርጕም ሲያስረዳም እናት ልጆቿን ሠርታ፣ ቀጥታ እንድታሳድግ ሕግም ሕዝቡን ሠርታ፣ ቀጥታ እንደምታኖር ይናገራል (ማቴ. ፳፩፥፬-፭)፡፡
ወደ ታሪኩ ስንመጣ ደቀ መዛሙርቱም እንደ አዘዛቸው አህያዬቱንና ውርንጫዋን ፈተው ለጌታችን አመጡለት፡፡ ልብሳቸውንም በጀርባዋ ላይ ጐዘጐዙለት፡፡ ኮርቻ ይቈረቍራል፤ ልብስ አይቈረቍርም፡፡ ጌታችንም የማትቈረቍር ሕግ (ሕገ ወንጌልን) መሥራቱን ለማጠየቅ ልብስ ጐዘጐዙለት፡፡ አንድም ልብስ ነውርን ይሠውራል፤ እርሱም ከባቴ አበሳ (በደልን በሥውር ይቅር የሚል) አምላክ ነውና ልብስ ጐዘጐዙለት፡፡ ጌታችንም በጥበቡ በሁለቱም አንድ ጊዜ ተቀምጦባቸዋል፡፡
በትርጓሜ ወንጌል እንደ ተጠቀሰው ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ ያለው ርቀት ዐሥራ ስድስት ምዕራፍ ይኾናል፡፡ ጌታችን ዐሥራ አራቱን ምዕራፍ በእግሩ ተጕዞ፤ ሁለቱን በአህያዋ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ሔዷል፡፡ በውርንጫዋ ላይ ተቀምጦ ደግሞ ቤተ መቅደስን ሦስት ጊዜ ዞሯል፡፡ ይህም የሦስትነቱ ምሳሌ ነው፡፡ ዐሥራ አራቱን በእግሩ መሔዱም ዐሥሩ፣ የዐሠርቱ ትእዛዛት፤ አራቱ የአራቱ ኪዳናት ማለት የኪዳነ ኖኅ (የኖኅ ኪዳን)፣ የክህነተ መልከ ጼዴቅ (የመልከ ጼዴቅ ክህነት)፣ የግዝረተ አብርሃም (የአብርሃም መገረዝ) እና የጥምቀተ ዮሐንስ (የዮሐንስ ጥምቀት) ምሳሌዎች ናቸው፡፡ አንድም አምስት ሺሕ አምስት መቶዉን ዓመት በአራት በአራት መቶ ቢከፍሉት ዐሥራ አራት ሊሞላ አንድ መቶ ይጐደለዋል፡፡ ዐሥራ አራቱ ምዕራፍ፣ ይህ ዘመን (አምስት ሺሕ አምስት መቶዉ) ሲፈጸም አምላክ ሰው እንደ ኾነ ያጠይቃል፡፡
ጌታችን በአህያ መቀመጡ ስለ ምን ነው ቢሉ ትንቢቱ፣ ምሳሌው ሊፈጸም ነው፡፡ እርሱ ባወቀ (በአምላካዊ ጥበቡ) ትንቢቱን አስቀድሞ አናግሯል፤ ምሳሌውንም አስመስሏል፡፡
- ትንቢቱ፡- ‹‹ሠረገላዉንም ከኤፍሬም፥ ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም ያጠፋል፤›› ተብሎ አስቀድሞ ተነግሯል (ዘካ. ፱፥፲)፡፡ የትንቢቱ ፍጻሜ ሲደርስ ጌታችን በፈረስና በሠረገላ ሳይኾን በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡
- ምሳሌው፡- ቀድሞ ነቢያቱ ዘመነ ጸብዕ (የጦርነት ዘመን) የሚመጣ እንደ ኾነ በፈረስ ተቀምጠው፣ ዘገር ነጥቀው (የጦር ትጥቅ ይዘው)፤ ዘመነ ሰላም የሚመጣ እንደ ኾነ ደግሞ በአህያ ተቀምጠው፣ መነሳንስ ይዘው ይታያሉ፡፡ ጌታችን የሰላም አምላክ ነውና የሰላም ዘመን መድረሱን፣ ሰላምን ይዞ መምጣቱን ሲያስረዳ በአህያ ላይ ተቀምጦ ታየ፡፡
ምሥጢሩስ ምንድን ነው ቢሉ በአህያ ላይ የተቀመጠ ሸሽቶ ማምለጥ፣ አሳዶ መያዝ አይችልም፡፡ ጌታችንም ለሚፈልጉት (ለሚያምኑበት) እንደሚገኝ፤ ለማይፈልጉት (ለሚክዱት) እንደማይገኝ ሲያመላክት በአህያ ላይ ተቀምጦ ታየ፡፡ አንድም በንጹሓን መሃይምናን ላይ አድሮ እንደሚኖር ሲያጠይቅ ነው፡፡
አህያ፣ የእስራኤል ምሳሌ ነው፤ አህያ፣ የሠረገላ ቀንበር መሸከም እንደምትችል እስራኤልም ሕግ መጠበቅ የለመዱ ናቸውና፡፡ ውርንጫ፣ የአሕዛብ ምሳሌ፤ ውርንጫ፣ ቀንበር መሸከም እንደማትችል አሕዛብም ሕግ መጠበቅ ያልለመዱ ናቸውና (አልለመዱምና)፡፡ በሌላ በኩል አህያ፣ የኦሪት፤ ውርንጫ የወንጌል ምሳሌዎች ናቸው፡፡ አህያ የሠረገላ ቀንበር መሸከም እንደ መልመዷ ኦሪትም በዘመኑ የተለመደች ሕግ መኾኗን፤ ውርንጫ ቀንበር መሸከም እንዳለመልመዷ ወንጌልም በዘመኑ ያልተለመደች (አዲስ) ሕግ መኾኗን ያመላክታል፡፡
ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ብዙ ሕዝብ ‹‹እንኳን አንተ፣ የተቀመጥህባት አህያም መሬት መርገጥ አይገባትም›› ሲሉ ልብሳቸውን በጎዳናው ላይ አንጥፈውለታል፡፡ ሌሎችም ቅጠል እየቈረጡ ከመንገድ ያነጥፉ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን መያዝ እንደዚህ ያስከብራል፡፡ ከእርሱ መለየት (እርሱን መካድ) ግን ያዋርዳል፡፡ እርሱን በሕይወታችን ላይ ካስቀደምን በእርሱ ምክንያት ብዙዎች ያከብሩናል፡፡
ሕዝቡ ለጌታችን ልብስና ቅጠል ማንጠፋቸው ከኢዩ የንግሥና ታሪክ ጋር ተመሳሳይ ኾኖ ይጠቀሳል፡፡ ኢዩ ከእስራኤል ነገሥታት አንዱ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ ለንግሥና ሲመረጥ ቅብዐ መንግሥት የተቀባው በድንገት ነው፡፡ ታሪኩም እንዲህ ነው፤ ነቢዩ ኤልሳዕ ከደቂቀ ነቢያት አንዱን ጠርቶ ‹‹ቀርነ ቅብዑን ይዘህ ሒድ፤ ኢዩን ቀብተህ አንግሠውና ፈጥነህ ና፤ ከሰው ጋር አትነጋገር›› ብሎ ላከው፡፡ መልእክተኛውም የኤልሳዕን ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ኢዩ ሔደ፡፡ ኢዩንም በአደባባይ ተቀምጦ ከባልንጀሮቹ ጋር ሲጫወት አገኘውና መልእክት እንዳለው ነገረው፡፡ ኢዩም ‹‹ከእኛ ነው ከሌላ?›› ብሎ ቢጠይቀው ‹‹መልእክት እንዳደርስ ወደ አንተ ተልኬ መጥቻለሁ›› አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ወደ እልፍኝ ይዞት ገባ፡፡ በዚያም ‹‹ከመዝ ይቤ አምላከ እስራኤል ‹ቀባዕኩከ ትንግሥ ላዕለ ሕዝብየ እስራኤል፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‹በሕዝቤ እስራኤል ላይ ትነግሥ ዘንድ ቀባሁህ›!›› ብሎ የንግሥና ቅብዓትን ቀብቶት ተመለሰ፡፡ ኢዩ ወደ ባልንጀሮቹ በሔደ ጊዜም ‹‹መልእክተኛው ምን አለህ? ነገረን?›› ብለው አፋጠጡት፡፡ እርሱም ‹‹ትነግሣለህ ብሎ ቀብቶኝ ሔደ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹እኛስ ሌላ ምን እንሻለን?›› ብለው ከፊሉ ምንጣፍ አንጥፈውለታል፤ ከፊሉ መጋረጃ ጋርደውለታል (፪ኛ ነገሥት ፱፥፩-፲፩ )፡፡
ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባም በዚህ አምሳል እስራኤላውያን ልብሳቸውን በጎዳናው ላይ አንጥፈዋል፡፡ ቅጠል እየቈረጡ ያነጠፉም ነበሩ፡፡ ቅጠሉ ሰሌን ከኾነ አብርሃም ይስሐቅን፣ ይስሐቅ ያዕቆብን፣ በወለዱ ጊዜ፤ እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ፤ ዮዲት ሆሎሆርኒስን ድል ባደረገች ጊዜ ሰሌን ቈርጠው ይዘው ማመስገናቸውን ያስታውሳል፡፡ ደግሞም ሰሌን እሾኽ እንዳለበት ዂሉ ጌታችንም የኃይል፣ የማሸነፍ ምልክት (ሥልጣን) ያለው አምላክ መኾኑን ያመላክታል፡፡ ሰሌንን እሳት አይበላውም፤ ለብልቦ ይተወዋል እንጂ፡፡ ይህም የጌታችን መለኮታዊ ባሕርይ የማይመረመር መኾኑን ያስገነዝባል፡፡
ቅጠሉ ተምር ከኾነ ተምር ልዑል (ትልቅ)፤ ፍሬው አንድና በእሾኽ የተከበበ እንደ ኾነ ዂሉ ‹‹አንተም ልዑለ ባሕርይ (በባሕርይህ ከፍ ከፍ ያልህ) ነህ፤ ባሕርይህ አንድ ነው፤ አይመረመርም›› ሲሉ የተምር ቅጠል አንጥፈውለታል፡፡ ቅጠሉ ዘይት ነው ያሉ እንደ ኾነ ዘይት ጽኑዕ (የጸና)፣ ብሩህ (የሚያበራ)፣ መሥዋዕት ነው፡፡ እስራኤል የዘይት ቅጠል ማንጠፋቸውም ጌታችን ጽኑዐ ባሕርይ (ባሕርዩ የጸና)፣ ብሩህ እንደ ኾነ እንደዚሁም ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ዓለምን እንደ አዳነ ያመላክታል፡፡ በዕለተ ሆሣዕና በቤተ ክርስቲያን የዘንባባ ቅጠል የሚታደለውም ይህንኑ ምሥጢር ለማስታወስ ነው፡፡
ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ በገባባት በዚያች ዕለት በእስራኤል የነበረው ደስታ የተለየ ነበር፡፡ ሕፃናት ሲመሩ አረጋውያን እየተከተሉ፤ አረጋውያን ሲመሩ ሕፃናት እየተከተሉ፤ ነቢያት ሲመሩ ሐዋርያት እየተከተሉ፤ በዐሥር ሺሖች የሚቈጠር ሕዝብ ጌታችንን ከፊትና ከኋላው ከበውት፤ ጻድቃን በቀኙ፣ ተነሳሕያን (ንስሐ የሚያስፈልጋቸው) በግራው አጅበውት እነዚህ ዂሉ ‹‹ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር ሆሣዕና በአርያም፤ ለዳዊት ልጅ መድኀኒት መባል ይገባዋል፤ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ (አምላክነቱን ገልጦ) በእግዚአብሔር ስም የመጣ እርሱ (ክርስቶስ)፣ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት፤ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን የሚያድል በሰማይ ያለ መድኀኒት እርሱ ነው›› እያሉ አመስግነውታል (መዝ. ፻፲፯፥፳፬-፳፮)፡፡
ከፈሪሳውያንና ከሕዝቡ መካከልም በዚህ ልዩ ምስጋና እና ደስታ ተበሳጭተው ‹‹መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ተቈጣቸው›› አሉት፡፡ ጌታችንም እነርሱ ዝም ቢሉ ድንጋዮች አፍ አውጥተው የሚያመሰግኑት አምላክ መኾኑን ነግሮ አሳፍሯቸዋል፡፡ በዕለተ ሆሣዕና ሕዝቡ ዂሉ ለጌታችን የቀረበዉን ምስጋና እና የነበረዉን ደስታ ዓይተው ተገረሙ፡፡ ከተማዪቱም ‹‹በዚህ አኳኋን የተገለጠ ይህ ማነው?›› ብላ፤ አንድም የፊቱ ብርሃን ፀሐይን ሲበዘብዝ (ከፀሐይ በላይ ደምቆ ሲያበራ) አይታ፤ የሕፃናትን ምስጋና ሰምታ ተረበሸች፤ ታወከች፤ ደነገጠች፡፡
በቀር እርሱን ዓይቶ ማን ተረጋግቶ ይቆምና! ጌታችን በትሕትና በተገለጠ ጊዜ ግርማው ይህን ያህል ካስደነገጠ በግርማ መለኮት፣ በክበበ ትስብእት ዳግም ለፍርድ ሲመጣ እንዴት ያስፈራ ይኾን? ያን ጊዜ የቅጣት ፍርድ ከመስማትና ከመደንገጥ እንድን ዘንድ ከኀጢአት ተለይተን በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን እንኑር፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡