ማይኪራህ
በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
ግንቦት ፲፩፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ከሌሊት ወፍ በመዓልቱ:
…… እልፍ እንቁላል ሊሰበሰብ፣
የወንዱ ጽንስ እንዲገፋ
…… ከበቅሎው ወተት ሊታለብ፤
ከማር ቀፎ የዝንብ መንጋ
…… አውሬው ጓዳ ገብቶ እንዲያድር፣
የተፈጥሮ ሕጉን ስቶ
…… ያለቦታው እንዲሰደር፤
ከጅቡም ለማዳ
ከአህያውም ፍሪዳ
ለአሣው ጎጆ በወፍ መንገድ
የጭስ ምኞት በጉም እቅድ
«ያንተ ያለህ!»
የነገውስ መታተር ከዛሬ ይልቅ እንዳይከር
ምን አለ? መጪው በድሮ ቢቀየር!
በእንተ ስማ ለጥበብ… በእንተ ስማ ለዜማ…
እያያችሁ አትለፉኝ! በአበው በእማት ጩኸቴ ይሰማ
እባካችሁ በጀ በሉኝ! ዛሬ በትናንት ይቀማ!
ቁራሽ አይደለም ከገበታው ትራፊ
ከመጠጡም ለእርካታ ከጨርቃችሁም እራፊ
ከንፈርን ከምትመጥጡበት ከርኅራኄው እላፊ
ይልቅ …
የጉሮሮዬን ንቃቃት የጩኸቴን ጩኸት ለዛ
በደረቅ ስልት እሪታ አንደበቴ ደክማ ፈዛ
አንዲት ነገር ተለመኑኝ ታካች ልቤ አደብ ይግዛ
አልቦ እምቅድሜሁ ወአልቦ እምድህሬሁ
እስኪ ጥሩልኝ ጸውኡ ሊተ ኪያሁ
ያሬድ ዘኢትዮጵያ ጥዑመ ልሳን ዝማሬሁ
በእንተ ስማ ለጥበብ… በእንተ ስማ ለዜማ…
እያያችሁ አትለፉኝ በአበው በእማት ጩኸቴ ይሰማ
እባካችሁ በጀ በሉኝ ዛሬ በትናንት ይቀማ
ዋይ ዜማ… ዋይ ዜማ … ዋይ ዜማ
ከየትኛው በአት ከየትኛው ዋሻ ከወደየት ይሰማ?
አይቴ ብኄራ ለዜማ ወአይቴ ብኄራ ለጥበብ
የመላእክቱን ረቂቅ ሕብስት ሰምቶ ጆሮ እንዲጠግብ
ወርቅ አቅፈው ያፈሩት ያባቶቼን ጉያ ሳስብ
ባንቺ ሆዬ ባቲ በአንባሰል ትዝታ መዝሙሩ ሲቀመር
የኖታ ስኬል ሜዠር በሰልፍ ሲደረደር
ባስረሽ ምችው ዝላይ በእስክስታው ዳንኪራ አቋቋም ሲቀየር
የሞዛርት ሜሎዲ ዜማ ቤት ሲሻገር
በሊቁ ያሬድ ርስት ቬትሆቨን ሲዘከር
ታሪክ እንዳይሰማ በዛሬ እንዳናፍር
ከመቃብር ዘልቆ አጥንት እንዳይሰብር
ዘንድሮው በአምናው … ዛሬ በትናንቱ… አሁን በቅድሙ ምን አለ ቢቀየር!
ተዘከሩኝ…
በእንተ ስማ ለጥበብ… በእንተ ስማ ለዜማ…
እያያችሁ አትለፉኝ በአበው በእማት ጩኸቴ ይሰማ
እባካችሁ በጀ በሉኝ ዛሬ በትናንት ይቀማ
በሉላዊነት ጥላ እርከን ሥር: ነፃ ገበያ ተመሥርቶ
በባህል ወረርሽኝ ሲራቆት: አባቱ የሰጠውን ትቶ
የዐባይ ልጅ በውኃ እጦት: በበረሃ ሲዳክር
የላጭ ልጅ ጠጉሩ አድጎበት: በቅማል ሲወረር
ከማይናገር ከብቱ
ከማይራገጥ ወተቱ
… ለባዕዳን ሲገበር ፤
የደገፈውን ክንድ አቃልሎ ነፋስ በገፋው ሲዋልል
ምነው ከማይኪራህ ተጎንጭቶ ለማስተዋል መንቃት ሲችል
የሕርያቆስ ቅዳሴ: የኤፍሬም ውዳሴ ቃል
ይኼ ሁሉ ቀለም…
ይኼ ሁሉ ቅኔ
……ይኼ ሁሉ ፊደል
ከነሆሜር ጥበብ ከሼክስፒር ሲያይል
ጥዑም ማጽኛ ጠፍቶ ከዜማ ሲራቆት በመዝሙር ሲገደል
ምን ይል ቅዱስ ያሬድ? ምን ይል አባ ጊዮርጊስ? ምን ይል አባ ጽጌ ድንግል?
በእንተ ስማ ለጥበብ… በእንተ ስማ ለዜማ…
በእንተ ስማ ለጥበብ… በእንተ ስማ ለዜማ…
በእንተ ስማ ለጥበብ… በእንተ ስማ ለዜማ…