ማዕከሉ ዐውደ ጥናት ሊያካሂድ ነው
የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ
የጥናትና ምርመር ማዕከል በሁለት ታላላቅ ርእሶች ላይ ያዘጋጀውን ዐውደ ጥናት የካቲት 23 ቀን 2005 ዓ.ም በብሔራዊ ሙዚየም አዲሱ አዳራሽ ውስጥ እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡
የጥናትና ምርምር ማዕከሉ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሰይፉ አበበ ለመካነ ድራችን በሰጡት መገለጫ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ የዓድዋ ድልና አንድምታው፤ እንዲሁም በጦርነቱ የተዘረፉ ቅርሶችን ከማስመለስ አንጻር የቤተ ክርስቲያኒቷ ድርሻ በሚሉ ሁለት ርዕሶች ላይ ትኩረት አድረጎ የሚቀርብ ነው፡፡” ካሉ በኋላ የዐውደ ጥናቱ የትኩረት አቅጣጫዎችን ሲጠቁሙ “ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት እንዳትገዛ፣ ነጻነቷ የተጠበቀ ሉአላዊት ሀገር እንድትሆን ከጦርነቱ ጀምሮ እስከ ድሉ የነበራትን ሚና፣ እንዲሁም በዓድዋና በማይጨው በልዩ ልዩ ጊዜያት በወራሪዎች የተዘረፉ ቅርሶችን ከማስመለስ አንጻር የቤተ ክርስቲያኒቱ ድርሻን ማመላከት የጥናቱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
በስተመጨረሻም ምክትል ዳይሬክተሩ ሁሉም ምእመናን ቅዳሜ የካቲት 23 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ በሚከናወነው በዚሁ ዐውደ ጥናት ላይ ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡