ማኅበራዊ ሕይወታችን!

ክፍል አንድ

በቃሉ እሱባለው

ሕይወታችንን ስናስብ የሌሎችን በሕይወት መቆየት እንጠባበቃለን። በጋራ ዓለም ላይ አብሮ የጋራ ዓለምን ማቅናት ላይ እንድንመረኮዝ እንገደዳለን። በሕገ ተፈጥሮ ውስጥ ለራሱ የተፈጠረ ፍጥረት የለም። ከእሑድ እስከ ዓርብ ያሉ ፍጥረታት እርስ በራሳቸው ተመጋጋቢ ቢሆኑም ሁሉም ግን ስለ አዳም ተፈጥረዋል። አንዳንዶቹ ለምግበ ሥጋ ምግበ ነፍስ፣ አንዳንዶቹ ለአንክሮ ለተዘክሮ፣ አንዳንዶቹ ለመድኃኒትነት፣ አንዳንዶቹ ለምስጋና፣ አንዳንዶቹ አዳም መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርባቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ ለሌላ ለተለያየ ነገር ተፈጥረዋል። እነዚህ ሁሉ ለራሳቸው ሲባል አልተፈጠሩም።

በዓርብ ዕለት የተፈጠረው አዳም ብቻውን አልተፈጠረም። “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” (ዘፍ ፩÷፳፯) እንዲል። እርሱ ራሱም ቢሆን ለራሱ የተፈጠረ አይደለም። ታዲያ ስለ ምን ተፈጥሯል ቢባል፣ ስለ እነዚህ ምክንያቶች ተፈጥሯል። የመጀመሪያው በምስጋና እንዲኖርና መንግሥቱን እንዲወርስ፣ በምስጋናም እንዲኖር፣ ሁለተኛ ከእሑድ እስከ ዓርብ ዕለትም ከእርሱ ጋር ለተፈጠሩት ፍጥረታት ገዥ፣ ጠባቂ ለመሆን ተፈጥሯል።

እነዚህን ምክንያቶች ብናይ እንኳን ፍጥረተ ዓለም በራሱ ለራሱ ብቻውን ህልውና የለውም። ፈጣሬ ዓለማት፣ እግዚአ አጋዕዝት እግዚአብሔር ፍጥረቱን አሳምሮ፣ አስውቦ እና አንዱን ለአንዱ ምቹ እና ተስማሚ እያደረገ ፈጥሯል። ያ  ድንቅ ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት በየነገዱ እና በየዘሩ አንዱ ለሌላው መኖር ተፈጥሮአዊ የህላዌ ጥያቄን የሚመልስ ነው።

ፍጥረታዊ ሕግ እና ሥርዓትን ሳንለቅ ሃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ መረዳቱን እንዳለ ከፊት አድርገነው ወደ ኋላ ሳይንሳዊ ሥርዓቱን እና መርሑን ለመዳሰስ ብንሞክር በባዮሎጂካል (ሥነ ሕይወታዊ) የሥነ ተፈጥሮ ምግብ ሰንሰለት እና የምግብ መረብ ላይ አንዱ ፍጥረት ለሌላው ተፈጥሮአዊ ተጋሪው ይሆናል።

በሰው ሥርዓተ ሕይወትም ውስጥ ይህን እናገኛለን። አንዱ የተፈጠረው ለሌላው ነው። አዳም ለሔዋን ሔዋንም ለአዳም። አንዱ ሲስት ሌላውን እንዲያርም፣ አንደኛው በመድከም ሲክድ ሌላኛው በጥንካሬው ርቱዓዊነትን (ቅን የሆነውን) እንዲያስተምረው እንጂ አንደኛው ሲወድቅ ሌላኛው መስፈንጠሪያ ጉልበት እንዲያገኝ፣ ድሃው በማጣቱ ውስጥ የሀብታሙን ከልክ ማለፍ እያየ በእግዚአብሔር ላይ ዐመጽ እና ክህደትን እንዲያመጣ፣ ትልቁ በቅድስና እና በሃይማኖት ሲበረታ ትንሹ በክህደት ወጥመድ እንዲሸበብ፣ ጎረቤት በሀብት ማማ ላይ ለመድረስ የባለ እንጀራውን የድህነት ጉድጓድ እየማሰ እንዲኖር አይደለም። ከራስ የተለየ ሰውነት የለምና። ለዚህ ነው ክርስቶስ “እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ እናንተ ደግሞ ቅርንጫፎች ናችሁ” ያለው። (ዮሐ.፲፭፥፭) የወይኑ ግንድ ክርስቶስ ነው። ቅርንጫፎቹ ደግሞ የሰው ልጆች ነን። ከአካሉ የበቀሉ ቅርንጫፎች በቅርንጫፍነታቸው ውፍረት እና ቅጥነት አዝነው እኛ ቀጫጭኖች ተቆርጠን እንውደቅ ወይም እንድረቅ፣ ወፍራሞቹ ደግሞ የውፍረታችንን መጠን የቀጫጭኖቹ መብዛት ያቀጭጨናል እና እኛ የበለጠ ይገባናል ሳይሉ በየወገናቸው ጸንተው አንዳቸው ለሌላቸው ጠበቃ እና ውበት ሆነው እንዲኖሩ፣ እኛ በክርስቶስ አንድ ቅርንጫፍ በመሆን የቆምን እንዲሁ በጠበቃ እና በጌጥ የተዋበ የአካል ክፍል ውስጥ መኖር እንዲገባን እናውቃለን።

ቅዱስ ጳውሎስም በመጀመሪያይቱ የቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ ክርስቶስን እኛ በክርስቶስ አንድ አካል እንደሆንን እርሱ ራሳችን ሲሆን እኛ ደግሞ የአካል ክፍሎች እንደሆንን ይመሰክራል። “አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል።….. እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ።” (፩ኛ ቆሮ ፲፪፥፲፪-፲፫፣፳፯)

አካል ከሌለ ብልቶቻችን አይኖሩም። ሐዋርያው እንደ ነገረን እነዚህን ብልቶች ብናይ እግር በደከመ ለእጅ፣ ለሆድ፣ ለዓይን ይተርፋል። ሌላውም እንዲሁ። እንዲያውም አንድ ሀገራዊ ወግ ጠቅሶ ማለፍ ነገራችንን ያጎላዋል።

በአንድ ወቅት ጭንቅላት (አእምሮ)፣ ዓይን፣ እጅ፣ ሆድ እና እግር ለስብሰባ ይቀመጣሉ። በስብሰባው ሁሉም የየራሱን ጥቅምና አስፈላጊነት የበላይነቱን የሚያሳይ ሐሳብ ይዞ ቀረበ። ከአእምሮ ጀምሮ እስከ እግር ድረስ የየራሳቸውን ከፍተኛ ተፈላጊነት እያጎሉ የሌላውን የበታችነት እያጣቀሱ መናገር ጀመሩና ሁሉም ንግግር አደረጉ። በዚህ መሐል ንግግር ያላደረገው ሆድ ነበር። እርሱም ሁሉን ከሰማ በኋላ ፍርዱን ተቀበለ። ረብ  የለሽ መሆኑን በየኑበት፤ ሆድም ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ምግብ ላለመብላት ወሰነ። በውሳኔው የጸናው ሆድ ለቀናት ከምግብ ታቀበ። ባለመብላት ቀጣቸው። ቀናት ሲነጉዱ አእምሮ እየደከመ፣ ጉልበት እየተልፈሰፈሰ፣ እጅ እያጠረ፣ ዓይን እየዛገ ሲመጣ ለውይይት ጉባኤ ጠሩ። ሆድም  በአቋሙ ነበረ። ግን የውሳኔው ብይን ሁሉም በአንድነት “መካተቻችን” አንዳችን ለአንዳችን በሕይወት እንድንኖር፣ በተስፋ እንድንጓዝ የምንሆነው በአንተ ነውና በጉባኤው ፊት እንድትበላ ወስነናል፤የሚል ፍርድ ፈረዱለት።

በራሱ ጸንቶ መቆም የሚቻለው የአካል ክፍል የለም። አንዱን ገፍቶ ሌላውን ከፍ አድርጎ መኖር ይቻል ይመስላል እንጂ አይሆንም። አንዳችን ለሌላችን ሌላችንም ለአንዳችን እናስፈልጋለን። እንደ ሆድ አንበላም ብሎ ከብዙዎቹ ውስጥ አንዱ ተግባሩን ቢያቆም በዙዎች መኖር ይከብድናል።

ታችኛው ሰፈር በላይኛው ሰፈር ከፍ ማለት የሚረበሽ ከሆነ፣ የላይኛው ሰፈር ወደ ታችኛው ሰፈር የሚያሰጥም ጎርፍ መልቀቁ አይቀርም። የተለቀቀው ጎርፍ የታችኛውን ሰፈር ሲሸረሽር የላይኛው መሠረት አብሮ ይደረመሳል። እናም በመከራችን እና በችግራችን ጊዜ የሚደርሱ ጎረቤቶች የመከራውን ውኃ የሚቀዱልን ሰዎች ያስፈልጉናል።

ኢትዮጵያዊያን በታሪካችን የመልካም ሰብእና ባለ ቤቶች ነን። ዓለም ስለ መልካምነታችን ተደንቆ ጽፎአል፤ መስክሯል። “ክፉ ነገር በሀገራቸው የተጠላ ነው። ርኅራኄያቸው እንደ እግዚአብሔር ነው” ተብሎ የተነገረልን በቸርነት እና በርኅራኄያችን ከእግዚአብሔር ጋር የተመሳሰልን ኩሩ ሕዝቦች ነበርን!። (የዓለም ታሪክ ጸሐፊው ሄሮዳተስ) ዛሬስ? ያ ትውልድ እየተባለ የሚነገርልን እኛ እንሆንን?

እስኪ ወደ ትናንት እንመለስ! ትናንትና በአንድ መሶብ በልተን ተጎራርሰናል። ቤታችን እንጀራ አልቆ ከጎረቤት እስከምንጋግር ድረስ ተባብለን ተበዳድረናል። እናት ልጆቿን ያለ ሥጋት ለጎረቤት እናት አደራ ጥላ ወጥታ ስትሄድ የአንድን እናት ጡት የተለያየ ቤተሰብ ልጆች ጡት እየተቀያየርን ጠብተን አድገናል። ዛሬስ? ትናንት ወለጋ ያለው ኦሮሞ ጎጃም ካለው አማራ እንግድነት ጠይቆ በቤቱ ተስተናግዷል። ጎጃሜውም ከሸዋው ኦሮሞ ሰንጋ ታርዶለት በልቷል። ሲዳማ ያለው ከከንባታው ተጋብቷል። ወሎ ያለው ከአፋሬው ጋር ሠርግና ምላሽ በልቷል። ጎንደሬው ከትግራዋዩ ጋር አብሮ ስለ እናት ሀገሩ በፍቅር ዘምቷል፤ ለተቀደሰች ሃይማኖታቸው ሲሉ በፍቅር እየተጠራሩ “ሰማዕትነት አያምልጣችሁ” እየተባባሉ የደም ሰማዕትነት ታሪክ ጽፈው አልፈዋል።

ለራሳችን፣ ያውም እኛ ብቻ ልንገዛት ይህች ዓለም የተሰጠችን እስኪ መስለን ድረስ ጊዜን መከታ ያደረግን ምስኪኖች ወደ ቀደመው ዘመን ለመመለስ፣ ወደ ኋላ ዞረን ለማየት የከበደን ለምንድን ነው? ሲያለቅሱ ማላቀስ፣ ሲያዜሙ ማዜም የሽንገላ ብቻ ሆኖ ከማኅተመ ልባችን (ከልባችን ማሕተም) እስከ መቼ ይሸሻል? በከንፈር መምጠጥ ብቻ የት ድረስ እንጓዛለን?

በኅብረት ኖረን በየተራ ለመሞት የተፈጠርን የጊዜ ሰዎች እኮ ነን። ለመኖራችንም ለመሞታችንም በኅብረት መኖሩ፣ ምርኩዝ መደራረጋችን ከመገፋፋታችን ይበልጣል። ዓለም በራሷ የራሷ ባልሆነችበት እኛ በዓለም ላይ ሥልጣን የለንም። ከዓለም አይደለንምና። (ዮሐ.፲፭፥፲፱) ከእኛም የሆነ አንዳች የለም። በእኛ የሚጠበቀው መኖር ብቻ ነው። “ሀገራችን በሰማይ ነው” እንዳለን ቅዱስ ጳውሎስ (ፊል.፫፥፳) በሰማያዊ ዜግነታችን ከዚያ ሰማያዊ የመለኮት ክብርና የቅዱሳን ኅብረት ተካፋዮች ለመሆን ለመንግሥቱ መብቃት የእኛ ድርሻ ነው።

ቤተ ክርስቲያን ሕጓ፣ ሥርዓቷ ሁሉ ኅብረትን መሠረት ያደረገ ነው። ቅዳሴዋ፣ ዶግማዋ፣ ቀኖናዋ የሚገለጠው በውኅዳን (በጥቂቶች) ሳይሆን ምልዓታዊ በሆነ አንድነት ነው። በዚህ ምሥጢር ሰዎች (ምድራውያን ) ብቻ ሳይሆኑ ስውራን፣ ረቂቃን ሁሉ ይሳተፉበታል። የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዋ ይህ ነው። በኅብረት መዳን በኅብረት ለክብር መብቃት። በግልጥ እና በስውር ያሉ ቅዱሳን፣ መላእክት ሁሉ የዚህ ኅብረታዊ ሥርዓት አካላት ናቸው። ከዚህ ኅብረት መውጣት እንዴት ያለ ታናሽነት ነው? ከዚህ ክብርና ጸጋ ከሚያጎናጽፍ ኅብረት መለየትስ ምን ዓይነት ልብ ማጣት ነው? ምን ዓይነትስ ሕያዋን የሆኑ ምውታን ለመሆን መሽቀዳደም ነው?

የክርስትናችን ጌጥ እና የጽድቃችን ጥሩር በፊታችን ባለው ወንድማችን መጎልመስ እና ወደ ክርስቶስ ፍቅር መቅረብና ማደግ፣ አንድ በምታደርግ የሃይማኖት ሥርዓት መሰብሰብ ላይ ማእከል ያደረገ ነው። ክርስትናችን ከስያሜው ጀምሮ አንድነት እንጅ ግላዊነት አይደለም። ከዚህ ማኅበር መውጣት በክርስቶስ ካሉ እና ከራሱ ከጌታችን ኅብረት መውጣት ነው። ብዙ ስንሆን አንድ፣ አንድ ስንሆን ብዙዎች ነንና። (ሮሜ ፲፪፥፭)

የሰው ልጅ ሰው እስከ ሆነ ድረስ በሰው ጉዳይ ያገባዋል። ለሰው ሁሉም ነገር መለኪያ ሚዛኑ ሰው ነው። የሰው ትጥቁ ሰው ነው። ለዚያውም እኛ በድህነት እና በመከራ ውስጥ ላለን፣ በማያገቡን እና ነገን የተሻለ በማያደርጉልን ሐሳቦች ላይ ቁጭ ብለን ከምንብከነከን ዛሬን የተሻለ በሚያደርጉልን የራሳችን ብሎም የወንድሞቻችን ጉዳዮች ላይ መመካከር፣ በመጠጥ አእምሮአችንን ስተን ከምንናውዝ፣ ሕይወታችንን በከንቱ ከምንገፋ ቆም ብለን ማሰብ የምንችልበትን መንገድ ለመምረጥ ብንዘጋጅ፣ ስለ አውሮፓ ኳስና ድስኩር ከምናብጠለጥል  ስለ ችግሮቻችን መሻገሪያ ምሥጢር ብንተጋ የተሰበረውን እና የተናቀውን መጠገን አይከብደንም።

በአንድ ወቅት አንድ በደቡብ አፍሪካ የአንትሮፖሎጂ ምሁር የነበረ ሰው ከሥራ መልስ ደክሞት አንድ መንደር ሥር ይጠለል እና ቁጭ ይላል። በዙሪያው ሲጫወቱ የነበሩ ሕፃናት ወደ እርሱ መጡና ከበውት ቆሙ። በዚህ መሐል አንድ ጨዋታ ሊያጫውታቸው ፈለገ። ይህ ጨዋታም በቅርጫት ውስጥ ፍራፍሬ አድርጎ ከዛፉ ሥር አስቀመጠና እነርሱን “ትንሽ ሜትሮች ራቅ ብላችሁ ቁሙ” በማለት ያዝዛቸዋል። ልጆቹም እንደተባሉት አደረጉ። ይህ ምሁር ሰው አሁን አንድ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ከዚያ ከዛፉ ሥር ቀድሞ የደረሰ በቅርጫቱ ውስጥ የሚገኙትን ፍራፍሬዎች ለራሱ ያደርጋል፤ ብቻውንም ይወስዳል፤ አላቸውና ሩጫውን እንዲጀምሩ አዘዘ። በዚህ ሰዓት እነዚያ ሕፃናት ሩጫውን እርስ በራሳቸው ተያይዘው መሮጥ ጀመሩ።

ሁሉም ከዛፉ ሥር ደርሰው ቅርጫቱን አነሱ። ፍራፍሬዎችን ሁሉም ወሰዱ። በዚህ ሰዓት ያ አንትሮፖሎጂስት በመደነቅና በጥያቄ ውስጥ ሆኖ ሲመለከት ከቆየ በኋላ ይጠይቃል። ልጆቹም አንድ ቃል ይናገሩታል። UBUNTU (Humanity to Others)። ቃሉ ለምሁሩ አዲስ ነበረ እና ምን ማለት ፈልገው እንደሆነ ይጠይቃል። ልጆቹም “እኛ ደቡብ አፍሪካውያን ነን። አንዳችን ለአንዳችን ልንቆም እንጅ ለብቻችን ልንወስደው ወይም ልንቆም አይቻለንም” የሚል ምላሽ ሰጡት። በዚህ ሰዓት ያ አንትሮፖሎጂስት በመደነቅ ውስጥ ሆኖ ተመለከታቸው። ይህ ማኅበራዊ ዕሴት ነው። አንድነት የልዩነት ማሰሪያ ገመድ ነው። ወደ አንድ መንገድ የሚጓዙ መንገደኞች ይደጋገፋሉ እንጅ አይገፋፉም።

የቤተ ክርስቲያን ልጆች ማኅበራዊ ዕሴታችን ሁሉ አውሮፓዊ ሥሪት እንዲኖረው ለምን ራሳችንን በራሳችን ለቅኝ ግዛት አሳልፈን እንሰጣለን? ከሰው ቤት እንዴት ቤትን መምራት እንደሚቻል ትምህርት እና ዘይቤ ይማሯል እንጂ በሰው ቤት ሕግ መተዳደርም አይቻልም። የሌላው ቤት ሕግ ፈርሶ ቤቱ ሲፈርስ የኛው ቤት መፍረሱ አይቀርም። በዚህ በደረቀው እና የሰው ቤት አመል በበዛበት ሥርዓተ ሕይወታችን ለመኖር ሳይሆን ለመሞት ቀናችንን እንጠባበቃለን። ወደ ፊት ሳይሆን ወደኋላ እንጎተታለን።

ይቆየን!