ማኅበሩ የንብ እርባታ ፕሮጀክቱን አስረከበ
በማኅበሩ የመቀሌ ማእከል ጸሐፊ የማን ኃይሉ በዚሁ የርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት፤ የገዳሙ መነኮሳትን ችግር ለማቃለል ማኅበረ ቅዱሳን ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የፕሮጀክት ጥናት በማካሄደ በ36ሺ 450 ብር ወጪ የንብ እርባታ አጠናቆ ለገዳሙ ማስረከብ ችሏል፡፡
ከቅዱስ ሲኖዶስ ከተሰጠው ሓላፊነቶች አንዱ ገዳማት አድባራትና የአብነት ት/ቤቶች በገቢ እራሳቸውን እንዲችሉ ማገዝ መሆኑን የጠቆሙት ጸሐፊው ወደፊትም ይህን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ግብርናና ገጠር ልማት ጽ/ቤት ተወካይ አቶ ግደይ መለስ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ የገዳሙን ቅርስና ሀብት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት ለገዳማውያኑ ጥሬ ገንዘብ እየሰጡ ተመፅዋች ከማድረግ ይልቅ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን እራስን የሚያስችል ፕሮጀክት ማከናወን ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት ጽ/ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡
አበእምኔት መ/ር አባ ገ/ማሪያም ግደይ በበኩላቸው፤ «ገዳሙ ተዳክሞ መነኮሳቱም በችግር ምክንያት ፈልሰው ወደ መዘጋት በተቃረበበት ወቅት ማኅበሩ ደርሶ ለገዳሙ ፀሐይ አወጣለት» ሲሉ በገዳማውያኑ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በቀጣይ ሊገጥመው የሚችለውን ችግሮች እየተከታተለ ይፈታ ዘንድ የተማፅንኦ ቃል ያሰሙት አበ ምኔቱ ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት መነኮሳቱ ተግተው እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡
በርክክቡ ወቅት የተገኙት የቆላ ተንቤን ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መ/ር አባ እዝራ ሃይሉ ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆኖ እያከናወነ ያለው ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚያስመሰግነው መሆኑን ጠቅሰው መንገዱ እጅግ አድካሚና አስቸጋሪ በሆነ ቦታ መጥቶ ከጥናት ጀምሮ እስከ ትግበራ ያከናወነው ፕሮጀክት ለሌሎች አርአያ ለመሆን የሚያስችለው ነው፡፡
ማኅበሩ የሠራውን ፕሮጀክት ተንከባክበው ውጤታማ በማድረግ ሥርዓተ ገዳማቸውን እንዲያፀኑ አሳስበዋል፡፡ በሠራው የተባበሩትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡
ጥር 4 ቀን 2002 ዓ. ም ማኅበሩ ፕሮጀክቱን ለገዳሙ ባስረከበበት ወቅት እንደተገለፀው በሀገራችን ካሉት ቀደምት ገዳማት አንዱ መሆኑ የሚነገርለት ይኸው ገዳም በጣሊያን ወረራ ወቅት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ከመሆኑ በተ ጨማሪ ከ1966 ዓ.ም. ለውጥ በኋላ የገዳሙ ይዞታ ሙሉ በሙሉ በመወረሱ ገዳሙ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነበር፡፡
ፕሮጀክት ድጋፍ እንዲውል የማኅበረ ረድኤት ትግራይ ከሃያ ስድስት ሺሕ ብር በላይ ግምት ያለው የማር ማጣሪያ ዘመናዊ ማሽን እና ተያያዥ ቁሳቁሶችን በእርዳታ መለገሱ በፕሮጀክቱ ርክክብ ወቅት ተገልጿል፡፡