ማኅበሩ የነጻ የትምህርት ዕድል መስጠት ሊጀምር ነው፡፡
ኅዳር 5 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ
ማኅበረ ቅዱሳን ኅዳር 2 ቀን 2005 ዓ.ም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮችና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በተገኙበት በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በተደረገ የማስተዋወቂያ መርሐ ግብር ለአብነት ተማሪዎችና መምህራን የነጻ ትምህርት ዕድል ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለጸ፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዲ/ን አዕምሮ ይኄይስ “ማኅበሩ ሐምሌ 21/2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ግዮን ሆቴል ከአብነት ምስክርና ከዩኒቨርስቲ ምሁራን ጋር የዘመናዊውን ትምህርት ከአብነት ትምህርት ጋር አቀዳጅቶ የመስጠትን አስፈላጊነት ወሳኝ ውይይት አድርጎ፤ በአባ ጊዮርጊስ ስም የተሰየመ ነጻ የትምህርት ዕድል ማዘጋጀቱን” ገልጸዋል፡፡
የአብነት ትምህርት ማጠናከሪያ፣ ማቋቋሚያና የአባ ጊዮርጊስ የነጻ ትምህርት ሥልጠና ዕድልን በተመለከተ አጠቃላይ ገለጻ ያደረጉት፤ የቅዱሳት መካናትና ልማት የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ “የመርሐ ግብሩ ዓላማ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ዘመኑን በዋጀ መልኩ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚያደርጋቸው ነው” ብለዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ገለጻ የአባ ጊዮርጊስ ነጻ ትምህርት ዕድል የአብነት ትምህርት ተማሪዎችና መምህራን ከመለስተኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የዘመናዊ ትምህርት ወይም ሥልጠና እንዲያገኙ የሚያግዝ ዕቅድ ነው፡፡ አክለውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤቶች ከዘመናዊው ትምህርት ጋር አብሮ አላደገም ያሉት ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ በዚህም እነዚህ ትምህርት ቤቶች ያለተንከባካቢና ከመንግሥት የሚደረገው ድጎማ መቅረቱ ሊቃውንቱ ያለተተኪ እንዲቀሩ አድርጓቸዋል፤ በዚህም ገዳማት ችግር ላይ መውደቃውቸን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም የአብነት ትምህርት እንደ ዕውቀት ተመራጭ አለመሆኑ፣ የአብነት ትምህርት ውሱንነት፣ በአብነት ትምህርት ለተማሩ አማራጭ የሥራ ዕድል አለመኖሩና ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ በየደረጃው በበቂ ዕውቀት የሚያገለግሉ ካህናት ማነስን እንደ ችግር የጠቀሱት ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ፤ ይህ መርሐ ግብር ለቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤቶች የሰው ኀይል ምንጭ በመሆናቸው አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
መርሐ ግብሩ በ750 ተማሪዎች ለሁለት ዓመት በሚቆይ የሙከራ ጊዜ የሚጀመር ሲሆን በዓመት እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚጠይቅና በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የገንዘብ ምንጭ መሆናቸውን እንዲሁም በጥር 2005 ዓ.ም እንደሚጀመር ለማወቅ ተችሏል፡፡