ማኅበረ ቅዱሳን የህብር ሚዲያ መካነ ድር አገልግሎት ጀመረ
በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ በፊት ከነበሩት የአማርኛ(www.eotcmk.org) እና የእንግሊዘኛ (www.eotcmk.org/site-en) መካነ ድሮች በተጨማሪ አዲስ የህብር ሚዲያ መካነ ድር (multimedia website) አገልግሎት ጀምሯል።
"multimedia.eotc-mkidusan.org" በሚል አድራሻ የተለቀቀው ይኸው መካነ ድር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓት እምነትና ክርስቲያናዊ ትውፊት የጠበቁ የምስል ወድምጽ ስብከቶችና ተከታታይ ትምህርቶች፣ ዜማዎችና፣ መዝሙራት እንዲሁም የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜና ንባብ ያስተላልፋል። ቅዱሳት ሥዕላትና የቅዱሳት መካናት ፎቶዎችም ከመግለጫ ጋር ይኖሩታል::(http://multimedia.eotc-mkidusan.org/video/?video=2364766985)
በመካነ ድሩ የሚተላለፉ የምስልና የድምጽ ውጤቶች የቤተክርስቲያንን ትምህርትና የስብከተ ወንጌልን ተደራሽነት እንዲጨምሩና በተለያዩ ቦታዎች ለሚሰጡ ትምህርቶችና ስልጠናዎች እንደ ግብአትነትና ምንጭነት እንዲያገለግሉ ታቅዶ አገልግሎቱ ተጀምሯል። ይህም ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
መካነ ድሩን ለአጠቃቀም ምቹ ለማድረግ የምስል ወድምጽ፣ የድምጽ፣ እና የምስል ዝግጅቶች እያንዳንዳቸው በተለያዩ ክፍሎች (ዐምዶች) ተደራጅተው ቀርበዋል። ተጠቃሚዎች ዝጅቶቹን መካነ ድሩ ላይ በቀጥታ በማጫወት(streaming) ወይም በማውረድ(downloading) መጠቀም የሚችሉበት መንገድም ተመቻችቷል።
መካነ ድሩ በአንድ የማኅበሩ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል አገልጋይ የተሠራ ሲሆን በገንዘብ ሲተመን ከ20 እስከ 30 ሺህ ብር ሊያወጣ እንደሚችል ይገመታል፡፡ መካነ ድሩ በሳምንት ከ10 ሰዓታት በላይ የምስል ወድምጽ ዝግጅቶችን ማቅረብ የሚጀምር ሲሆን የኢንተርኔት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ለሌለባቸው አካባቢዎች እነዚህ ዝግጅቶች በሲዲ የሚሰራጩበት መንገድም ከማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ፕሮግራም ጋር በመተባበር እየተመቻቸ ነው ።
የህብር ሚዲያ መካነ ድር መሰናዶዎች በተለያዩ ቅርጾች (formats) ማለትም በጽሑፍ፣ በድምጽ እና በተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ቋሚ ምስሎች ተዘጋጅተው በመካነ ድር የሚቀርቡበት ሚዲያ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜም በመላው ዓለም በሚገኙ ታላላቅ የሚዲያ ተቋማት ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ የመጣ እና እጅግ ብዙ የሰው ሀይል፣ ገንዘብ እና ቁሳቁስ የሚያስፈልጋቸውን ዘልማዳዊ (fotress) ሚዲያዎችን እየተካ ያለ አሰራር ነው፡፡
ይህንን አገልግሎት ለማሳካትና የበለጠ ለማሳደግ በመላው ዓለም ከሚገኙ ምእመናን የጸሎት፣የሐሳብ፣ የሙያ እና የገንዘብ ድጋፍ ይጠበቃል።ለበለጠ መረጃ፣ ለአስተያየቶችና ለድጋፍ የዝግጅት ክፍሉን ወደ mkelectronicsmedia@gmail.com በመጻፍ ማግኘት ይቻላል።