ማቴዎስ ወንጌል
ነሐሴ 22 ቀን 2006 ዓ.ም.
ምዕራፍ 7
በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ ሰባት ውስጥ የሰውን ነውር ከማጋነን ይልቅ የራስን ባሕርይ መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑን በሰፊው እንማራለን፡፡ ዋና ዋና አሳቦቹም የሚከተሉት ናቸው፡፡
-
ስለ ፍርድ
-
የተቀደሰውን ለውሾች መስጠት እንደማይገባ
-
ዕንቁን በእሪያዎች ፊት ማስቀመጥ እንደማይገባ
-
ስለ ልመና
-
ስለ ጠባቧ ደጅ እና ስለ ሰፊው ደጅ
-
ስለ ሐሰተኞች ነቢያት
-
በዐለት ላይ ስለተመሠረተውና በአሸዋ ላይ ስለተመሠረተው ቤት
1. ስለ ፍርድ፡-
ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሌላው ላይ መፍረድ እንደማይገባ አስተምሯል፡፡ በዚህ ትምህርቱም “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፡፡” ብሏል፡፡ ይህም ንጹሕ ሳትሆኑ ወይም ሳትሾሙ ብትፈርዱ ይፈረድባችኋል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ተሾመው የፈረዱ አሉና፡፡ ለምሳሌ፡- ሙሴ በስለጰዓድ፣ ኢያሱ በአካን፣ ቅዱስ ጴጥሮስ በሐናንያና ሰጲራ፣ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በበርያሱስ ፈርደዋል ዘኁ.27፡1-15፣ 36፡2-12፣ ኢያ.7፡1-26፣ የሐዋ.5፡1-11፣ 13፡4-12፡፡ አንድ ሰው ንጹሕ ሳይሆን በፈረደው ፍርድ እንደሚፈረድበት ከንጉሡ ከዳዊት ሕይወት መማር ይቻላል 2ኛ ሳሙ.12፡1-15፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ “ስለዚህ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና፡፡ እንደዚህም የሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ የምትፈርድን ያንን የምታደርግ ሰው ሆይ አንተ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን?” ብሏል፡፡
ለዚህም ነው ጌታችን በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ከማውጣትህ በፊት በዓይንህ የተጋረድውን ምሰሶ አስወግድ ያለው፡፡ ጉድፍ የተባሉት ጥቃቅን ኃጢአቶች ሲሆኑ ምሰሶ የተባሉት ደግሞ ታላላቅ ኃጢአቶች ናቸው፡፡ ይህም ጥቃቅኗን ኃጢአቶች እየተቆጣጠርክ በባልንጀራህ ከመፍረድህ በፊት አንተው ራስህ ታላላቆቹን ኃጢአቶችህን በንስሐ አስወግደህ እንዳይፈረድብህ ሁን ማለት ነው፡፡
እዚህ ላይ የባልንጀራ ኃጢአት ትንሽ የራስ ኃጢአት ደግሞ ትልቅ የተባለበት ምክንያት ሰው የባልንጀራውን ኃጢአት የሚያውቀው በከፊል የራሱን ግን የሚያውቀው ሙሉ በሙሉ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ተላልፎ እገሌ እንዴት ኃጢአት ይሠራል ብሎ በሌላው መፍረድ ፈሪሳውያንን መሆን ነው ማቴ.23፡1-39፡፡
2. የተቀደሰውን ለውሾች መስጠት እንደማይገባ፡-
ጌታችን “በእግራቸው እንዳይረግጡት፣ ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፣ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ” ብሏል፡፡ ለመሆኑ ውሾች የተባሉት ሥራይን የሚያደርጉ፣ ሴሰኞች፣ ነፍሰ ገዳዮች ጣዖትን የሚያመልኩና የሐሰትን ሥራ ሁሉ የሚወዱ ናቸው ራእ.22፡15፡፡ እነዚህም ከቶ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገቡም፡፡ ዕድል ፈንታቸው ጽዋ ተርታቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፡፡ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው ራእ.21፡8፣ 27፡ 1ኛ.ቆሮ.6፡9-10፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ ማለቱ የተቀደሰውን ሥጋዬንና የከበረውን ደሜን ለእነዚህ አታቀብሉ ማለቱ ነው፡፡ አንድም ቋንቋችን ከቋንቋችሁ፣ መጽሐፋችን ከመጽሐፋችሁ አንድ ነው፡፡ እያሉ እንዳይከራከሯችሁና እንዳይነቅፏችሁ ሃይማኖታችሁን ለመናፍቅ አትንገሩ ማለቱ ነው፡፡ መናፍቃንም ውሾች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ውሾች የተባሉ ወደ ቀደመ ግብራቸው የሚመለሱ በደለኞች ናቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችንን እና መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ከማወቅ ጋራ ከዚህ ዓለም ኃጢአት ከተለዩ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የሚሸነፉ ከሆነ ከቀደመ በደላቸው ይልቅ የኋላው በደላቸው የጸና የከፋ ይሆናል፡፡ አውቀዋት ከተሰጠቻቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ ጥንቱኑ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት ይሻላቸው ነበር፡፡
ምክንያቱም እንደ ውሻ ወደ ትፋት መመለስ ነውና ብሏል 2ኛ.ጴጥ.2፡20-22፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ሰላም የሚያውኩ ሰዎችም ውሾች ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ጺፍላቸው በኒያ ለከፍካፎች መናፍቃን እወቁባቸው ብሏቸዋል ፊል3፡2፡፡ አንድም የተቀደሰ የተባለ ሥጋውና ደሙ ነው፡፡ ስለሆነም ከኃጢአት ለመመለስ ላልወሰኑ በደለኞችና በክህደት ለጸኑ መናፍቃን ሥጋውንና ደሙን ማቀበል አይገባም፡፡
3. ዕንቁን በእሪያዎች ፊት ማስቀመጥ እንደማይገባ፤
ጌታችን “ዕንቁዎቻችሁን በእሪያዎች ፊት አትጣሉ” ያለበትም ምክንያት አለው፡፡ ከአገራቸው ቀን ዋዕየ ፀሐይ ይጸናል፡፡ ሌሊት ዕንቁ ከተራራ ላይ አኑረው የሚጽፍ ሲጽፍ፣ አውሬ የሚያድንም ሲያድን ያድራል፡፡ እሪያ /አሳማ/ መልከ ጥፉ ነው፡፡ በዕንቁው አጠገብ ሲሄድ የገዛ መልኩን አይቶ ደንግጦ ሲሄድ ሰብሮት ይሄዳል፡፡
ዕንቁ የጌታ እሪያ የአይሁድ ምሳሌ ናቸው፡፡ በገዛ ኃጢአታቸው ቢዘልፋቸው የዕንቁ መስተዋት ሆኖ መልከ ጥፉ ኃጢአታቸውን ቢያሳያቸው ጠልተው ተመቅኝተው ገድለውታል፡፡ አንድም እሪያ የተባሉ ወደ ቀደመ ኃጢአታቸው የሚመለሱ ሰዎች ናቸው፡፡ “የታጠበች እሪያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል” 2ኛ.ጴጥ.2፡22፡፡
አንድም እሪያዎች የአጋንንት ማደሪያዎች ሆነው ወደ እሳት ባሕር ለሚገቡ ሰዎች ምሳሌዎች ናቸው ማቴ.8፡32፡፡ አንድም እሪያዎች የተባሉ መናፍቃን ናቸው፡፡ ስለሆነም ዕንቁ የሆነ ሃይማኖታችንን፣ ሥርዓታችንን፣ ታሪካችንን እና ትውፊታችንን በእነርሱ ፊት ልናቀርብ አይገባንም፡፡
4. ስለ ልመና፡-
“ለምኑ ይሰጣችሁማል፡፡” ጌታችን እንዲህ ማለቱ የበቃውንና ያልበቃውን በምን እናውቀዋለን ትሉኝ እንደሆነ “ለምኑ ይሰጣችኋል” ማለቱ ነው፡፡ ለምነው ያገኙ ዮሐንስ ዘደማስቆና ድሜጥሮስ የበቃና ያልበቃ ለይተው ያቀብሉ ነበር፡፡ ምክንያቱም መንፈሳዊ ሰው ሁሉን ይመረምራልና 1ኛ.ቆሮ.2፡15፡፡ ፈልገው ያገኙና አንኳኩተው የተከፈተላቸው ሰዎች ብዙዎች በመሆናቸውም “የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፣ የሚፈልገውም ያገኛል፣ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል” አለ፡፡ ከቀደሙ ሰዎች አብርሃም ከኳላ ሰዎች ደግሞ ሙሴ ጸሊም በፀሐይ በሥነ ፍጥረት ተመራምረው አምነዋል፡፡ በክርስቶስ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ በመለመኑ በመፈለጉ እና በማንኳኳቱ የገነት በር ተከፍቶለታል፡፡ “ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው፡፡ ኢየሱስም እውነት እልሃለሁ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው” ሉቃ.23፡42፡፡
በተጨማሪም፡- ለባሕርያችሁ ክፋት ጥመት የሚስማማችሁ ስትሆኑ እናንተ ለልጆቻችሁ በጎ ነገርን የምታደርጉላቸው ከሆነ ቸርነት የባሕርይ የሚሆን ሰማያዊ አባታችሁማ በጎ ነገርን ለሚለምኑት እንደምን በጎ ነገርን ያደርግላቸው ይሆን አላቸው፡፡
5. ስለ ጠባቧ ደጅ እና ሰፊው ደጅ፡-
ሀ/ ወደ ሕይወት የምትወስድ ጠባብ ደጅ እና ቀጭን መንገድ የተባለች ሕገ ወንጌል ናት፡፡ ምክንያቱም “ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጐናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሔድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሒድ፡፡ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፣ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ ትላለችና፡፡
ለ/ ጠባብ ደጅና ቀጭን መንገድ የተባለች ባለጸጋን ጹም ድኃን መጽውት ማለት ነው፡፡
ሐ/ ጠባብ በር የተባለች ፈቃደ ነፍስ ናት
መ/ ወደ ጥፋት የሚወስድ ሰፊ ደጅና ትልቅ መንገድ የተባለች ኦሪት ናት፡፡ ምክንያቱም የገደለ ይገደል፣ ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ ጥርስ የሰበረ ጥርሱ ይሰበር፣ እጅ የቆረጠ እጁ ይቆረጥ፣ እግር የሰበረ እግሩ ይሰበር፣ ያቃጠለ ይቃጠል፣ ያቆሰለ ይቁሰል፣ የገረፈ ይገረፍ ትላለችና ዘጸ.21፡23፣ ማቴ.5፡38፡፡
ይቀጥላል
ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 4ኛ ዓመት ሚያዚያ 1989 ዓ.ም.