መንፈሳዊ ኮሌጆች ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተጠቆመ

 

ጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. 

በይብረሁ ይጥና

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚገኙት መንፈሳዊ ኮሌጆች አንድ ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርትና የትምህርት ጥራት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተገለጠ፡፡

 

ከጥቅምት 4-11 ቀን 2006 ዓ.ም. በተካሄደው የ32ኛ መንፈሳዊ የሰበካ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ላይ በተሳታፊዎች ተደጋግሞ እንደተነሣው የአቋም መግለጫው እንደሚያመለክተው የቅድስት ሥላሴ፣ የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስና የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጆች በርካታ ደቀ መዛሙርትን ድኅረ ምረቃ፣ በዲግሪ፣ ዲፕሎማና ሠርተፍኬት በማስተማር እንደሚያስመርቁ ተገልጿል፡፡

 

ነገር ግን ከአቀባበል፣ የትምህርት አሰጣጥ ክትትልና ምዘና ክፍተት የሚታይባቸው በመሆኑ ሁሉም ኮሌጆች ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርትና የትምህርት ጥራት ሊከተሉ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

 

በተጨማሪም ከመንፈሳዊ ትምህርቱ ጎን ለጎን የሥራ ተነሳሽነት ያለው ትምህርትና በቤተ ከርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት የሚያበረክቱበት ሥልጠና ለተማሪዎች አብሮ መሰጠት እንዳለበት ተወስቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው አስተዳደራዊ ችግር ተጠንቶ እልባት እንዲያገኝም የአቋም መግለጫው ያመለክታል፡፡