“መባዬን በመያዝ ወደ ቤትህ እገባለሁ” (መዝ.፷፭፥፲፫)
ሰኔ ፲፯፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ድንቅ በሆነ ሥራው ዓለምን ከእነ ጓዟ ለፈጠረ አምላክ የሚበቃ ከሰው ዘንድ የሚሰጥ ምን ነገር ይኖራል? ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ባለ ጸጋው አምላካችን ልናቀርብስ የምንችለው ከእኛ የሆነ ከእርሱ ዘንድ ዋጋ ያለውስ ነገር ምን ይሆን? እርሱ ባወቀና በፈቀደ ከእርሱ የሆነ ግን ከእኛ የሚሰጥ ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር ስጦታን እንድናቀርብ ግን ተሰጠን፡፡ “ለከበረ ስምህም ከአንተ የተገኘውን ዕጣን አቀረብንልህ” እንዲል፡፡ (አንቀጸ ብርሃን) ሁሉ በእጁ ለሆነው አምላክ ስጦታ እንድናቀርብም ክቡር ፈቃዱ ሆነልን፡፡
ለአምላካችን የምንሰጠው ስጦታ ለእርሱ ካለን ፍቅር የተነሣ፣ እንደ አቅማችንና እንደ መረዳታችን የሚሰጥ ነው፡፡ ይህም በእርሱ ዘንድ የተወደደ እንደሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይነግረናል፤ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።” (፪ኛ ቆሮ.፱፥፯)
በመጽሐፈ ሥነ ፍጥረት የተመዘገበው የአቤልና የቃየል ታሪክ ለዚህ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው፡፡ “ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ።” ታሪኩን እስከ መጨረሻው ስናነብ ቃየል በቅናትና በጥላቻ ወንድሙ አቤልን እንደገደለ እናውቃለን፡፡ (ዘፍ.፬፥፩-፰)
በብሉይ ኪዳን ሕዝበ እግዚአብሔር እንዲሰጥ ተፈቅዶለት ከነበረውን የስጦታ ዓይነት (ዘሌ.፩፥፫፣ ዘኁ.፯፥፲፪)፣ ቃየል ያቀረበው በግዴለሽነትና በበጎ ፈቃድ ባለመሆኑ አምላክ እንዳልተቀበለውም እንረዳለን፡፡ ለሐዲስ ከዳን ምእመናን ለእኛ የተፈቀደልን የእንስሳት ዓይነት ማቅረብ ባይሆንም አማናዊው በግ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል መሥዋዕት ሆኖ በቀረበልን መሠረት ሌላ በግ ወይም እንስሳ አርደን ሳይሆን ስጦታን ለቤቱ እናቀርባለን፡፡
ልበ አምላክ ነቢዩ ዳዊት መባዕ ለእግዚአብሔር ቤት እንደሚገባ ሲገልጽ “እበውእ ቤተከ ምስለ መባእየ፤ መባዬን በመያዝ ወደ ቤትህ እገባለሁ” ብሏል፡፡ (መዝ.፷፭፥፲፫)፡፡ ለቤተ መቅደስ መገልገያ የሚሆኑንና ንዋያተ ቅድሳትን እንዲሁም ጧፍ፣ ዕጣን፣ ዘቢብ፣ … የመሳሰሉትን ለእርሱ በቂ ሆነው ሳይሆን መባዕ ማቅረብ የተገዥነት መገለጫና በረከት የሚያስገኝ ምግባር በመሆኑ ነው፡፡ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እና በተለያዩ ገዳማት ስንሄድ ይዘን የምንገባውና የምንሰጠው መባዕ ሊሆን ይገባል፡፡
መባዕ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ከመፈጸም አንጻር ያለው ዋጋ እጅግ የላቀ እንደሆነ አገልጋዮችም ሆነ ምእመናን ሊያውቁት ሊረዱት የሚገባው ነው፡፡ በጸሎተ መባዕ በካህኑ በሚደርስው ሥርዓተ ጸሎት መሠረት የመንፈሳዊ ጸጋ ተሳታፊ ያደርጋልና፡፡ (ማቴ. ፭፥፳፬፣ ማር.፯፥፲-፲፪)
የጸሎተ ኪዳን፣ የቅዳሴ፣ የሥርዓተ ፍትሐትና የሌሎችም ጸሎት መፈጸሚያ ምእመናን የሚያቀርቡት መባዕ በመሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ዋጋውን ተድረተን፣ በደስታና በፍቅር ስጦታውን ልናቀርብ ይገባናል፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ስጦታችን ይቀበልንን፤ አሜን!