መስቀል ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

መስከረም 28/2004 ዓ.ም.

ምን አልባት አንድ ሰው የእውነትን እውቀት ቢያስተምር በእውቀቱ ለመማረክ ከጠቢቡ ይልቅ አላዋቂው በጣም የቀረበ ነው፡፡ እርሱንም ወደዚህ እውቀት ለማምጣት ከጠቢቡ ይልቅ አላዋቂው በጣም ይቀላል፡፡ ይህን እውቀት እረኞችና ባላገሮች ፈጥነው ለመቀበል የበቁት እውቀት ነው፡፡ እነርሱ ለሁልጊዜውም አንዳች ጥርጣሬ በልቡናቸው ሳያሳድሩ እውቀቱን እንደ ጌታ ቃል አድርገው ተቀብለውታል፡፡ በዚህ መልክ ጌታችን የአሕዛብን ማስተዋልና ጥበብ አጠፋው፡፡ ይቺ የአሕዛብ ማስተዋልና ጥበብ አስቀድማ ራሱዋን አዋርዳለችና ለዘለዓለም ለምንም የማትጠቅምና የማትረባ አደረጋት፡፡ ይቺ ማስተዋልና ጥበብ ምንም እንኳ የእርሱዋን አቅምና ችሎታ በጌታችን ሥራ ላይ ለመግለጥ ብትሞክርም አልሆነላትም፡፡ ስለዚህም አሁን ራሱዋን ለማላቅ አልተቻላትም፡፡ ምክንያቱም በክርስቶስ የተገለጠው እውቀት እርሱዋን የሚሻ አይደለምና፡፡ ይህ አዲስ የተገለጠው እግዚአብሔርን የማወቅ መንገድ ከእርሱዋ በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ወደ ዚህ ወደ እግዚአብሔር የእውቀት ከፍታ ለመምጣት እምነትና የዋሃት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ከውጭ በትምህርት ከምናገኛቸው ይልቅ ሊኖሩን የሚገቡ መንፈሳዊ ሀብታት ናቸው፡፡ ምክንያቱም “እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እድርጎአታል ብሎናልና፡፡

ነገር ግን “እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አድርጐታል” ሲል ምን ማለቱ ነው? ምክንያቱም ሞኝነትን በእምነት ካለመቀበል ጋር አቆራኝቶ ነውና ያስተማረው፡፡ የዚህ ዓለም ጥበበኞች የሚባሉት በዚህ እውቀታቸው አብዝተው የሚመኩ ቢሆንም ጌታችን ግን እነርሱን ለመጋፈጥ ጊዜውን አላጠፋም ነበር፡፡ መልካም የሆነውን ነገር ፈጽማ ለይታ ማወቅ የተሳናት ይህች ጥበብ ምን ዓይነት ጥበብ ናት? ስለዚህ አስቀድማ የእርሱዋ ጥበብ የማይጠቅምና የማይረባ መሆኑን ከተረዳች በኋላ ጌታችን ደግሞ ሞኝነት እንደሆነ ገለጠው፡፡ ይህች ሰዋዊት ጥበብና ማስተዋል የእግዚአብሔርን ሕልውና በእውቀቱዋ ተደግፋ ማረጋገጥ አልተቻላትም፤ እንዴት ታዲያ ከዚህ በእጅጉ የሚልቀውንና የሚሰፋውን የእግዚአብሔርን ሥራ መረዳትና ማስረዳት ይቻላታል? ስለዚህም ከዚህ እንደምንረዳው የእግዚአብሔርን ጥበብ ለመረዳት የግድ እምነት እንጂ ብዙ ምርምርና ድካም አለማስፈለጉን ነው፡፡ በዚህ መልክ እግዚአብሔር አምላክ የዓለምን ጥበብ ሞኝነት እንዳደረጋት ማስተዋል እንችላለን፡፡

 

እርሱ በወንጌል ሞኝነት ዓለሙን ለማዳን ወድዶአል፡፡ ነገር ግን ሞኝነት ሲል በአላዋቂነት ማለቱ ግን አይደለም በወንጌል ሞኝነት ሲል በሰው ዘንድ እንደ ሞኝነት በሚቆጠር መልኩ ሲለን ነው፡፡ በእርሱ የተገለጠችው ጥበብ ታላቅ የሆነች ጥበብ ናት፤ ነገር ግን ለዓለሙ የገለጠባት መንገድ ግን ሞኝነት ይመስላል፡፡ ከእግዚአብሔር ሞኝነት የሚልቅ ጥበብ ፈጽሞ የለም፡፡ ከዓለሙም ሲያስተዋውቃት ሞኝነት በሚመስል መንገድ ነበር፡፡ ይህችን ጥበብ ወደ ዓለም ሲያገባት ለምሳሌ ልክ እንደ አፍላጠን አሪስጣ ጣሊስ፣ ሶቅራጠስ በፍልስፍና በተካኑት ወገኖች በኩል አልነበረም ፡፡ ነገር ግን በተናቁ ዓሣ አጥማጆች በኩል ነው እንጂ፡፡ እንዲህ ስለሆነም ድሉ እጅግ ታላቅና አንጸባራቂ ሆነ፡፡

ሐዋርያው በመቀጠል ስለመስቀሉ ኃይል ሲገልጽ “መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ፣ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፣ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ፣ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፤ የተጠሩት ግን አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎች ቢሆኑ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው፡፡” (ቁ.፳፪-፳፬) አለ፡፡

ለዚህ ኃይለ ቃል ሰፊ ትንታኔን መስጠት ይቻላል፡፡በዚህ ቦታ ሐዋርያው ሊገልጠው የፈለገው ነገር እንዴት እግዚአብሔር አምላክ ሰው ከሚያስበው በተቃራኒው መንገድ ሞትን ድል እንደነሣውና ወንጌል ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠች ስለመሆኑዋ ነው፡፡ ስለዚህ ሲናገር ምን አለ?፡- አይሁድን በክርስቶስ እመኑ ስላቸው እነርሱ ደግሞ የሞተውን አስነሡትና በአጋንንት ቁራኛ የተያዘውን ፈውሱትና አሳዩን እነዚህን ምልክቶችን ብታሳዩን በእርሱ እናምናለን፡፡ እኛ ግን በምላሹ ስንመልስላቸው እኛስ “የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብክላችኋለን” እንላቸዋለን፡፡ እንዲህ ዓይነት ቃላችን ፈቃዱ የሌላቸው ትእቢተኞችን ብቻ አይደለም የሚያሸሻቸው፣ ነገር ግን በእርሱ ለማመን ፈቃዱ ያላቸው አይሁድ እንኳ የሚያስበረግግ ቃል ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ቃሉ ያን ያህል የሚያስበረግግ ቃል ሆኖ ግን አይደለም፡፡ ይልቁኑ የጠፉትን ወደ እርሱ የሚያቀርብና ለእግዚአብሔር ምርኮን የሚያመጣና ድል የሚነሣ ቃል ነበር፡፡

 

አሕዛብ ደግሞ ቃሉን በንግግር ጥበብ አሳምረን በፍልስፍና መንገድ እንድናቀርብላቸው ይሻሉ፡፡ እነርሱ እንዲህ እንዲቀርብላቸው ቢወዱም እኛ ግን ስለ መስቀሉ እንሰብክላቸዋለን፡፡ ስለዚህም በአይሁድ ዘንድ እንደ ደካሞች ተደርገን እንደተቆጠርን እንዲሁ በእነዚህም ዘንድ እንደሞኞች እንቆጠራለን፡፡ እኛን ከመስማት የሚመለሱት እነርሱ በጠየቁን መልክ ባለማቅረባችን ብቻ ግን አይለደም፤ እኛን ከመስማት የሚመለሱት፣ ነገር ግን እነርሱ ከጠየቁን በተቃራኒው አድርገን በማቅረባችንም ጭምር ነው እንጂ፡፡ ለእነርሱ ለእኛ የመዳን ምልክታችን መስቀል ስለመሆኑ በምክንያት አለመግለጻችን ብቻ አይደለም እኛን ከመስማት እንዲመለሱ የሚያደርጋቸው ነገር መስቀሉ ለእነርሱ የደካማነት ምልክት እንጂ የኃያልነት ምልክት አለመሆኑም ጭምር እንጂ፡፡ በእነርሱ ዘንድ ይህ ጥበብ ሳይሆን ሞኝነትን የሚያሳይ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፡፡

ስለዚህም እነርሱ ኃይልን የሚሰጣቸውን ምልክትንና ጥበብ ሲሹ የጠየቁትን አለማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን እነርሱ ከሚመኙት ምልክት በተቃራኒ በማቅረባችንና ክርስቶስን እንዲከተሉት በመስበካችንም ይሰነካከላሉ፡፡ እንዴት ታዲያ እኛ የምንሰብከው የመስቀሉ ኃይል ከመረዳት ያለፈ አይሆን? አንድ በመከራ ውስጥ ላለና ከስቃዩ ለማረፍ መጠጊያ ለሚፈልግ ሰው እኛ እጅግ አደገኛ ወደሆነው የባሕር ማዕበል ውስጥ እርሱን የምንመራውና በዚያ ውስጥ የምናድነው መሆናችንን የገለጽንለት ብንሆን እንዴት እኛን አምኖን ደስ ብሎት ሊከተለን ይችላል? ወይም አንድ ሐኪም የታመመነውን ቁስለኛ ሰው ሕማሙን በመድኃኒት ሳይሆን ቁስሉን ራሱን ደግሞ በማቃጠል እንደሚያድነው እየማለ ቢነግረው እንዴት ሊቀበለው ይችላል? ይህ በእርግጥ ልዩ የሆነ ኃይል ነው፡፡ ስለዚህም ክርስቶስ ሐዋርያትን ወደ ዓለም ሁሉ ሲልካቸው ያለ ምልክት አልሰደዳቸውም፡፡ ነገር ግን ከሚታወቁት ምልክቶች በተቃራኒው የሆኑ ምልክቶችን ያደርጉ ዘንድ ነበር ሥልጣንን የሰጣቸው ፡፡

 

በሥጋው ወራት ጌታችን እንዲህ ዓይነት ከተፈጥሮአዊ ሥርዓት በወጣ መልኩ ምልክቶችን ያደርግ ነበር፡፡ ለምሳሌ ሲወለድ ጀምሮ ዐይነ ስውር በነበረው ላይ ኃይሉን በመፈጸም አሳይቶናል፡፡ የዚህን ሰው የታወሩትን ዐይኖች ጌታችን ሲፈውሳቸው ዐይነ ስውርነትን በሚያባብስ ጭቃ ቀብቶ ነበር፡፡ (ዮሐ.9፥6) በጭቃው ጌታችን ይህን እውር የሆነው ሰው እንደፈወሰው እንዲሁ በመስቀሉ ዓለሙን ወደ እርሱ አቀረበው፡፡ ተቃዋሚዎችን ድል መንሣት የማይቻለውን ኃይልን በማስታጠቅ ድል የሚነሣ አደረገው፡፡

እንዲህ ዐይነትን ተግባር በሥነፍጥረትም ላይ ፈጽሞት እናገኘዋለን፡፡ ፍጥረታትን ሲፈጥራቸው እነርሱኑ መልሶ በሚያጠፋ ነገር ነው ፈጥሮአቸው የምናገኘው፡፡ ለምሳሌ የባሕር ማዕበልን በአሸዋ በመገደብ ለኃይለኛው ማዕበል ደካማ የሆነው አሸዋ ይጠብቀው ዘንድ መሾሙን እናስተውላለን፡፡ ምድርን በውኃ ላይ አጸናት፡፡ ውኃን እጅግ ስስና ቀላል በሆነ ደመና እንዲቁዋጠር አደረገው፡፡ በነቢያትም በኩል በአነስተኛ የእንጨት ቅርፊት ከውኃ ውስጥ ዘቅጦ የነበረውን ብረት አወጣ፡፡ (2ነገሥ.6፥ 5-7) እንዲሁ በመስቀሉ ዓለሙን ወደ እርሱ አቀረበ፡፡ ታላቅ ስለሆነው ኃይልና ጥበብ አታስተውሉምን? እነሆ ከእኛ መረዳት በተቃራኒው በሆነ ኃይል እኛን ወደ እምነት ሲያቀርበን አትመለከቱምን? እንዲሁ መስቀልም ደካማ ሊመስለን ይችላል፤ ነገር ግን በእጅጉ ብርቱ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ወደራሱ የሚስብ ኃይል በላዩ እንዳደረበት ማስተዋል እንችላለን፡፡

ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ እነዚህን ሁሉ በአእምሮ ውስጥ ሲያመላልሳቸው ቆይቶ በመደነቅና በመገረም “ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታል”(ቁጥ.፳፭) አለ፡፡ ከመስቀሉ አንጻር ሞኝነትናና ደካማነትን አስቀመጠ ነገር ግን አማናዊ የሆነውን ሞኝነትንና ደካማነት ሳይሆን የሚመስለውን ነገር ነበር የገለጠልን፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ስለመስቀሉ ኃይል ሲሰብክ በተቃራኒ ጎራ ያሉትን ወገኖች አመለካከታቸውን ሳይጎዳ ነበር የሰበከው፡፡ ፈላስፎች በምክንያት ይህን ኃይል መረዳት እንደማይችሉ ነገር ግን በእነርሱ ዘንድ ሞኝነት የሚመስለው የመስቀሉ ነገር ታላቅ የሆነ ኃይል ያለው መሆኑን ነበር ያስገነዘባቸው፡፡ ስለዚህ ብዙ ወይም ጥቂት ወይም አንድ ተከታይ ያለው ጠቢብ ሰው የት አለ? ፕላቶና ተከታዮቹ እንዴት ያለ አድካሚ በሆነ መንገድ ጥበብን ማግኘት ሻቱ! እነርሱ ለእኛ ስለ መስመር፣ ስለማዕዘን(angle)፣ ስለ ነጥቦች፣ ስለቁጥሮች፣ ተመጣጣኝ ስለሆኑትና ስላልሆኑት ሒሳባዊ ቀመሮች ልክ እንደ ሸረሪት ድር እያወሳሰቡ አስተምረውን ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እነዚህ ድሮች በዚህ ምድር ስንኖር አያስፈልጉንም ማለታችን ግን አይደለም ሆኖም ከዚህ ከሚልቀው ጋር ሲተያዩ እምብዛም አስፈላጊዎች አይሆኑም፡፡ ፈላስፋው ፕሉቶ ነፍስ ሕያዊት እንደሆነች ለማስረዳት እንዴት ደከመ! ሲወጣም ሲገባም ስለነፍስ ሕያዊነት ትንታኔ ለመስጠት ሞከረ ነገር ግን ስለነፍስ እርግጠኛውን ነገር ለማስተማር አልበቃም፡፡ ይባስ ብሎ በዚህ ጉዳይ ሰሚ አጣ፡፡

ነገር ግን መስቀል ባልተማሩት ሐዋርያት በኩል ብዙ ሰዎችን ወደ እርሱ አቀረበ፡፡ ዓለሙ ሁሉ ተገልብጦ ክርስቶስን ወደ መከተል ተመለሰ፡፡ የተለመዱትን ብቻ አልነበረም ሲያስተምሩ የነበሩት ነገር ግን ስለእግዚአብሔር፣ እውነተኛ ስለሆኑት አንድ ክርስቲያን ሊላበሳቸው ስለሚገቡ መልካም ምግባራት እንዲሁም በወንጌል ሕይወት እንዴት መመላለስ እንዲገባን በተጨማሪም ስለዓለም ምጽአት በሰፊው ሰብከዋል፡፡ በትህምርታቸውም የተከተሏቸውን ሁሉ ፈላስፎች አደረጉዋቸው፤ ያልተማሩትንም በጥበብ ቃል የሚያስተምሩ መምህራን አደረጓቸው፡፡ ወዳጄ ሆይ ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት እንዴት እንደሚልቅ ተመልከት፡፡ ምክንያቱም በዚህ ታላቅ በሆነ በመስቀሉ በተገለጠው ኃይል ዓለሙ ሁሉ ድል ተነሣ፤ ብዙዎች የተሰቀለውን ክርስቶስን እየሰበኩ ብዙዎችን ለእርሱ ማረኩ፡፡ እነዚህ እየሰፉና ዓለምን እየከደኑዋት ሲመጡ በተቃራኒ ጎራ ያሉ ወገኖች ግን እየጫጩና እየጠፉ ሄዱ፡፡ ሕያው የሆነው ቃሉ ከሙታን ጋር ውጊያን ገጠመ ድል ነሣቸውም፡፡

ስለዚህም አንድ ፈላስፋ እኔን ሞኝ ሲል የእርሱን እጅግ የበዛውን ሞኝነቱን ይመለከታል፡፡ ምንም እንኳ እኔ በእርሱ አንደበት ሞኝ ብባልም መረጃዎች ግን የሚያሳዩት እኔ ከእርሱ ይልቅ ጠቢብ መሆኔን ነው፡፡ እርሱ እኔን ደካማ ቢል እንዲህ ባለበት ንግግሩ የእርሱን ደካማነት ይረዳል፡፡ ከዓሣ ማጥመድ የመጡት ሐዋርያት በእግዚአብሔር ጸጋ ለመፈጸም የተቻላቸውን ከአሕዛብ ፈላስፎች፣ ንግግር አዋቂዎችና፣ ገዥዎች ወይም በአጭሩ ዓለም ሁሉ ከዚህ ወደዚያ ብዙ ሺህ ጊዜ ቢታትር በእነርሱ ያደረውን ሀብት በድካማቸው ለማግኘት ቢጥሩ አይደለም ማግኘት ሐዋርያት የስተማሩትን ደግመው መናገር አይቻለውም፡፡ በመስቀሉ ያልተሰበከ ምን ነገር አለ? ስለነፍስ ሕያውነት ፣ ስለሥጋ ትንሣኤ ፣ ስለዚች ዓለም አላፊነት፣ ተስፋ ስለምናደረጋት ሕይወት፣ ሰዎች መላእክነትን ስለመምሰላቸው፣ ራስን ባዶ ስለማድረግ እንዲሁም ሌሎችም ወደ ፍጹምነት የሚያደርሱ አስተምህሮዎች የተላለፉበት በመስቀሉ ነው፡፡….

ከዚህ በላይ እኛ ምን ልንል እንችላለን ? ነገር ግን በተግባር እርስ በእርሳችን ያለንን ድንቅ የሆነ መተሳሳሰብን እናጠንክር ፡፡ የጽድቅም ብርሃን ደምቆ እንዲታይ እናድርግ፡፡ ሐዋርያውም እናንተን ለዓለም የምታበሩ ብርሃናት ናችሁ ይላችኋል(ፊልጵ.፪፥፲፭)፡፡ መንፈሳዊው ተግባር ከዓለማዊው ተግባር እንደመላቁ እግዚአብሔር አምላክ ከፀሐይም ከሰማይም ከውቅያኖስም በላይ ታላቅ ሥራን ለዚህች ምድር እንድንፈጽም ሓላፊነትን ሰጥቶናል፡፡ እኛ በሰማይ ላይ የምታበራውን ፀሐይንና ክበቡዋን አይተን እናደንቃለን፡፡ ይልቁኑ ከእርሱዋ በእጅጉ የሚልቀው ብርሃን በእኛ ውስጥ እንዳለ እናስተውል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን እኛ ይህን ብርሃን ካልሠራንበት የዚህ ብርሃን ተቃራኒ የሆነ ድቅድቅ ጨለማ እንደሚነግሥብንም ልብ እንበል፡፡ ጽኑ የሆነው ጨለማ ዓለምን ሲውጣት ዓለም በጭንቅ ውስጥ ትሆናለች፡፡ በእኛ ውስጥ ድቅድቅ ጨለማ ሰፍኖ ሲገኝ ነፍሳችን በጭንቅ ትያዛለች፡፡ ጨለማው በከሃዲያን ወይም በአሕዛብ ላይ ብቻ ያለ አይደለ ነገር ግን በእኛም መካከል ባሉት ክርስቲያናዊ እውቀቱና ሕይወቱ በሌላቸው ላይ ነግሦም ይታያል፡፡

 

ከመካከላችን አንዳንዶች ትንሣኤውን አይቀበሉም፣ አንዳንዶች ደግሞ በጥንቆላና በኮከብ ቆጣሪዎች የሚታመኑ እነርሱ ባሉዋቸውም የሚመሩ ወገኖች ናቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከክፉ ይጠብቀናል ሲሉና አጋንንትንም እንስብበታለን በማለት አሸን ክታቦችን በአንገታቸው ላይ የሚያንጠለጠሉ ናቸው፡፡

ስለዚህም ጉዳይ ጦምን እንያዝ በውጊያውም ረዳት ሁኑኝ፡፡ በእናንተ ክርስቲያናዊ ምልልስ እነርሱን ወደዚህ ወደተቀደሰ ሕይወት ማምጣት ይቻላልና፡፡ እኔ ሁልጊዜ እንደማስተምረው አንድ ሰው ክርስቲያናዊ ስብዕናን አስመልክቶ ሌሎችን ከማስተማሩ አስቀድሞ ራሱን ሊያስተምር ይገባዋል እላለሁ፡፡ እርሱን የሚሰሙት ከቅድስና ሕይወት ወጥተው እንዳይመላለሱ አርዓያ ሊሆናቸው ይገባል፡፡ በዚህም መልክ በመመላለሰ አሕዛብ ስለእኛ በጎ የሆነ አመለካከት እንዲኖራቸው እናድርግ፡፡ ወንጌልን በሕይወታችን ለእነርሱ በመስበካችን ከእነርሱ የምንቀበለው መከራ ይኖራል ነገር ግን አላፊ ነው፡፡

ይህን በሕፃናት አታስተውሉትምን፡፡ አንዳንዴ ልጆች በአባታቸው እቅፍ ሳሉ በቁጣ የአባታቸውን ጉንጭ በጥፊ ሊመቱት ይችላሉ፤ ነገር ግን አባት ልጁ ቁጣውን በእርሱ ላይ በመግለጡ በልጁ አይቆጣም ይልቅኑስ በእርሱ ዘንድ እጅግ ጣፋጭ ይሆንለታል፡፡ ቁጣው ከልጁ ላይ ባለፈ ጊዜ ደግሞ አባት ይበልጥ ደስ ይለዋል፡፡ እንዲሁ እኛም ለኢአማንያን እናድርግ ልክ ልጅ እንዳለው አባት እንሁን፡፡ ይህን እንደስንቅ ይዘን ለእነርሱ የክርስቶስን ወንጌል እንስበክላቸው፡፡ ሁሉም አሕዛብ በእኛ ዘንድ እንደ ሕፃናት ናቸውና፡፡ እንዲህም እንደሆነ የእነርሱ አንዳንድ ጸሐፍት “ይህ ሕዝብ እንደ ሕፃን ነው ከአሕዛብም አንድም አረጋዊ ሰው የለም” ብለው ቃላችንን ያረጋግጡልናል፡፡ ሕፃናት የሚጠቅማቸውን ነገር ሊለዩ አይችሉም፤ አሕዛብን ሁል ጊዜ እንደ ሕፃናት ጨዋታ ወዳዶች ናቸው፡፡ በአፈር ላይ ይንደባለላሉ በከንቱ ነገር በቀላሉ ይወሰዳሉ ከንቱ በሆነም ነገር በፍቅር ይወድቃሉ፡፡ ለሕፃናት የሚጠቅም ነገርን ስንነግራቸው ጆሮ ሰጥተው አያዳምጡንም ከዚህ ይልቅ እኛ ስንናገር እነርሱ ይስቃሉ፡፡ አሕዛብም እንዲሁ ናቸው፡፡ እኛ ስለመንግሥተ ሰማያት ስንሰብክላቸው እነርሱ ይስቃሉ፡፡ ከሕፃናት አፍ በብዛት የሚወርደው ለሃጭ ምግቡ ላይ ሲያርፍ ምግቡን እንዲያበላሸው እንዲሁ ከአሕዛብ አንደበት የሚወጡ ቃላት ከንቱዎችና የረከሱ ናቸው፡፡

ለሕፃናት የሚስፈልጋቸውን ምግብ እንኳ ብንሰጣቸው ክፉ የሆነ ቃላት ከአንደበታቸው እያወጡ ሊነጫነጩብን ይችላሉ እኛም እነርሱን በመታገሥ እናሳልፋቸዋለን፡፡ ሕፃናት አንድ ሌባ ወደቤታቸው ገብቶ የቤቱ ቁሳቁሶችን እየወሰደ ቢያዩት ዝም ብለው ከመመልከትና እንደ ተባባሪ ወገን ሆነው ሲስቁ ከመገኘት ባለፈ እርሱን አይቃወሙትም፡፡ ነገር ግን እነርሱ ከሚጫወቱበት እቃ አንዱ የተወሰደባቸው እንደሆነ የወሰደባቸው ሰው ለመጉዳት ሲጥሩ ሲያለቅሱና በንዴት መሬቱን ሲጠበጥቡት እናስተውላቸዋለን፡፡ አሕዛብም እንዲሁ ናቸው፡፡ ሰይጣን ነፍሳቸውን የሚጠቅመውን መንፈሳዊ ሀብት ሲዘርፋቸው ከዚህም አልፎ ለሕይወታቸው አስፈላጊ የሆነውን ሲያሳጣቸው እያዩ ይስቃሉ፡፡ እንዳውም ከእርሱ ጋር እንደ ጓደኛ ሲተባበሩት ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ከእነርሱ እንደ ሕፃን መጫወቻ የተናቀን እቃን ሲወስድባቸው ቢመለከቱ ልክ እንደ ሕፃን ይጮኻሉ ያነባሉ፡፡ ሕፃናት ራቁታቸውን ስለመሆናቸው እንደማያስተውሉ አሕዛብም እንዲሁ ናቸው፡፡ ስለዚህም ሕጋዊው ተራክቦው እነርሱን ሲያሳፍራቸው ሕገወጡ መዳራት ግን አያሳፍራቸውም፡፡

እናንተ በዚህ ትምህርቴ ልትረኩና ደስታችሁን በእልልታ ልትገልጡልኝ ትችሉ ይሆናል ነገር ግን ከደስታችሁ ጋር በእነርሱ ተግባር ተስባችሁ እንዳትወሰዱ ለራሳችሁ ጥንቃቄን እንድታደርጉ ልመክራችሁ እወዳለሁ፡፡ ስለዚህም አዋቂዎች ትሆኑ ዘንድ እለምናችኋለሁ፡፡ እኛ እንደ እነርሱ ሕፃናት ከሆንን እንዴት አዋቂዎች እንዲሆኑ እነርሱን ማስተማር ይቻለናል? እንዴትስ እነርሱን ሞኝነት ከሆነው ከሕፃናዊ ድርጊታቸው መመለስ እንችላለን? ስለዚህ ተዋዳጆች ሆይ ወደ ክርስቶስ የእውቀቱ ከፍታ እንድንደርስና የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን እራሳችንን አዋቂዎች እናድርግ፡፡ ሰው እንሁን፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየስሱ ክርስቶስ ፍቅርና ርኅራኄ ለእግዚአብሔርና መንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡