መስቀል ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ቀን ፡ መስከረም 16/2004 ዓ.ም.

መስቀል ለእኛ ለኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ልዩ የሆነ መንፈሳዊ አንድምታ አለው ፡፡ በመስቀል እነሆ አሮጌው ሰዎችንን በመስቀልና ከጐኑ በፈሰሰው ውኃ ተጠምቀን በመቅበር አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለብሰን ተነሥተናል(ኤፌ.4፥22-24)፡፡ በመስቀል እርግማናችን ተወግዶ የኃጢአት ስርየትን አግኝተናል ፡፡ በመስቀሉ ላይ ከተሰዋው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ በመመገብ ከሚያፈቅረን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ፍጹም የሆነ ተዋሕዶን መሥርተናል(ማቴ.26፥26) ፤ እርሱ በእኛ ፣ እኛም በእርሱ የሆንበት ሰማያዊ ማዕዳችን መስቀሉ ነው (ዮሐ.6፥56) ፡፡

በመስቀሉ በአዳምና በሔዋን መተላለፍ ምክንያት በእኛ ላይ ጸንቶ የነበረው የፍርድ ትእዛዝ ተሽሯል(ቆላ.2፥14)፡፡ በብሉይ ለሙሴና ለእስራኤል ዘሥጋ እግዚአብሔር አምላክ በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ባለችው የቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ  ሆኖ በደመና አምድ ይገለጥላቸው ነበር(ዘጸአ.33፥9) ፡፡ ቢሆንም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የምታገባዋ ጎዳና ተዘግታ ነበር ፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ “ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል እርሱም ስለ ራሱና ስለሕዝቡ ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም ፤ ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳየናል”(ዕብ.9፥6-) ብሎ ተናገረ ፡፡

እነሆ እግዚአብሔር በደመና አምድ የሚገለጥበት የሥርየት መክደኛው ወይም የምህረት ዙፋኑ የተባለው የቃል ኪዳኑ ታቦቱ የመስቀሉ ምሳሌ ነው ፡፡ ምንም እንኳ እግዚአብሔር አምላክ በደመና አምድ የሚገለጥበት ሥፍራ የሥርየት መክደኛ (mercy seat) የምህረት ዙፋን ይባል እንጂ የጌታ ምህረት ለአዳም ልጆች ገና አልተፈጸመላቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን ወጣ ላለው ነገር ጥላ አለውና መስቀሉን ታቦቱ አድርጎ በእግዚአብሔርና በሰው ፣ በቅዱሳን መላእክትና በሰዎች መካከል የነበረውን የጥል ግርግዳ አፍርሶ እርቅን ከሰው ልጆች ጋር ፈጸመ ፡፡ የልዩነት መጋረጃው ተቀደደ መስቀሉንም ዙፋኑ በማድረግ በምህረት ለእኛ ታየ (ዕብ.4፥16) ፡፡

በመስቀሉ የእግዚአብሔር ልጅነትን ሥልጣን አገኘን(ዮሐ.1፥12) ፡፡ በመስቀሉ የርስቱ ወራሾች ፣ ቅዱስ ሕዝብና የመንግሥቱ ካህናት ተባልን(1ጴጥ.2፥9) ፡፡ በመስቀሉ አባ አባ የምንልበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበልን(ሮሜ.8፥15) ፡፡ በመስቀሉ የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደሶች ተሰኘን(1ቆሮ.3፥16) ፡፡ በመስቀሉ አካላችን የሆነውን በጥምቀት የለበስነውን ክርስቶስን የምናገለግልበትን ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎችን ተቀበልን(ገላ.3፥27፣ 1ቆሮ.12፥4-11)፡፡ እነሆ እኛ አሁን በክርስቶስ አዲስ ፍጥረታት ተሰኝተናልና አገራችንም በሰማያት ነውና እሳትም መንፈስም በሆነው መንፈስ ቅዱስ ተጠምቀን እሳታዊያንና መንፈሳውያን የሆኑትን መላእክትን መስለናቸዋልና ለአዲሱ ተፈጥሮአችን የሚስማማ ሰማያዊ ማዕድ ተዘጋጀልን(ኤፌ.2፥10 ፤ ፊልጵ.3፥20፤ ማቴ.22፥31) ፡፡ ማዕዱም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ነው፡፡ ይህ ሰማያዊ ማዕድ ለነፍሳችንም ለሥጋችንም ሕይወትና መድኃኒት ነው፡፡ በመስቀሉ ላይ በተሰዋው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙም ከመለኮታዊ ርስት ተካፋዮች (2ጴጥ.1፥4) ፡፡ ስለዚህም ነው እኛ ኦርቶዶክሳውያን የጌታችን ቅዱስ ሥጋ ክቡር ደሙ ለሚፈተትበት የመስቀሉ አምሳል ለሆነው  የምህረት ቃል ኪዳን ታቦቱ ልዩ አክብሮትና ፍቅር ያለን ፡፡

እኛ ኦርቶዶክሳውያን መስቀሉን ከክርስቶስ ክርስቶስን ከመስቀሉ ነጣጥለን አንመለከትም፡፡ ክርስቶስንም ስናስብ በመስቀሉ ስለእኛ የተቀበለውን መከራ እናስባለን ፡፡ መስቀሉንም ስንመለከት እርሱን ዙፋን አድርጎ ባሕርያችንን ያከበረውን ክርስቶስን አናስተውለዋለን ፡፡ መስቀል ማለት ለአንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ወንጌል ማለት ነው ፡፡ ከልደቱ እስከ ትንሣኤው መስቀሉን ጠቅሰን እንሰብካለን ፡፡ ይህ ነው የመስቀሉ ቃል ፡፡መስቀል ምንድን ነው ቢሉን ክርስቶስ ስለእኛ ድኅነት ሲል የተሰቀለበት የክብር ዙፋኑ ነው እንላቸዋለን ፡፡ ማን ነው እርሱ ቢሉን የባሪያውን መልክ ይዞ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው እግዚአብሔር ቃል ነው ብለን መልስ እንሰጣቸዋለን ፡፡ ስለምን በመስቀል ላይ መዋል አስፈለገው ብለው ቢጠይቁን በአዳም መተላለፍ ምክንያት በእኛ ላይ የተፈረደውን የሞት ፍርድ በሞቱ ሽሮ ሕይወትን ሊሰጠን እንላቸዋለን፡፡ ሞቶ ቀረ ወይ ብለው ቢጠይቁን ደግሞ ”ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጉታላችሁ ተነሥቶአል”(ሉቃ.24፥5)እንላቸዋልን፡፡ የመስቀሉ ቃል ለእኛ ጥልቅ የሆነ ትርጉም አለው ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የቆሮንቶስ መልእክትን በተረጎመበት በአራተኛው ድርሳኑ  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና ፡፡ የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ ፣ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና ፡፡ ጥበበኛ የት አለ ? ጻፊስ የታለ ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገውም? ” (1ቆሮ.1፥18-20) ብሎ የተናገረውን ኃይለቃል ሲተረጉም እንዲህ ይላል ፡፡ “በጽኑ ደዌ የተያዘና በጣር ላይ ላለ ሕመምተኛ ጤናማ የሆነ ምግብ አያስደስተውም ፤ ወዳጆቹንና ዘመዶቹን እንደታላቅ ሸክም ይቆጥራቸዋል ፡፡ ለእርሱ ያላቸውንም መቆርቆር ፈጽሞ አያስተውልም ፤ ይልቁኑ ሰላምን እንደሚነሡት ቆጥሮ ይጠላቸዋል ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጠባይ በኃጢአት ምክንያት በነፍሳቸው በጠፉት ላይም ይታያል ፡፡

እነዚህ ወገኖች ወደ ድኅነት የምትወስዳቸውን ጎዳና ፈጽመው አያውቋትም ፡፡ ይህ ጤናማ ከሆነ ተፈጥሮ የሚመነጭ አይደለም ከተያዙበት በሽታ እንጂ፡፡ እነዚህ ወገኖች ልክ እንደ አእምሮ ሕመምተኛ ሰው ስለእነርሱ መዳን የሚያስቡላቸውን ይጠላሉ፡፡ ከዚህም አልፈው በእነርሱ ላይ ጥቃትን ለማድረስ ይነሣሣሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጠባይ በኢአማንያንም ላይ የሚታይ ጠባይ ነው፡፡እነዚህ ወገኖች እነርሱን የሚያስቱዋቸውን ከመጠን በላይ ይወዱዋቸዋል እነርሱንም ለመገናኘት ይናፍቃሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች መልካም ወዳጆቻቸውን ለይተው ለማወቅ አለመቻላቸው በሽታው በእነርሱ ላይ ምን ያህል እንደከፋ የሚያሳይ ልዩ ምልክት ነው፡፡ ይህ በአሕዛብም ላይ የሚታይ ነው ፡፡

ስለዚህ ወዳጆች ሆይ እንትጋ፡፡ አዎን ከቤተሰቦቻችንም በላይ ስለእነርሱ መዳን እንሥራ ስለእነርሱም አብዝተን እንጸልይ ፡፡ ምክንያቱም ለሁሉ ከመጣው ድኅነት ርቀዋልና ፡፡ሰዎችን ሁሉ ወደ ድኅነት ከማድረስ አንጻር አንድ ሰው ሰውን ሁሉ ከማፍቀሩ በላይ ቤተሰቡን ሊያፈቅር ሊያፈቅራት አይገባውም፡፡ ስለዚህ ለነገሮች ሁሉ ብልህ እንሁን ወይም እንደችሎታችን መጠን እንድከም፡፡ “የመስቀሉ ቃል በራሱ ኃይልና ጥበብ ሆኖ ሳለ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት … ነውና” ተብሎ እንደተጻፈ ለእነርሱ ለጥፋት  ሆኖባቸዋልና እናልቅስላቸው፡፡

ነገር ግን ከመካከላችን አንዳንዶች መስቀሉ በአሕዛብ ሲዘበትበት ተመልክተው ስለመስቀሉ ቀንተው የአሕዛብን ፍልስፍና  በመጠቀም ፈላስፎችን ሊረቱ የሚተጉ ክርስቲያኖች ነበሩና እንዲህ ዓይነት ወገኖችን ቅዱስ ጳውሎስ ሊያጽናናቸው በመሻት የአሕዛብ ፍልስፍና ከንቱ እንደሆነ ለማስረዳት ሲል ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፡፡ ከሚጠፉት ወገኖች ዘንድ የሆኑ ግን ይህንን ታላቅ ምሥጢር መረዳት አልተቻላቸውም፡፡ ምክንያቱም ከእነርሱ አጠገብ ያሉት ፈላስፎችና ራሳቸው የአእምሮ ሕመምተኞች ናቸውና፤ ወደ ጤንነት የሚያመጣቸውን መድኅኒት ፈጽመው ጠልተውታልና፡፡

ነገር ግን ሰው ሆይ “የባሪያውን መልክ ይዞ ተገኘ”(ፊልጵ.2፥7) ይላልና ክርስቶስ የባርያውን አርዓያ ይዞ በመገኘቱ ስለእኛ ድኅነት በመስቀል ላይ መቸንከሩ እንዲሁም ሞትን ድል አድርጎ ስለመነሣቱ በአሕዛብ ፍልስፍና እንዴት ብለህ ማስረዳት ትችላለህ? ለእግዚአብሔር አምላክ አምልኮን ማቅረብ ፣ ለሰዎች ልጆች ስላለው ጥልቅ ፍቅር ማድነቅ ይገባሃል እንጂ አባት ወይም የልብ ወዳጅ ወይም ልጅ ለአባቱ የማያደርገውን ለአንተ አድርጎ በማግኘትህ በፍጹም ጥበብ የተሞላውን ተግባሩን እንደሞኝነት በመቁጠር በእርሱ ላይ ምላስህን ታንቀሳቅሳለህን? ደህና! ይህ ግን የሚያስገርም ነገር አይደለም፤ ወደ ድኅነት የሚመራቸውን ጉዳይ አለማስተዋላቸው በነፍሳቸው የመጥፋታቸው ምልክት ነው እንጂ ፡፡

ወገኔ ሆይ አጠገብህ ያሉ ኢአማንያን እውነት በሆነው በዚህ ጉዳይ ላይ ሲያፌዙ ብትመለከት እንግዳና አዲስ ክስተት እንደተፈጸመ ቆጥረህ ልትረበሽ  አይገባህም፡፡ ይህን ታላቅ ምሥጢር የሰዎችን የመረዳት አቅም ተጠቅመህ ማስረዳት አይቻልህም፡፡ እንዲህ ለማድረግ የሞከርኽ እንደሆነ ግን ውጤቱ ተቃራኒ ይሆንብሃል፡፡ እንዲህ ዓይነት ከሰው አእምሮ በላይ የሆነ ክርስቲያናዊ እውቀት በእምነት ብቻ የሚቀበሉት ነው፡፡ እስኪ ንገረኝ እግዚአብሔር ቃል እንዴት ሰው ሆነ? እንዴትስ ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ? ስለዚህ ጉዳይ በእምነት ከመቀበል ውጪ ሰዎችን በምክንያት ማስረዳት ይቻልሃልን?  እነዚህ ወገኖች በእምነት ይህን ካልተቀበሉት በቀር በዚህ ጉዳይ ላይ ማፌዛቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህም ነው የእግዚአብሔርን ሥራ ሰዎች በአእምሮ ጠባያቸው   ተደግፈው ለመመርመር በመሞከራቸው የጥፋት ልጆች ናቸው የሚባሉት ፡፡

ስለምን ነገሬን ለማስረዳት እግዚአብሔርን ብቻ እንደ ምክንያት እጠቀማለሁ? ይህ ዓይነት ነገር እግዚአብሔር  በፈጠራቸው ሥነፍጥረታትም ላይ የሚታይ አይደለምን ? ነገሮችን ሁሉ በምክንያት ለማስረዳት ለምትጥር ለአንተ  አንድ ሰው  እንዴት ብርሃንን ለማየት እንደምንችል ሊያስረዳህ ቢሞክር እርሱን አይደለም ብለህ ምክንያትን በማቅረብ ልትከራከረው ትችላለህን? ፈጽሞ አትችልም፡፡ ይልቁኑ አንድ ሰው ብርሃንን ለመመለከት ዐይኑን መክፈት ብቻ ይበቃዋል በማለት እውነታውን ብቻ ከማስቀመጥ ባለፈ  ዝርዝር ጉዳዩን በምክንያት ማስረዳት አይቻልህም፡፡

ለእያንዳንዱ ነገር ምክንያቱ ሊገለጥ ይገባዋል ለሚል ሰው ስለምን በጆሮአችን መመልከት አልቻልንም? ወይም በዐይናችን መስማት አልቻልንም? ወይም ስለምን በአፍንጫችን ማየት  አልቻልንም? ወይም በዐይናችን ማሽተት አልቻልንም? ብለን ብንጠይቀው መልሱን ከመመለስ ይልቅ እኛን እንዳላዋቂ ቆጥሮ በእኛ ላይ ሊሳለቅብን ይችላል ፡፡ ነገር ግን እኛ በእርሱ ላይ መልሰን አንሳለቅበትምን? ምክንያቱም ለእነዚህ  የስሜት  ሕዋሳቶቻች ሁሉ ምንጩ አንዱ የአእምሮ ክፍል ነውና፡፡ እንዲሁም አንዱ አካል ከአንዱ አካል እጅግ ተዛምዶ ያለው በመሆኑ ስለምን አንዱ አካል የሌላውን አካል ተግባር መሥራት ይሳነዋል ? ብለን ጥያቄ ብናቀርብለት ለዚህ ጥያቄያችን አሳማኝ ምክንያትን ሊያቀርብንልን  አይችልም ፤ ወይም ለዚህ ድንቅ ለሆነ ተፈጥሮ ስለአተገባበሩ ትንታኔ መስጠት አይቻለውም ፡፡ እኛም ይህን ለማስረዳት ብንዳዳ እርሱ መልሶ በእኛ ላይ አያፌዝብንምን? ስለዚህ ይህን ሁሉ በቀላሉ ማከናወን የሚቻለውንና የጥበብ ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔር ጉዳዩን እንተውለትና  እኛ የእርሱን ሥራ በአእምሮ ጠባያችን  ከመመርመር እንከልከል፡፡ ይህን በሁሉም የእግዚአብሔር ሥራዎች ላይ እናሳይ ፡፡  ከእኛ አእምሮ ጠባይ በላይ  ስለሆነው ሥራዎቹ እኛ ትንታኔ መስጠት አይቻለንም፡፡

የአሕዛብ ፈላስፎች ተሳልቆ ከአእምሮቸው የማስተዋል ማነስ የተነሣ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ ሞኝነት የተነሣ ነው እንጂ፡፡ ምክንያቱም ታላቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሥራ የሰው እውቀት ፈጽሞ ሊረዳው አይቻለውምና፡፡ተወዳጆች ሆይ እኔ “እርሱ ስለሰው ልጆች ድኅነት ተሰቀለ” ስል ፈላስፋው ደግሞ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? እርሱን ለስቅላት ሲነዱት መከላከል ያልቻለና ጽኑ ሕማምን የተቀበለ እንዴት ከዚህ በኋላ ከሞት ተነሥቶ ሌሎችን ሊረዳ ይቻላል?፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ሆኖ ቢሆን ኖሮ ከሞት በፊት አድርጎት ባሳየን ነበር ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ይህን በእርግጥ አይሁድም፡- “ሌሎችን አዳነ ራሱን ሊያድን አይችልም” ብለው ነበር፡፡ (ማቴ.27፥41-42) ይህ ፈላስፋ ደግሞ  “እርሱ ራሱን ማዳን ያልቻለ እንዴት ሌላውን ሊያድን ይችላል፤ ለዚህ ምንም ምክንያትን ልታቀርቡ አትችሉም፣ ለዚህ ምንም ምክንያት ሊኖራችሁ አይችልም ፤ ሊል ይችላል፡፡  አንተ ሰው ሆይ ያልከው በእርግጥ እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ እኮ ከሰው አእምሮ በላይ የሆነ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው፡፡ የመስቀሉ ኃይል በቃላት ሊገለጽ የማይችል እጅግ ግሩም ነው እንዴት ፍጥረታዊው አእምሮ ሊረዳው ይችላል፡፡

ሠለስቱ ደቂቅ ወደ እቶን እሳት ባይጣሉ ኖሮ በእነርሱ የተገለጠው የእግዚአብሔር ጠባቂነት አድንቆት ባልተቸረው ነበር፡፡ ወደ እቶን ሲጣሉ በእሳቱ ላይ በመረማመድ እሳቱን ድል እንደነሡት ታወቀ፡፡ የዮናስንም ታሪክ ስንመለከት ከሠለስቱ ደቂቅ በላይ የሚያስገርም ተአምር እንደተፈጸመ ልንመለከት እንችላለን፡፡ ዮናስ ምንም ግዙፍ በሆነው ዓሣ አንባሪ ቢዋጥም እርሱን ግን አልጎዳውም ነበር፡፡  እርሱ በዓሣ አንበሪው ባይዋጥ ኖሮ በእርሱ የተፈጸመው እጅግ አስገራሚ ተአምር ባልተደነቀ ነበር፡፡ እንዲሁ ነው በክርስቶስ የተፈጸመው፡፡ እርሱ ባይሞት ኖሮ ሙታን ከሞት እስራት እንደተፈቱና ወደ መንግሥቱ እንደፈለሱ ባልታመነ ነበር፡፡ ስለዚህም “ስለምን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ራሱን ከመስቀል ሞት አላዳነም ?” ብለህ አትናገር፡፡ እርሱ ሞትን ድል ሊነሣ ሊሞት ስለእኛ መዳን መሞትን መረጠ፡፡ እርሱ ከመስቀሉ ላይ ራሱን ሊያወርድ ያልቻለበት ምክንያት ችሎታ ስለሌለው አይደለም ፤ ስላልፈገ ነው እንጂ፡፡ ሞት ሊቋቋመው ያልቻለ እርሱን እንዴት እጆቹን የተቸነከሩት ችንካሮች  እርሱን አስረው ሊይዙት ይችላሉ ?

የክርስቶስ ዓላማ ለእኛ ለክርስቲያኖች በጣም የታወቀ ነው፡፡ እኛ እንደ ኢአማንያን አይደለንም ፡፡ ስለዚህም  ቅዱስ ጳውሎስ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና ፡፡ የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ ፣ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና ፡፡ ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የታለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገውም? ” አለን (1ቆሮ.1፥18-20)  ቅዱስ ጳውሎስ ለዚህ ዓለም ፈላስፎች ምክንያትን በመደርደር ሊከራከራቸው አልሞከረም ፡፡ ነገር ግን ትምህርቱን ለማስረዳት ቅዱሳት መጻሕፍትን አንደ መረጃ ጠቀሰ እንጂ፡፡ ስለዚህም በድፍረትና በታላቅ ቃል “ጥበበኛ የት አለ ? ጻፊስ የት አለ ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት አላደረገውምን ?በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም በጥበቡዋ ስላላወቀች በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ለራሱ ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃዱ ሆኖአልና” ብሎ ተናገረ፡፡ “የጥበበኞችን ጥበብ ያስተዋዮችን ማስተዋል አጠፋለሁ ተብሎ ተጽፎአልና” ፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ “ጥበበኛ የት አለ ? ጻፊስ የት አለ ? በማለት የአይሁድ ምሁራንንም የአሕዛብ ፈላስፎችንም በዚህ ቦታ እንዳዋረዳቸው እንመለከታለን ፡፡ የትኛው የአሕዛብ ፈላስፋ ወይስ የአይሁድ መምህር ነው እኛን ወደመዳን እውቀት የመራና  እውነትን የገለጠልን ? ማንም የለም ፡፡ ከሰዎች ወገን ወደ ድኅነት ጎዳና የመሩን ከዓሣ አጥማጆቹ ሐዋርያት በቀር ከአይሁድ ምሁር ወይም ከአሕዛብ ጠቢብ ማንም የለም፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ  ነገሩን ሲያጠቃልልና የእነርሱን ትምክህት ሲያዋርደው “እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገውም” ? አለ፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ምክንያቱንም አስቀመጠ ፡፡ “በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም በጥበቡዋ ስላላወቀች” አለ፡፡ ስለዚህ በመስቀሉ የእርሱን ጥበብ አሳየን፡፡ ሐዋርያው  “በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት” ሲል ምን ማለቱ ነው ? በፈቃዱ ራሱን በሥነ ፍጥረቱ የገለጠበትን ጥበብ ማለቱ ነው፡፡ ከሚታየው ነገር ተነሥተው ለፈጠራቸው አምላክ አድናቆት እንዲኖራቸው በመሻት አስቀድሞ እግዚአብሔር ራሱን በሥነ ፍጥረቱ ገልጦ ነበር ፡፡

እንደ እውነቱ  ከሆነ የዚህ ሰማይ ተፈጥሮው ድንቅ አይደለምን ? የምድሪቱስ ስፋት የሚገርም አይደለምን ? እነዚህን የፈጠራቸው አምላክ በእውነት ኃያል አምላክ ነው ፡፡ ሰማያቱ በእርሱ መፈጠራቸው ብቻ አይደለም የሚደንቀው ነገር ግን በቀላሉ እነርሱን በመፍጠሩም ጭምር እንጂ ፡፡ የምትታየውንም እህቺ ምድርም በእርሱ መፈጠሩዋ ብቻ አይደለም የሚደንቀው ፣ ካለመኖር ወደ መኖር ማስገኘቱም ጭምር  እንጂ ፡፡ ስለዚህም ጉዳይ በነቢዩ ዳዊት አስቀድሞ “አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው ፡፡”(መዝ.101፥25) ተባለ፡፡  ኢሳይያስም “ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው ፣  እንደ ድንኳንም ለመኖሪያ የሚዘረጋቸው ፣ አለቆችንም እንዳልነበሩ የሚያደርጋቸው የምድርንም ፈራጆች እንደ ከንቱ ነገር የሚያደርጋቸው እርሱ ነው ፡፡”አለን (ኢሳ.40፥23)

በዚህ ጥበቡ ዓለም እግዚአብሔርን ለማወቅ ባለመፈለጉዋ ምክንያት ሞኝነት በሚመስል መልኩ ያም ማለት በወንጌል እምነት ወደ ራሱ ሊያቀርባቸው ወደደ ፡፡ የእግዚአብሔር ጥበብ ባለበት የሰው ጥበብ እንደ ምናምን ይቆጠራል፡፡ ከዚህ አስቀድሞ ግን ዓለምን እንዲህ ግሩምና ድንቅ አድርጎ የፈጠረ አምላክ ማንም  ሊቋቋመው የማይቻለው ብርቱ አምላክ እንደሆነና ከመረዳት ያለፈ ጥበብና እውቀት ያለው ፈጣሪ እንደሆነ በሥነ ፍጥረቱ ለማስረዳት ሞክሮ ነበር፡፡ ከዚህም ተነሥተን እርሱን ወደ መረዳት መድረስ ነበረብን፡፡ አሁን ግን በሥነፍጥረቱ እርሱን ማወቅ ስላልቻልን በምክንያት ሳይሆን በእምነት እኛን ለማዳን ፈቀደ ፡፡ ሐዋርያት ጠቢባን ስለነበሩ አልነበረም የተመረጡት ፤ እምነት ስላላቸው እንጂ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔርን በመመራመር ሳይሆን የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ በእምነት በመቀበላቸው ምክንያት በጥበባቸው ከአሕዛብ ጠቢባን በላይ አዋቂዎች ሆኑ፡፡ የእርሱ ሥራ ከሰዎች የማወቅ ችሎታ በላይ እጅግ ታላቅ ግሩም  ነው፡፡  ነገር ግን “እንዴት እግዚአብሔር የአሕዛብን ጥበብ አጠፋ ? ቢባል ከቅዱስ ጳውሎስና ከሌሎችም ሐዋርያት እንደተማርነው የአሕዛብን ጥበብና ማስተዋል የማይጠቅምና የማይረባ በማድረግ ነው፡፡ የምሥራቹን ወንጌል የሰው ልጅ እንዲሰማ በማድረግ ጠቢባን በእውቀታቸው እንዳይጠቀሙ ያልተማሩትም  ባለማወቃቸው እንዳይጎዱ አደረጋቸው ፡፡

ይቀጥላል……..