*መስቀላችሁ የቃል ኪዳን ምልክታችሁ*
ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ይህ ኃይለ ቃል ከማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ዋና ጸሐፊና የግቢ ጉባኤያት ማደራጃ ማስተባባሪያ ዋና ክፍል ሓላፊ ከአቶ እስጢፋኖስ ታፈሰ ንግግር የተወሰደ ሲኾን፣ ይኸውም የአቃቂ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በተመረቁበት ዕለት ተገኝተው ያስተላለፉት መልእክት ነው፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል፣ በአዲስ አበባ ማእከል ግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያና በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ ማእከል አማካይነት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በአቃቂ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ግቢ ጉባኤ በምሕንድስና የትምህርት ዘርፍ ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁና በማኅበሩ የሚሰጡ ልዩ ልዩ የትምህርተ ሃይማኖት ኮርሶችን ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች አባቶች ካህናት፣ የማኅበሩ አገልጋዮችና የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ ሦስተኛ ፎቅ አዳራሽ ተመርቀዋል፡፡
የምረቃ ሥርዓቱ በአባቶች ጸሎት ከተከፈተ በኋላ *ፍሬ ፃማከ ተሴሰይ፤ የድካምህንም ፍሬ ትመገባለህ* /መዝ.፻፳፯፥፪/ በሚል ኃይለ ቃል በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ ትምህርተ ወንጌል ከተሰጠ በኋላ በተመራቂዎች የበገና ዝማሬ የቀረበ ሲኾን፣ በመቀጠልም በግቢ ጉባኤው በልዩ ልዩ ክፍሎች በሥራ አስፈጻሚነት በትጋት ሲያገለግሉ የቆዩና በተቋሙ በተማሩት የትምህርት ዘርፍ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ አምስት ተመራቂዎች ከአባቶች እጅ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡
አቶ እስጢፋኖስ ታፈሰ በምረቃ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የማኅበሩን መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት *ይህ ዛሬ የተቀበላችሁት መስቀል ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለምትገቡት ቃል ኪዳን ምልክትና መክሊታችሁ መኾኑን በመገንዘብ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ድረስ መንፈሳዊ ሀብቷን ሳትነፍግ ያሳደገቻችሁን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በዕውቀታችሁ፣ በገንዘባችሁና በጉልበታችሁ እንድታገለግሉ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጠበቀ መልእክቷን ታስተላልፋለች* በማለት ማኅበሩን ወክለው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በተጨማሪም *ተመራቂዎች በሰንበት ትምህርት ቤቶችና በሰበካ ጉባኤያት የላቀ ተሳትፎ እንድታደርጉ፤ በምትሠማሩበት የሥራ መስክም ክርስቲያናዊ ጨዋነትን በማንጸባረቅ ታታሪነትን፣ ታማኝነትን፣ ሥራ አክባሪነትን፣ ቁጥብነትን በተግባር በመፈጸምና አገራችንን ከልዩ ልዩ ችግሮች ለማላቀቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ ኹሉ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታችሁን እንድትወጡ፤ እንደዚሁም በየማእከላት፣ ወረዳ ማእከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች በማገልገል በግቢ ውስጥ የነበራችሁን መንፈሳዊ ሕይወት እንድትቀጥሉ አደራ እንላለን* ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በአባቶች ጸሎት የምረቃ ሥርዓቱ ተፈጽሟል፡፡
የአቃቂ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ግቢ ጉባኤ ከተቋቋመ አምስት ዓመታትን እንዳስቈጠረና ማኅበረ ቅዱሳን የግቢውን ተማሪዎች ሲያስመርቅም ዘንድሮ ሁለተኛ ጊዜው እንደ ኾነ በማኅበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማእከል የግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ መደበኛ አስተባባሪ ዲ/ን ዘመኑ ገረመው ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸውልናል፡፡