መልካም አስተዳደር እና ቤተ ክርስቲያን
ክፍል ሁለት
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ታኅሣሥ ፲፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
፪. የመልካም አስተዳደር እጦት በቤተ ክርስቲያን፡-
መልካም አስተዳደር ምን ማለት እንደ ሆነ ከዚህ በፊት ባቀረብነው ክፍለ ትምህርት ለመግለጽ ሞክረናል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ መሆኑ እንደማያጠያይቅም ተመልክተናል፡፡ ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያናችንን ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከመመሪያ እስከ አጥቢያ የመልካም አስተዳደር እጦት በእጅጉ እየፈተናት መሆኑን በርካታ አካላት ይገልጻሉ፡፡ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል መጋቢት ፳፻፯ ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ላይ ‹‹የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንዲሁም የወደ ፊት ሥጋቶች›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናት ላይ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ለመውደቅ መፍገምገም ጀምራለች›› ሲሉ የጉዳዩን ክብደት አመልክተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ለሥራ ኃላፊዎች ሐምሌ ፱ ቀን፣ ፳፻፭ ዓ.ም በተሰጠ ሥልጠና ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር እየከፋ ስለመሄዱ አስረግጠው ተናግረው ነበር፡፡
አቡነ ሳሙኤል ባቀረቡት ጥናት የታደሙ አካላትም በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኗ በዕቅድና በሕግ እየተመራች አለመሆኑን፣ እንዲሁም በጥራዝ ነጠቆች እየተደፈረች፣ ደካማ አመራርና አንዱ ከሌላው የሚጣረስ የሥራ ኃላፊነት መኖር፣ መስመር የለቀቀ ዘረኝነት፣ ልቅ ሙስናና ዝርፊያ መስፈኑንና ዘመናዊ አስተዳደር እንዳይኖር የሚቃወሙ አካላት ጭምር መብዛታችውን አንሥተው ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
ጥናት አቅራቢው አባት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በወቅቱ ዋና ዋና ያሏቸውን ግኝቶች ሲያስረዱ፡-
- ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ የመዋቅራዊ አደረጃጀት ክፍተት መኖሩን፤
- ተጠያቂነት የሌለበት ኃላፊነት መስጠት እየተለመደ መምጣቱን
- በዕውቀት ላይ ያልተመሠረተ የሰው ኃይል ምደባ መለመዱን
- የሥራና ሠራተኛ አለመገናኘት (የሥራ ድርሻን ለተገቢው ሰው ያለመስጠት)
- በመንደርተኝነት መሳሳብና ሀብት ለማፍራት መሯሯጥ መብዛቱን፣
- ኋላ ቀር የፋይናንስ ሥርዓትና የንብረት አያያዝ መኖሩ እና መሰል በርካታ
- የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቤተ ክርስቲያንን ገፍተው ሊጥሏት እንደሆነ በጥናታቸው ገልጸዋል፡፡
ቀሲስ ወንድም ስሻ አየለ የተባሉ አባት በበኩላቸው ‹‹የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መሻሻል ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ›› በሚል ርእስ ባዘጋጁት የጥናት ሰነድ ‹‹ቀኖናዊነትን አጽንቶ የዛሬውን ትውልድ ለመምራት ጥብቅና ዘመናዊ አስተዳደር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ይህን እንደ ሽፋን ሊጠቀምበት የሚፈልግ የእምነት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም ፍላጎት ያለው ሁሉ ለራሱ ጥቅም እየገባ ያሻውን እንዲያደርግ ምቹ ሆኖ መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግር ደረጃው ይለያያል እንጂ በሁሉም የቤተ ክርስቲያን መዋቅር የሚታይ ነው፡፡ በአዲስ አበባና በአንዳንድ አህጉረ ስብከት በተለይም ከፍተኛ ሀብት ባላቸው አድባራትና ገዳማት ችግሩ ከፍተኛ ነው፡፡
፪.፩. የቤተ ክርስቲያን መልካም አስተዳደር እጦት መንሥኤዎች፡-
ቤተ ክርስቲያንን እግር ከወርች ይዞ አላራምድ ያላት የመልካም አስተዳደር ችግር ብዙ መንሥኤዎች ይኖሩታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸው፡፡
፩ኛ. የመዋቅር ችግር
ይህም ማለት መዋቅራዊ አደረጃጀቱ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱንና በየደረጃው ያሉ የመምሪያና የአድባራት ኃላፊዎችን ሚና ቁልጭ አድርጎ የሚያመለክት አለመሆኑ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ዕውቀት አይኖረውም፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን አመራር ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን እንዲያስተዳደሩ፣ ሌላው ደግሞ የፋይናንስ፣ የንብረት፣ የሰው ኃይል አስተዳድሩን እንዲሁም ልማቱን ወቅቱ በሚፈልገው ዕውቀትና የሰው ኃይል እንዲመራ አለመደረጉ በዕለት ዕለት እንቅስቃሴያችን የምንታዘበውና ከላይ የጠቀስናቸው ጥናት አቅራቢዎችም የጠቆሙት ሐሳብ ነው፡፡ አሁናዊውን የቤተ ክርስቲያን የተወሳሰበ አስተዳደራዊ ችግር ለመፍታት ከመንፈሳዊ ዕውቀትና መንፈሳዊነት ባሻገር ጊዜው በሚጠይቀው የአስተዳደር ጥበብና ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
፪ኛ.የምእመናን ተሳትፎ አናሳ መሆን
የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ማኅበረ ካህናትንና ማኅበረ ምእመናንን ያቀፈ ነው፡፡ ስለሆነም ምእመናን በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ መተኪያ የሌለው ሚና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አባቶቻችን ሥጋዊውንም፥ መንፈሳዊውንም አስተዳደር ስለሚመሩ ከአስተዳደሩ ስፋትና ወቅቱ ከወለደው የአስተዳደር ጥበብ የተነሣ ክፍተቶች ስለሚፈጠሩ ይህን ክፈተት ለመሙላት ምእመናን የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ የሥራ ክፍፍልን ያስተማረች ቤተ ክርስቲያን አሁን ላይ አስተዳደራዊ ፈተናዎች የበዙበት በመሆኑ ሕግ የማውጣት፣ ሕግ የማስፈጸም እና ሕግ የመተርጎም ሥራ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ሙያው ያላቸውንና የተመሰከረላቸው ምእመናን ማሳተፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ይሞላል፡፡ ይህን በተመለከተ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልም በጥናታቸው ‹‹ለምእመናን የተሰጠ ሥልጣን ስለሌለ ይህም ተጠያቂነት የሌለበት አሠራር እንዲሰፍን አድርጓል›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊው ካህን የሙሴ አማት ዮቶር ሙሴ ሕዝቡን በመዳኘትና በመምራት በደከመና ሕዝቡ በተጉላላ ጊዜ ማድረግ ያለበትን እንደሚከተለው መክሮታል፡፡
‹‹……አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም፡፡ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም፡፡……አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን፤ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ፤ ሥርዓቱንም ሕጉንም አስተምራቸው፤ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያደርጉትንም ሥራ ሁሉ አሳያቸው፡፡….ከሕዝቡ ሁሉ ዐዋቂዎችን፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፣ የታመኑ፣ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ…..በሕዝቡ ላይ ሁል ጊዜ ይፍረዱ፤…እነርሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ፤ ለአንተም ይቀልልሃል፡፡….መቆም ይቻልሃል፤ ሕዝቡም በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል…›› ሲል መፍትሔውን ነግሮታል፡፡ (ዘፀ.፲፰፥፲፯-፳፫)
ችግሩን ለመቅረፍ አባቶቻችን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሕግ አውጪም፣ ሕግ አስፈጻሚም፣ ሕግ ተርጓሚም ሆነው፣ ሃይማኖታዊውንም ሥጋዊውንም ጉዳይ ሊያስተዳድሩና ሊመሩ አይገባም፡፡ የአብያተ ክርስቲያን አስተዳደዳሪዎችም ሙያ የሚጠይቀውን ሥራ ለባለሙያው አይተውም፡፡ ከልማት ኮሚቴ፣ ከሰበካ ጉባኤ፣ እንዲሁም በየደረጃው የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉ መንፈሳዊ ማኅበራት ጋር የሚፈጠረው ግጭት ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ይህ ማለት ለምእመናን ምንም ሥልጣን አልተሰጠም ማለት ሳይሆን በቂ አለመሆኑንና ተግባራዊነቱም ችግር የሚስተዋልበት መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡
፫ኛ. የመንግሥት ጣልቃ ገብነት
በቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከቀድሞ ጀምሮ ችግር ሆኖባት የዘለቀ ጉዳይ ነው፡፡ በንጉሡ ዘመን ቤተ ክርስቲያን እና መንግሥት እንዳይለያዩ በማድረግ ብዙ የሃይማኖት መሪዎች በንጉሡ ይሾሙ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ የደርግ መንግሥት ሲገባ ቤተ ክርስቲያንን ከንጉሡ ጋር በመፈረጅ ሀብት፣ ንብረቷን ወርሷል፡፡ ኢሕአዴግ መንግሥትም በከፍተኛ ደረጃ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መዳከምና ለመልካም አስተዳደር ችግር እንድትጋለጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን አሁንም የተላቀቀችው ችግር ባለመሆኑ ዘረኞች፣ ሙሰኞች፣ ተሐድሶ መናፍቃን እንዲሁም ፖለቲከኞች በመንግሥት ትከሻ ተጭነው ቤተ ክርስቲያን በመግባታቸው፣ ሕዝብ በፖሊስ የሚያስደበድቡ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ቢሮዎችን፣ የማኅበረ ቅዱሳን ማእከላትን የሚያሳሽጉ፣ የሰበካ ጉባኤ እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችን የሚያሳስሩ ሰው የሚያስፈራሩ የግል ፖሊስ ጥበቃ ያላቸው አማሳኝ ቡድኖች ከዚህም ከዚያም የሚታዩ መሆናቸው የአደባባይ እውነት ነው፡፡
፬ኛ. ዕውቅና ያለው የራሷ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት አለመኖር
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፈንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን?…በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፤ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን? እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው፡፡ ብትበደሉ አይሻልምን?ብትታለሉስ አይሻልምን?›› ይላል፡፡ (፩ኛቆሮ.፮፥፩-፯)
ቤተ ክርስቲያን ዶግማዋና ሥርዓቷ በሚፈቅደው አግባብ አገልጋዮቿንና ምእመኖቿን የምትዳኝበት ፍርድ ቤት የላትም፡፡ የአገልጋዮች ጉዳይ ጭምር የሚዳኘው በመንግሥት ፍርድ ቤት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቀኖና ጥሰትና በእምነት ችግርና በሌሎችም ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያን ያገደቻቸው አካላት ተመልሰው እንዲገቡና የብልሹ አስተዳደር ምክንያት ሆነው እንዲዘልቁ ከማድረጉም በላይ ቤተ ክርስቲያናንን ለትችት ዳርጓታል፡፡
፭ኛ.ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ድልድል አለመኖር
ይህ መሠረታዊ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በየደረጃው የሚሾሙና የሚቀጠሩ ሰዎች ማንነት፣ ብቃት፣ መንፈሳዊነት ሁልጊዜ ጥያቄ ይነሣበታል፡፡ ምደባው፣ ዝውውሩና ቅጥሩ በጣም ግልጸኝነት የጎደለው፣ ከወንዜነትና ከጥቅም ጋር የተሳሰረ፣ “ምን ያህል ተምረሃል? ሳይሆን ምን ያህል ትከፍላለህ?” የሚባልበት፣ እምነቱ፣ ሥነ ምግባሩ፣ እውቀቱ ግምት ውስጥ የማይገባበት፣ ተጠያቂነት እና ግልጸኝነት የጠፋበት ቅጥር፣ ዝውውር፣ ሹመት የሚሰጥበት መሆኑን መረዳት አይከብድም፡፡ ‹‹በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል›› እንዳለ ሐዋርያው ብዙ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ሳይቀር በየመድረኩ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ብልሹ አሠራር እያነሡ ምእመናንን አንገት ሲያስደፉ የነበረው የሚረሳ አይደለም፡፡ (ሮሜ ፪፥፳፬)
በየጊዜው ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ባነር አሠርተው ሰልፍ የሚወጡ አገልጋዮችና ምእመናን ሁሉ ስናስታውስ የሚያመለከቱት ይህንኑ እውነት ነው፡፡ የሀብት ክፍፍሉም ፍትሐዊ አለመሆኑ ምንም አጠያያቂ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሀብት ቢኖራትም ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ግን ማስቀደሻ አጥተው ተዘግተዋል፡፡ ነጠላ ለብሰው የሚቀድሱ ካህናት እንዳሉ የሰማ ጆሮ አዲስ አበባ ያለውን ማስቀመጫ ያጡ አልባሳትና ንዋያተ ብዛት ማሰብ ያማል፡፡
ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ቀዳሽ አጥተው፣ ብዙ ተማሪዎች መምህር አጥተው ብዙ መምህራን ምግብ አጥተው ጉባኤ ታጥፏል፡፡ ወንጌል ተሰብኮበት የማያውቅ ዐውደ ምሕረት ብዙ ነው፤ ብዙ ገዳማት ተፈተዋል፡፡ ሀብቷ ለገዳሞቿ፣ ለምእመናን፣ ለአብነት ትምህርት ቤቶቿ አልደረሰም፡፡ ሁሉም ከተማ ገብተዋል፤ ሁሉም አንድ ቦታ ላይ ተከማችተዋል፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ እና አንዳንድ ትልልቅ ከተሞች ላይ በወር አንድ ጊዜ እንኳን የአገልግሎት ተራ የማይደርሳቸው አገልጋዮች ብዙ ናቸው፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ችግረኛ ገዳማትና አድባራት፣ ጥቂት የተትረፈረፈ ሀብት ያላቸው ባለጸጋ ገዳማትና አድባራት፣ ሊቀምሱት፣ ሊለብሱት ያጡ ብዙ መነኮሳትና ካህናት እንዲሁም በቅንጡ መኪና የሚንሸራሸሩ ጥቂት መነኮሳትና ካህናት፣ የቤተ ክርስቲያኗን ችግር ለመቅረፍ፣ ክብሯን ለማስጠበቅ፣ ገዳማቷ፣ አብነት ትምህርት ቤቶቿ እንዳይፈቱ ቆላ ደጋ የሚሉ፣ ከኪሳቸው ችግሯን ለመቅረፍ የሚተጉ ምእመናን ያሏት ቤተ ክርስቲያን ገንዘቧን መዝብረው፣ ቅርሷን ሸጠው በዓለም ጌጥና ምቾት የሚዘባነኑ ጥቂት ግለሰቦች ያሏት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የብልሹ አስተዳደር መገለጫው ይህ ነው፡፡
ውድ የዚህ ጽሑፍ ተከታታዮች! የመልካም አስተዳደር መንሥኤዎች እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ እንመለስበታለን፡፡ እስከዚያው መልካም ሳምንት!