‹‹ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተውአቸው፤ አትከልክሉአቸውም›› (ሉቃ.፲፰፥፲፮)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ግንቦት ፲፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
አእምሯቸው ብሩህ ልቡናቸው ንጹሕ የሆኑት ሕፃናት ተንኮል፣ ቂም፣ በቀል የሌለባቸው የዋሃን ናቸው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕፃናትን ወደ እርሱ እንዲያመጡ አድርጎ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ እንደ እነርሱ (ሕፃናት) ተንኮል፣ ቂም፣ በቀልን በልቡና መያዝ እንደማያስፈልግ ከክፋት መራቅ እንዳለብን አስተማረባቸው፡፡
ወላጆች እንደ ልማዳቸው ለማስባረክ ሕፃናትን ወደ ጌታችን ሲያመጧቸው ደቀ መዛሙርቱ ‹‹ለምን አመጣችሁ!›› ብለው ወላጆችን በተናገሩ ጊዜ ጌታን ‹‹ተዋቸው›› አለ፤ ደቀ መዛሙርቱ መከልከላቸው ትምህርት ያስፈቱናል (ሕፃናት ናቸውና ይረብሻሉ) በማለት ነው፡፡ ጌታችን ግን እንዲመጡ አደረጋቸው፤ ባረካቸው፤ እነዚህ ሕፃናት ቁጥራቸው ከ፪፻ መቶ በላይ እንደሆነ መተርጉማነ አበው ያብራራሉ፤ በዚያን ጊዜ ከጌታችን የተባረኩት ሕፃናት አድገው ጳጳስ፣ ኤጲስ ቆጶስ ሆነዋል፤ ከፍጹምነት ማዕረግ ደርሰዋል፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ፲፱፥፲፭)
ውድ ክርስቲያኖች! ልጆቻችን በሥነ ምግባር ታንፀውና በሃይማኖት ጸንተው ያድጉ ዘንድ ከቤተ እግዚአብሔር ልናመጣቸው በአባቶች ካህናት ልናስባርካቸው ያስፈልጋል፤ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆኑትን ልጆቻችንን በአግባቡ የማሳደጉ ኃላፊነቱን ልንወጣፅ ይገባል፤ ያለንበት ጊዜ ልጆቻችን ከፍትፍትና ከእሳት ፊት ለፊት ቆመው የቱን እንደሚመርጡ ግራ የተጋቡበት ወቅት ነው ለማለት ያስደፍራል።
የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ (ከነፋስ፣ ከእሳት፣ ከመሬት፣ ከውኃ) እንደመሆኑ እነዚህ ባሕርያት በሕይወት ዘመኑ ይንጸባረቃሉ፤ የልጅነት ዕድሜ የነፋስነት ባሕርይ ጎልቶ የሚንጸባርቅበት ነው፤ በዚህ ዕድሜ የመፍጠን፣ ብር ብር ማለት፣ ነገሮችን በስሜታዊነት ባለማወቅ መረዳት፣ የመተርጎምና የመከወን (የመፈጸም) ጠባያት ይንጸባረቃሉ፤ ይታያሉ፤ ታዲያ ወላጆች ልጆቻችን በስሜታዊነት ተነሣስተው በሚፈጽሙት ተግባር ለጥፋት እንዳይዳረጉ በምግባር ልጓም ልንይዛቸውና አላስፈላጊ ፍጥነታቸውን ልናቀዘቅዝላቸው ያስፈልጋል፡፡ ልጆቻችንን ከጉያችን ሊነጥቁን እንዲሁም ለጥፋት ሊዳርጋቸው የሚችሉ በቀላሉ የሚገኙ ቁሶች አሉ! በተለይ ዘመኑ የወለደው የቴክኖሎጂ ፍሬ የሆነው ሞባይል (ተንቀሳቃሽ ስልክ) በእጃቸው ላይ አልያም ከወላጅ ተቀብለው የሚጠቀሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሥልጣኔው የወለደው የመገናኛ ብዙኃኑ በውስጡ ጠቃሚም የሆኑ ለጥፋትም የሚዳርጉ መረጃዎችን የሚተላለፉባቸው እንደ መሆናቸው የቱን መምረጥ እንዳለባቸው ልናስገነዝባቸው ግድ ይለናል፡፡
በነቢዩ ኤልሳዕ ዘመን ሕፃናት ከሥነ ምግባር ውጪ ሆነው የእግዚአብሔርን ነቢይ ሲሰደቡ እርሱም ረገማቸው፤ አውሬ ድብ ወጥቶ ሰበራቸው (ገደላቸው)፤ ሕዝቡም ይህን ሲመለከቱ “ረግሞ እንዲህ ካደረገ ቢመርቃቸው ይባረካሉ” በማለት ወላጆች ልጆቻቸውን አምጥተው አስባረኩ፡፡ በጌታችን ዘመን ወላጆች ይህን ማድረጋቸው በዚያ ልማድ ነበር፤ ልጆቻቸው ይባረኩላቸው ዘንድ የሁላችን ፈጣሪ ከሆነው ከጌታችን ዘንድ አመጧቸው፤ ተባረኩ፤ ለቁም ነገር ደረሱ፤ በሃይማኖታቸው ጽናት፣ በምግባራቸው ለብፅዓት በቁ፡፡ ልጆቻችንን ይዘን እንመጣ ዘንድ በመዳፉ ይባረኩ ዘንድ ዛሬም ‹‹አምጧቸው›› ይለናል፡፡
ውድ ክርስቲያኖች! ልጆቻችን ከቤተ እግዚአብሔር ሄደው እንዲማሩ የምናደርግ ስንቶች እንሆን? ከአባቶች ዘንድ አቅርበን የምናስባርካቸው፣ ካህናትን እንዲያከብሩ፣ ለታላቅ መታዘዝን በቃል ከማስተማር ባለፈ በተግባር እንዲከውኑ የምናደርጋቸው ስንቶች እንሆን? ጥፋት ሲያጠፉ፣ ሥርዓት ሲተላለፉ፣ ከእኛ ውጪ የሆነ ሰው ሲቆጣቸው፣ አልፎም ሲቆነጥጣቸው የማንከፋ (ልጆቻችንን በሌሎች ሰዎች መቀጣታቸውን የምንደግፍ) ስንቶች እንሆን? ቤተ ክርስቲያንን እንዲወዱ ሥርዓት የምናስተምራቸው ስንቶች እንሆን?
ዛሬ በልጅነታቸው በሥነ ምግባር የሚጓዙበትን መንገድ ካላመለከትናቸው፣ መሥመር ከሳቱብን፣ ወደ ጥፋት ካመሩ በኋላ መመለሱ ይከብዳልና ከቤተ እግዚአብሔር ወስደን እናስባርካቸው፤ ከአባቶች ቡራኬን ያገኘ የፈተናን አቀበት ወጥቶ ካሰበበት ደርሶ ለራሱ፣ ለቤተ ሰብ አልፎም ለአገር ለወገን የሚጠቅም ይሆናልና! ‹‹ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተውአቸው፤ አትከልክሉአቸውም›› ከሚለን አምላካቸው፣አባታቸው፣ ቸር እረኛቸው ከሆነው እግዚአብሔር ቤት እንውሰዳቸው፡፡
ውድ ወላጆች! ለልጆቻችን ሕይወት መቃናት ከአንደበታችን ግሣፄ የበለጠ እኛ የምንከውናቸውን ተግባራት ወሳኝነት አለውና ፈለጋችንን ተከትለው ያድጉ ዘንድ የእኛም ሕይወት ሊቃና ያስፈልጋል፤ ጌታችን በትምህርቱ ሕፃናቱን ወደ እርሱ እንዲመጡ እንዳይከለክሏቸው ከማስተማሩ በተጓዳኝ ለታላላቆችም የሚሆን ትምህርት ‹‹እውነት እላችኋላሁ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም›› በማለት አስተምሯል፡፡ (ሉቃ.፲፰፥፲፯)
መንግሥቱን ለመውረስ እንደ ሕፃናት ልበ ንጹሐን እና ኅዳጌ በቀል መሆን እንደሚገባ አስገንዝቧል፤ ከንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጀርባ ንግሥት ዕሌኒ፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ ጐን እናቱ ዮካብድ፣ ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ፊት እናቱ አንቱዛ ነበሩ፤ እነዚህ ታላላቅ አባቶች የሕይወታቸው መሠረት፣ የመንገዳቸው መሪዎች እናቶቻቸው ነበሩ፤ የእነርሱን ፈለግ ተከትለው በማደጋቸው ለቅድስና ሕይወት፣ ለታላቅ ክብር በቁ፤ ልጆቻችንን የምንመኝላቸውን ታላቅነት እንዲሁም መልካምነት ይዘው እንዲገኙ የእኛም ሕይወት ሊቃና እና አርአያ ሊሆን ይገባል!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!