ሕንጸተ ቤተ ክርስቲያን
በዝግጅት ክፍሉ
ሰኔ ፳ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ ተመዘገበልን ሰኔ ፳ ቀን በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ አገር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ያለ እንጨት፣ ያለ ጭቃና ያለ ውኀ በሦስት ድንጋዮች በተወደደ ልጇ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የታነጸበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከሚከብሩ ከእመቤታችን በዓላት አንደኛው ሲኾን ታሪኩንም በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤
ጌታችን በዐረገ በስምንተኛው ዓመት ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስ ወደ ፊልጵስዩስ ገብተው በክርስቶስ ስም አሳምነው ብዙ አሕዛብን ካጠመቁ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሊሠሩላቸው ወደዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ርእሰ ሐዋርያት እያለ እኛ መሥራት አይገባንም ብለው በሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት ላኩበት፡፡ እርሱም ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር መጥቶ ከቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ በርናባስ ጋር በኢየሩሳሌም ተገናኙ፡፡
በዚያም በአንድነት ሱባዔ ይዘው ከቆዩ በኋላ ጌታችን የሞቱትን አስነሥቶ፣ ያሉትንም ጠርቶ ቅዱሳን ሐዋርያትን በፊልጵስዩስ አገር ሰብስቦ ‹‹በእናቴ በድንግል ማርያም ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚሠራዉን የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ ላሳያችሁ፤ ሥርዓቱንም ላስተምራችሁ ሰብስቤአችኋለሁ›› ብሎ ወደ ምሥራቅ ይዟቸው ወጣ፡፡ በዚያ ሥፍራ የነበሩትን ሦስት ድንጋዮችንም የተራራቁትን አቀራርቦ፣ ጥቃቅኑን ታላላቅ አድርጎ ቁመቱን በ፳፬፤ ወርዱን በ፲፪ ክንድ ለክቶ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሰጣቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት ሰም እሳት ሲያገኘው እንዲለመልም፣ ድንጋዩ በእጃቸው ላይ እየተሳበላቸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሠርተው ፈጽመዉታል፡፡ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራዉም ጌታችን በዐረገ በ፲፱ኛው፤ እመቤታችን በዐረገች በ፬ኛው ዓመት ሰኔ ፳ ቀን ሲኾን፣ በ፳፩ኛው ቀን (በማግሥቱ) ኅብስት ሰማያዊ፣ ጽዋዕ ሰማያዊ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወረደ፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችን ጋር ከሰማየ ሰማያት መጥቶ እመቤታችንን ታቦት፤ ሐዋርያትን ልዑካን አድርጎ፣ እርሱ ሠራዒ ካህን ኾኖ ቀድሶ ካቈረባቸው በኋላ ‹‹እምይእዜሰ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ፤ ከዛሬ ጀምሮ እናንተም እንደዚህ አድርጉ›› ብሎ አዝዟቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡
ይህ ታሪክ ብዙ ምሳሌዎች አሉት፡፡ ይኸውም፡- የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ቁመት በነገሥታት ዘመን የነበሩ የ፳፬ቱ ነቢያት፤ አንድም የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ አምሳል ሲኾን፣ ወርዱ ደግሞ የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፡፡ ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴ አምሳል ሲኾኑ፣ ከታች አቀማመጣቸው ሦስት፤ ከላይ ሕንጻቸው አንድ መኾኑ የሥላሴን ሦስትነትና አንድነት ያመለክታል፡፡ የሠሩትም ሦስት ክፍል አድርገው ሲኾን፣ ይህም የመጀመሪያው የታቦተ አዳም፤ ሁለተኛው የታቦተ ሙሴ፤ ሦስተኛው የታቦተ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዳግመኛም የሦስቱ ዓለማት ማለትም የመጀመሪያው የጽርሐ አርያም፣ ሁለተኛው የኢዮር፣ ሦስተኛው የጠፈር ምሳሌ ነው፡፡
አንድም መጀመሪያው የኤረር፣ ሁለተኛው የራማ፣ ሦስተኛው የኢዮር አምሳል ነው፡፡ በኤረር፡- መላእክት፣ መኳንንት፣ ሊቃናት፤ በራማ፡- ሥልጣናት፣ መናብርት፣ አርባብ፤ በኢዮር፡- ኃይላት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌል ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ዘጠኙ ነገደ መላእክት የዘጠኙ መዓርጋተ ቤተ ክርስቲያን (መዓርጋተ ክህነት) አምሳል ሲኾኑ፣ ይኸውም መላእክት – የመዘምራን፤ መኳንንት – የአናጕንስጢሳውያን፤ ሊቃናት – የንፍቀ ዲያቆናት፤ ሥልጣናት – የዲያቆናት፤ መናብርት – የቀሳውስት፤ አርባብ – የቆሞሳት፤ ኃይላት – የኤጲስ ቆጶሳት፤ ሱራፌል – የጳጳሳት፤ ኪሩቤል – የሊቃነ ጳጳሳት አምሳሎች ናቸው፡፡
ይህም በታች (በምድር) የሚኖሩ ደቂቀ አዳም ከቅዱሳን በቀር ወደ ላይ (ወደ ሰማይ) መውጣት እንደማይቻላቸው፣ ከመዘምራን እስከ ጳጳሳት ድረስ ያሉ ካህናትም ከእነርሱ በላይ ያሉትን መዓርግ መሥራት (መፈጸም) እንደማይቻላቸው ያጠይቃል፡፡ እንደዚሁም በላይ የሚኖሩ መላእክት ወደ ታች መውረድ እንደሚቻላቸው ሊቃነ ጳጳሳትም ከእነርሱ በታች ያሉ ካህናትን ተልእኮ መፈጸም (መሥራት) እንደሚቻላቸው ያስረዳል፡፡
በጽርሐ አርያም መንበረ ብርሃን (የብርሃን መንበር)፤ ታቦተ ብርሃን (የብርሃን ታቦት)፤ መንጦላዕተ ብርሃን (የብርሃን መጋረጃ)፤ እንደዚሁም ፬ ፀወርተ መንበር (መንበሩን የሚሸከሙ)፤ ፳፬ አጠንተ መንበር (መንበሩን የሚያጥኑ) መላእክት አሉ፡፡ ጽርሐ አርያም – የመቅደስ፤ መንበረ ብርሃን – የመንበር፤ መንጦላዕተ ብርሃን – የቤተ መቅደሱ መጋረጃ፤ ፬ቱ ፀወርተ መንበር – የ፬ቱ ሊቃነ ጳጳሳት ወይም የመንበሩ እግሮች፤ ፳፬ቱ አጠንተ መንበር – የጳጳሳት (የኤጲስ ቆጶሳት) አምሳሎች ናቸው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ምንጭ፡-
- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳ ቀን፡፡
- መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻፭ ዓ.ም፤ ገጽ ፫፻፵፱ – ፫፻፶፩፡፡