ሐዋርያዊ ጉዞ በምሥራቅ ኢትዮጵያ

 

 ጥር 29 ቀን 2006 ዓ.ም.

በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል አስተባባሪነት ከጥር ፲፮ እስከ ፳፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ለአሥር ተከታታይ ቀናት በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሲካሔድ የሰነበተው ሐዋርያዊ ጉዞ ተጠናቀቀ፡፡

በሐዋርያዊ ጉዞው ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ክፍል አባላትን ጨምሮ የማኅበረ ቅዱሳን መምህራን፣ መዘምራንና ጋዜጠኛ በድምሩ ሃያ አራት አባላት ያሉት የልዑካን ቡድኑ መነሻውን ከዋናው ማእከል ማኅበረ ቅዱሳን በማድረግ በአፋር፣ ድሬዳዋ፣ ምሥራቅ ሐረርጌና ሱማሌ ሀገረ ስብከት በመዘዋወር ሰፊ የስብከትና መዝሙር አገልግሎት ፈጽሞ ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ሲመለስ የማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል አባላት ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ጥር ፲፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም በአፋር ሀገረ ስብከት አዋሽ ከተማ ሲደርስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮናስ ጉባኤውን በጸሎትና ቡራኬ ከፍተው ጉባኤው ለሦስት ተከታታይ ቀናት በአዋሽ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ሥላሴና ደብረ ሲና ቅድስት ማርያም ተካሒዷል፡፡

በመቀጠልም ጥር ፲፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ወደ ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት በማምራት በድሬዳዋ ኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ቀን አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡ በምሥራቅ ሐረርጌ ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖትና ጅግጅጋ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል አብያተ ክርስቲያናት ሁለት ሁለት ቀን የፈጀ ተመሳሳይ አገልግሎት ተፈጸሟል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ከተያዘለት ዕቅድ በተጨማሪ በአፋር ሀገረ ስብከት መልካ ወረር ደብረ መድኀኒት መድኀኔዓለም፣ በድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል፣ በድሬዳዋ ደብረ መንክራት ቅዱስ ዑራኤል፣ በጅግጅጋ ምሥራቀ ፀሐይ ኪዳነ ምሕረት አብያተ ክርስቲያናት ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንደነበር የልዑካኑ አስተባባሪ መጋቤ ሃይማኖት ለይኩን ገልጸውልናል፡፡

በእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ጉባኤ ሲካሔድ ምእመኑ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የፀሐዩን ግለትና የሌሊቱን ውርጭ ተቋቁሞ እስከ ምሽቱ 3፡30 ድረስ ጉባኤውን ታድሟል፡፡