ልደታ ለማርያም
ሚያዚያ ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
በግንቦት አንድ ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች። እርሷም ለሰው ሁሉ ወገን ድኅነት የሆነባት ናት፡፡ ከወንዶች ወገን የከበረ አባቷም ስሙ ኢያቄም ከሴቶች ወገን የከበረች ሚስቱ ሐና ይባላሉ፡፡ ሁለቱም ልጅ በማጣት ሲያዝኑ ኖሩ። በዚያ ወራት የመካኖች መብዓ ካህናቱ አይቀበሉም ነበርና፡፡ እነርሱም ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኅዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር፡፡ ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ሐሳባቸውን ተመለከተ፡፡ ክቡር ኢያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው፡፡
በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ፤ ለተመሰገነች ሚስቱ ለሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት። ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች። ልዑል እግዚአብሔርንም አመሰገነች። የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርገው ዘንድ ለእግዚአብሔር ስለትን ተሳለች፡፡
ከዚህም በኋላ ይህችን የከበረች ሕፃን ፀንሳ ወለደች። ስሟንም ‹ማርያም› ብላ ሰየመቻት። ትርጓሜውም ‹እመቤት› ነው። ‹ደግሞም ሀብታና ስጦታ› ማለት ነው፡፡ በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነትን ያገኘንባት ናትና።
የሥጋና የነፍስ መድኃኒት የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ለዘለዓለሙ ይኑር፤ አሜን፡፡
ከመጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት