ልደቱ ለቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
ሰኔ ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ከካህን አባቱ ዘካርያስና ከቅድስት እናቱ ኤልሣቤጥ የተወለደው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የስሙ ትርጓሜ ‹‹ፍሥሐ፣ ሐሴት፣ ርኅራኄ›› ነው። የመወለዱም ነገር እንዲህ ነው፤ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በአምላኩ ትእዛዝ ወደ ዘካርያስ በመምጣት በመጀመሪያ በመሠዊያው በስተቀኝ በኩል ተገልጦ ታየው፡፡ ከዚያም ‹‹ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፤ ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፡፡ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናልና የወይን ጠጅና የሚያሰክርም መጠጥ ሁሉ አይጠጣም፤ ከእናቱ ማሕፀን ጅምሮም መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል፡፡ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎቹን ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ይመልሳቸዋል፡፡ እርሱም የአባቶቻችን ልብ ወደ ልጆች፥ የከሓዲያንንም ዐሳብንም ለእግዚአብሔር የተዘጋጀ ያደርግ ዘንድ በኤልያስ መንፈስ ቅዱስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል፡፡›› ዘካርያስም መልአኩን እንዲህ አለው፤ ‹‹ይህ እንደሚሆን በምን አውቃለሁ? እነሆ፥ እኔ አርጅቻአለሁ፤ የሚስቴም ዘመንዋ አልፏል፡፡›› መልአኩም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህንም እነግርህና አበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልኬአለሁ፡፡ አሁንም በጊዜው የሚሆነውንና የሚፈጸመውን ነገሬን አላመንኽኝምና ይህ እስኪሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገርም ይሳንሃል›› በማለት አበሠረው፡፡ (ሉቃ.፩፥፲፫-፳)
ሚስቱ ኤልሣቤጥም ፀነሰች፤ በዚያንም ወቅት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፀንሳ እናቱ ኤልሣቤጥን ለመጠየቅ ሄደች፤ በማሕፀኗ ውስጥ ሳለም ሕፃኑ ለጌታችን ሰገደ፡፡ (ሉቃ.፩፥፴፱-፵፩) ኤልሣቤጥ የመውለጃዋ ጊዜ በደረሰ ጊዜ ወንድ ልጅን ወለደች፡፡ ዘመድ አዝማዱና ጎረቤቷም ደስ ተሰኙ ተሰብስቦ ወደ እርሷ መጥተው ጠየቋት፤ ሕፃኑም ስምንት ቀን በሞላው ጊዜ ይገረዝ ዘንድ ገራዦች መጥተው ስሙንም በአባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ሊሰይሙት ፈለጉ፤ እናቱ ኤልሣቤጥ ግን ‹‹ዮሐንስ›› ተብሎ መጠራት እንዳለበት አሳወቀች፡፡ ይህንንም ነገር በሰሙ ጊዜ ካህኑ ዘካርያስን ማን በመባል እንዳለበት ጠየቁት፤ እርሱም መናገር የተሣነው ዲዳ ስለነበር ብራና ለምኖ ስሙ ‹‹ዮሐንስ ይባል›› ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም ተደነቁ፤ የዘካርያስ አንደበትም ይህን ጊዜ ተፈታ፤ እርሱም አምላኩ እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ (ሉቃ.፩፥፶፪-፷፬)
ንጉሥ ሄሮድስም መሢሕ ሕፃን ክርስቶስ መወለዱን ሲሰማ መንግሥቱን እንዳይቀማው በመፍራት በቤቴልሔም ያሉ ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች ያሉ መቶ ዐርባ አራት ሽህ የቤቴልሔም ሕፃናትን በሰይፍ ሲያስገድል ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ ስትሰደድ፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ ደግሞ ወደ ሲና በረሃ ሄዳ ልጇን ዮሐንስን ከዚያ ደብቃዋለች፡፡ ከመሄዷ በፊት ግን ከባሏ ከዘካርያስ ጋር ሲሰነባበቱ የሚሆነውንም ሁሉ እርሱ ቀድሞ ያውቅ ነበርና ‹‹ሕፃኑን ልጄን ሲያጡ እኔን ይገድሉኛል፤ አንቺ ግን ወደ በረሃው ይዘሽው ሂጂና በዚያ ሸሽጊው›› ብሎ መክሯታል፡፡ እርሷም ከሄደች በኋላ የርጉም ሄሮድስ ጭፍሮች ዮሐንስን ባጡት ጊዜ ወደ ዘካርያስ መጥተው ‹‹ልጅህን ወዴት አድርሰኸው ነው? ወዴትስ ደበቅኸው? አሁን ከደበቅህበት አምጥተህ ፈጥነህ አስረክበን›› በማለት የፍጥኝ አስረው ካሠቃዩት በኋላ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ከሚሠዋበት በቤተ መቅደስና በዕቃ ቤት መካከል አንገቱን ቆርጠው ገደሉት፡፡ የዘካርያስም ደም እስከ ሰባት ዓመት ድረስ እየፈላ ደሙ ሲካሰሳቸው ኖረ፡፡ ‹‹ቅድስት ኤልሣቤጥም ልጇን ዮሐንስን ይዛ ወደ በረሃ ከገቡ አምስት ዓመት በሆናቸው ጊዜ ዮሐንስ ዕድሜው ሰባት ዓመት ከመንፈቅ ከሆነው በኋላ እናቱ ኤልሣቤጥ ሞተችበትና ብቻውን ከበረሃ ውስጥ ተወችው፡፡ ዮሐንስም በሰፊዋ በረሃ ውስጥ በአራዊቶች መካክል ብቻውን ቀረ፡፡ ለዮሐንስ ግን በእርሱ ላይ ምንም መጥፎ ነገር ሳያደርጉ የቶራና የአንበሳ የነብርም ልጆች እንደ ወንድምና እንደ እኅት ሆኑት፡፡ አራዊቶችም ሁሉ ወዳጅ ሆኑት፡፡ ምግቡም የበረሃ ቅጠል ነው፤ መጠጡም ከተቀመጠባት ድንጋይ ሥር የፈለቀችለት ውኃ ነበረች፡፡ ዮሐንስ ሰውነትን አለምልመው፣ ሥጋን አለስልሰው፣ ገጽንና ፊትን የሚያሳምሩትን ምግቦች አልተመገበም፡፡ የበረሃ ቅጠሎችንም አልተመገበም፡፡ አንቦጣ ከተባለችው ከአንዲት የበረሃ ቅጠልና ከጣዝማ ማር በስተቀር ከሚበሉት ምግቦች ሁሉ ዮሐንስ ኅርምተኛ ሆኖ የተለየ ነበር›› ይላል ቅዱስ ገድሉ፡፡ ነገር ግን ‹‹አንቦጣ›› ተብላ የምትጠራ አንዲት የበረሃ ቅጠልንና የጣዝማ ማርን እየተመገበ ማደጉን ለመግለጽ ብዙ ጊዜ በተለምዶ ‹‹የዮሐንስ ምግቡ የበረሃ አንበጣ ነበር›› ተብሎ የተሳሳተ ነገር ሲነገር ይሰማል፡፡
ንጉሥ ሄሮድስ በሞተ ጊዜ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ በግብፅ ኀገር ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ በመታየት ‹‹እነሆ የዚህን ሕፃን ነፍስ የሚሹ ሙተዋልና ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ እስራኤል ተመለስ›› ካለው በኋላ ዮሴፍ ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ምድረ እስራኤል ገባ፡፡ ጌታችን ‹‹ልጄ ናዝራዊ ይባላል›› ተብሎ በነቢይ የተነገረው ቃል ይደርስ ይፈጸም ዘንድ መጥቶ ናዝሬት በምትባል ሀገር ተቀመጠ፡፡ ለሞት ይፈልገው የነበረው የተረገመ ከሃዲ ሄሮድስ ከሞተ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ከምድረ ግብፅ ተመልሶ በናዝሬት ተቀምጦ ሳለ የዕድሜ ባለፀጋ የሆነችው የዮሐንስ እናት ክብርት ኤልሳቤጥ ልጇን ዮሐንስን ይዛው ወደ ደብረሲና በረሃ ከገቡ ከአምስት ዓመት በኋላ ዐረፈች፡፡ ዮሐንስም በእናቱ አስክሬን አጠገብ ተቀምጦ በእጅጉ እያዘነ መሪር ልቅሶንም ሲያለቅስ የተሸሸገውን ሁሉ የሚያውቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በናዝሬት ተቀምጦ ሳለ የኤልሳቤጥን መሞትና ዮሐንስ ብቻውን ከበረሃ ውስጥ ተቀምጦ እያለቀሰ መሆኑን ዐወቀ፡፡ ጌታችን በናዝሬት ሆኖ ያለቅስ ጀመር፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ልጇ ወዳጇ ሲያለቅስ ባየችው ጊዜ ‹‹ልጄ ወዳጄ ሆይ! ምን ሆንክ? ስለምንስ ታለቅሳለህ?›› ብላ ጠየቀችው፡፡ ጌታችንም ለቅድስት እናቱ እንዲህ በማለት መለሰላት፤ ‹‹እነሆ ወገንሽ የሆነችው ኤልሣቤጥ ዐረፈች፤ ዮሐንስንም ብቻውን ከበረሃ ውስጥ ተወችው፡፡ ዮሐንስም ሕፃን ስለሆነ የሚያደርገውን አጥቶ በእናቱ አስክሬን አጠገብ ከፊት ለፊቷ ተቀምጦ በመረረ ኃዘን ያለቅሳል፡፡ እናቴ ሆይ እኔም ዘመድሽ የሆነ የዮሐንስን ልቆሶ ስላወቅሁኝና የእርሱም ኃዘን ስለተሰማኝ የማለቅሰው ስለዚህ ነው›› አላት፡፡ በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የፀናች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የኤልሣቤጥን መሞት በሰማች ጊዜ በጣም ምርር ብላ አለቀሰች፡፡ ያንጊዜም ብርሕት ደመና መጥታ ከፊታቸው ቆመች፤ ፈጥናም ተሸከመቻቸውና ኤልሣቤጥ ከሞተችበት ዮሐንስም ካለበት ቦታ ከደብረሲና በረሃ ውስጥ ወስዳ አደረሰቻቸው፡፡
ዮሐንስም ባያቸው ጊዜ ደነገጠ፤ ከዚያ በፊት ሰው አይቶ ስለማያውቅ የእናቱን አስክሬን ብቻውን ትቶ ወደ ጫካ ሸሸ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የዮሐንስን ፍርሃት አራቀለትና እንዲህ አለው፤ ‹‹እኛን ከማየትህ የተነሣ አትፍራ፤ አትደንግጥም፤ አይዞህ እነሆ የእናትህ ዘመዶች ማርያምና ሰሎሜ በእናትህ አስክሬን ላይ መልካም ነገር ሊያደርጉ መጥተዋልና ና ወደ እኛ ቅረብ›› አለው፡፡ ዮሐንስም ይህን ቃል ከጌታችን አንደበት በሰማ ጊዜ ወደኋላው ተመለሰ፡፡ ከመሬትም ላይ ወድቆ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰገደለት፡፡ ጌታችንም እመቤታችን ማርያምንና ሰሎሜን ‹‹በጠማው ጊዜ ለእርሷ ይጠጣ ዘንድ ለዮሐንስ በፈለቀችለት ውኃ የኤልሣቤጥን ሥጋ አጥባችሁ ገንዙ›› አላቸው፡፡ እንዳዘዛቸውም የኤልሣቤጥን አስክሬን አጥበው ገነዙ፡፡ ጌታችንም ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን ይመጡ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ፈጥነው እንደ ዐይን ጥቅሻ ከሰማይ ወርደው መጡና ከጌታችን ፊት ቆሙ፡፡ ጌታችንም ‹‹የኤልሣቤጥን ሥጋ የሚቀበርበትን መሬት ቆፍሩ›› አላቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤልም መቃብሩን ይቆፍሩ ዘንድ ጀመሩ፡፡ ጌታችን ዘካርያስንና ስምዖንን በአካለ ነፍስ ከሰማይ መጥተው በኤልሣቤጥ አስክሬን ላይ ጸሎተ ፍትሃቱን ያደርሱ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ እነርሱም የኤልሣቤጥ አስክሬን ካለበት ቦታ ላይ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል፣ እመቤታችን ማርያምና ሰሎሜ ከጌታችን ፊት ቆመው ሳለ ስምዖንና ዘካርያስ በአስክሬኑ አጠገብ ቆመው ጸሎተ ፍትሃቱን ያደርሱ ጀመር፡፡ ጸሎተ ፍትሃቱንም በጨረሱ ጊዜ መላእክት በቆፈሩት መቃብር ውስጥ ቀበሩዋትና የስምዖንና የዘካርያስ ነፍስ ወደነበረችበት ቦታዋ ተመለሰች፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የኤልሣቤጥን መቃብር በትእምርተ መስቀል አምሳል ደፈነው፡፡ እርሷም ያረፈችበት ዕለት የካቲት ፲፮ ቀን ነው፡፡
ከዚህ በኋላ ዮሐንስን ብቻውን ከበረሃ ውስጥ ትተውት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ጋር ወደ ናዝሬት ለመመለስ በደመናዋ ላይ ሄደ፡፡ ያንጊዜም ክብርት እመቤታችን ልጇን እንዲህ አለችው፤ ‹‹ጌታዬና አምላኬ ፈጣሪዬ ሆይ! ስለምን ዮሐንስን ብቻውን ከበረሃ ውስጥ ትተወዋለህ? እንዴትስ ትተነው እንሄዳለን? ወደዚህ ቦታ ይዛው የሸሸችው እናቱ ጥላው ሞታ በመቃብር ውስጥ ተቀብራለች፤ ከእኛ ጋር ይዘነው እንሂድ እንጂ›› አለችው፡፡ ዳግመኛም እመቤታችን እንዲህ አለችው፤ ‹‹ነፍስ ያለወቀ ሕፃን ስላሆነ አራዊት ይበሉታልና ይዘነው መሄድ አለብን›› አለችው፡፡ ጌታችንም ለቅድስት እናቱ እንዲህ በማለት መለሰላት፤ ‹‹በመምህርነት ወጥቶ ለእስራኤል ታይቶ እስከሚያስተምር ድረስ የሰማያዊው አባቴ ፈቃድ በበረሃ ውስጥ ብቻውን እንዲኖር ነው፡፡ አንቺ ብቻውን እንዴት ከበረሃ ይኖራል ትያለሽ፤ አራዊቶች እንዳይጣሉት ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከእርሱ አይለይም፡፡ በፈለገው ነገር ሁሉ እንዲራዱትና እንዲታዘዙለት መላእክተ ብርሃንን አዝለታለሁ፡፡ ብርሃናዊው መልአክ ገብርኤልም ሰማያዊ ኅብስትን ለምግቡ ያመጣለታል፤ በጠማውም ጊዜ እንደ ወተት የነጣችውን እንደ ወለላ ማርም የጣፈጠችውን ውኃ ከኤዶም ገነት ያመጣለታል፡፡ ይህችንም እርሱ ካለበት ድንጋይ ሥር የምትፈልቀውን ውኃ እንደ እናቱ ጡት ለአፉ የጣፈጠች አደርግለታለሁ፡፡ አንቺ ብቻውን እንዴት በበረሃ ውስጥ ይኖራል ትያለሽ? እስከ ዛሬ ድረስም የጠበቅሁት እኔ ነኝ፤ ሌላ ማን ጠበቀው ብለሽ ነው? እኔ አይደለሁምን? ወዳጄ ዮሐንስን ሰማያዊው አባቴ ከዚህ ዓለም ፍጥረት ሁሉ በጣም አብልጦ ይወደዋል፡፡ አባቱ ዘካርያስም በሥጋው ቢሞት በነፍሱ ሕያው ስለሆነ ዮሐንስን ለማጽናናት በአካለ ነፍስ ከእርሱ እንዳይለየው አደርጋለሁ፡፡ እናቱ አልሣቤጥም በሥጋዋ ብትሞት በነፍሷ ሕያዊት ስለሆነች ታጽናናው ዘንድ በነፍሷ በፍጹም ከእርሱ እንዳትለየው አደርጋለሁ፡፡ ዮሐንስን የተሸከመች ማኅፀን ንዕድ፣ ክብርት ስለሆነች በሥጋዋ ውስጥ መጥፎ ሽታ ክፉ መዓዛ አይገኝባት፤ በመቃብሯም ውስጥ ትሎች አይገኙበት፡፡ ድንግል እናቴ ሆይ! አንቺ እኔን ፀንሰሽ ሳለሽ ወደ ኤልሣቤጥ በሄድሽ ጊዜ በእጇ ይዛ ጨብጣ፣ በአፏ በሳመችሽ ጊዜ እንዲህ ብላ ትንቢት ተናግራለች፡፡ ‹አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፤ የጌታዬ እናቱ ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድነኝ? ከእግዚአብሔር አግኝተው የነገሩሽን ቃል ይደረጋል ብለሽ የተቀበልሽ አንቺ ብፅዕት ነሽ፤ ክብርት ነሽ› ብላ ስላመሰገነችሽ እንኳን ሥጋዋ ሊፈርስ ይቅርና መግነዟም አይለወጥም፤ መቃብሯም አይጠፋም፤ ነፍሷንም ከሥጋዋ ጋር እንድትኖር አደርጋታለሁ፡፡› ስለ ወዳጁ ዮሐንስ ለድንግል እናቱ ነግሯት ከጨረሰ በኋላ ዮሐንስን ከበረሃ ውስጥ ትተውት በደመና ላይ ተጭነው ወደ ናዝሬት ተመለሱ፡፡ ዮሐንስም አድጎ በሀገረ እስራኤል እስከተገለጠበት ጊዜ በበረሀ ኖረ፡፡
(ምንጭ፡- ገድለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ-ደብረ መንክራት ሚጣቅ ቅዱስ አማኑኤል አንድነት ገዳም ያሳተመው፣ የመስከረምና የየካቲት ወር ስንክሳር)