‹‹ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል፤ ዋጋዋ ከቀይ ዕንቊ እጅግ ይበልጣል!›› (ምሳ. ፴፩፥፱

ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ዓለማችን የልዩነት መድረክ ናት፡፡ ልዩነቶቹ እንዲህ፣ እንዲያ፤ አንድ እና ሁለት ተብለው የማይወሰኑ ናቸው፡፡ ሴትነትና ወንድነትም የጾታ ልዩነት አንድ መደብ ናቸው፤ የሴት መሆንም የወንድ መሆንም መገናኛው ሰው መሆን ነው፡፡ ጥያቄው ታዲያ ምን ዓይነት ሴት ወይም ምን ዓይነት ወንድ እንሁን፤ ከዚያም ምን ዓይነት የሰው ልጅ ይኑር የሚለው ነው፡፡ ወንድ የሚለው ስም ብቻውን ወደ ሰውነት አያደርስም፤ ሴት ተብሎ መጠራትም ሴት የመሆንን ትክክለኛ መዳረሻ ጥግ አያመጣውም፡፡ ሁሉ በተገቢው ሚዛን ሊመዝነው የሚችለውን ሚዛን መምረጥ አለበት፡፡

ሴትነት እኛ ከምንረዳው እና ከምናያቸው ዓይነት ተራ ትርጉሞች የተለየ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ሴትነት ከብር፣ ከወርቅ፣ ከዕንቊዎችም እጅግ ውድ ከሆነው ከቀይ ዕንቊ ጋር ይነፃፀራል፡፡ ከዚህም እጅግ ይልቃል ተባለ እንጂ ይስተካከላል አልተባለም፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ዓለም ባስቀመጠችው ልኬት ብቻ እየተራመዱ፣ በተፈቀደለት ድምፅ ብቻ እየተናገሩ አይደለም፡፡ ዕንቁነት በራሱ ትልቅ ውድነት ነው፡፡ ከቀይ ዕንቊ ልቆ መገኘት ደግሞ በእጅጉ ዋጋ ያለው ክብር ነው፡፡ ታዲያ የዚህ ዋጋ ክብደት ሲመዘን በተራ ሚዛን መሆን የለበትም፡፡ መስፈሪያው ከሌሎች ለየት ማለት አለበት እንጂ፡፡ እዚህ ላይ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል፤ ዋጋዋ ከቀይ ዕንቊ እጅግ ይበልጣል›› ሲል ባስቀመጠልን መሠረት ለማየት እንሞክር፤ በዓለም ላይ ከሞሉ ውድ ነገሮች ስለምን ያችን ልባም ሴት ከቀይ ዕንቁ ጋር አነጻጸራት ብለን እንጠይቅ፡፡

ቀይ ዕንቁ በዓለም ለይ በጣም በውድነት እና በብዙ አለመገኘት ከሚፈረጁት የዕንቊ ዓይነቶች አንዱ ነው፡፡ ሌሎች የዕንቊ ዓይነቶች ቀለማቸውን ከናይትሮጅን ከቦሮን አልያም ከሌሎች ንጥረ ነገሮች ሊያገኙ ይችላሉ፤ ቀይ ዕንቊ ግን ቀለሙን የሚያገኘው ከራሱ ከካርበን ብቻ ሲሆን ይሄን ቀለም ለመያዝ ረጅም ጊዜያትን በሙቀትና ፈታኝ በሆነ መንገድ ማለፍ አለበት፡፡ በዓለም ላይ እስካሁን የሚገኙት ቀይ ዕንቊዎች እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ እነዚህ ቀይ ዕንቊዎች አይገኙም፤ ሲገኙም ዋጋቸው በጣም ውድ ነው፡፡ ከቀይ ዕንቊ ቀጥሎ ውድነቱው ከሚነሣ ከሐምራዊ እና ሮዝዳይመንዶች እንኳን ዋጋቸው ከሦስት መቶ እስከ ዐራት መቶ ፐርሰንት ብልጫ አለው፡፡፩ አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ የአንድ ካራት ዕንቊ ዋጋ ከ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ የአሜሪካን ዶላር ጀምሮ ሲሆን የቀይ ዕንቊዎች የመነሻ ዋጋ ግን ከዐሥር ሺህ የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡ “The more rare the diamond is the more desired and valuable, አልማዝ የማይገኝበት መጠኑ በበዛ ቁጥር ዋጋው የዚያን ያህል ተፈላጊና ውድ ይሆናል” የሚባለው ለዚሁ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ከላይ ያለውን የቀይ ዕንቊ መገለጫዎች ያነሣነው ከዚህ ከቀይ ዕንቊ ጋር የተነሣችው ልባም ሴት ጋር ለመድረስ ነው፡፡ እህታለም ውድነት ላንቺ ምንድን ነው? ልባምነትስ? እጅግ ውድ በተባሉ ልብሶች አጊጦ መታየት ነው? ወይስ ትናንት ከነጮቹ የታየውን ዛሬ አንቺ ማድረግሽ? በእርግጥ የእኛ ዘመን መጥፎ ገጽታ አንዱ መገለጫው ለመልካም ሴት የምንሰጠው የተዛባ ምስል ነው፡፡ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንም በጣም ጥሩና ተወዳጅ ሴት ብለው የሚያሳዩን በግማሽ ዕርቃኗ የምትሄድ፣ ፀጉሯን ያንጨባረረች፣ ዐይን አውጣ፣ ኃይለኛ፣ ደፋር የምትመስል ነገር ግን ራስን መግዛት ያልተላበችውን ብሎም ለኅሊናዋ እንኳን የማትገዛዋን ነው፡፡፪ ታዲያ እንዳለመታደል ሆኖ ወጣት ሴቶቻችን፣ እናቶች፣ ሚስቶች እንዲሁም ሕፃናት ሴት ልጆች እንኳን ሳይቀሩ ይህንን ሰይጣናዊ ምስል ለመቅዳትና ለማስመሰል ሲሉ ነፍሳቸውን በምግባር እያበላሹ ቤታቸውን እያፈራረሱ የራሳቸውን የሌሎችን ሕይወት ሲያመሰቃቅሉ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡

ሊቁ ጠርጡሉስ ይህንኑ ሐሳብ ሲገልፅ ‹‹ነገሮች ሞገስን የሚያገኙት ውድና ያልተለመደ በመሆን ነው፣ አንዳንድ ግዜ በብዛት እንደሚገኙት መገኘት በራሱ ጸያፍ ስድብ ይሆናል ፣አንቺ ግን ትኅትናን ማጌጫሽ አድርጊያት››፫ ይለናል፡፡ አንቺ እኮ ውድ ነሽ፤ ርካሽ ብትሆኝማ ኖሮ ለቅድስት ቤተክርስትያን ምሳሌ አትሆኚም ነበር፡፡ የውድነትሽ መጠን በዚህ ልክ ይሁን፡፡ በልብስ እና ውጫዊ ማንነትን ለማስዋብ ከሚተጉት ጋር ብቻ አትፈረጂ፣ ውስጥሽን መልካም ለማድረግ ትጊ እንጂ፡፡ የሴት ማንነት ትውልድ የሚቀረፅበት በመሆኑ አለም ከትውልዱ አስቀድማ ሴቶችን እንደፍላጎቷ ለመቅረፅ እየታተረች ትገኛለች፤ አንቺ ግን ለዚህ እጅ አትስጪ፡፡ ቅዱሳት አንስትን እያየሽ ሂጂ መንፈሳዊ እናትነት ያንቺ ኃላፊነት ነው፡፡ ሙሴ እኮ በፈርዖን ቤት ቢያድግ እንኳን እስራኤላዊ ማንነት እንዲኖረው አድርጋ ያሣደገችው እናቱ ናት፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙን ተመልከች ጎርጎርዮስ ሆኖ እንዲያድግ ያደረገችው ኖና ናት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን በሚደንቅ ሰብእና ያስገኘችው ቅዱስ አትናስያ ናት፡፡

ስለዚህ የሚታየው ማንነትሽን ከማስዋብ በዘለለ ልባምነትን ገንዘብ አድርጊ፤ በምሳሌ ‹‹የወርቅ ቀለበት በእሪያ አፍንጫ እንደሆነ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት›› ተብሎ እንደተገለጸ ውበትና ደምግባትስ ከንቱ ነው፤ ከእነዚህስ ይልቅ ከጥበብ ጋር መወዳጀት እጅጉን ይልቃል፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ሰብእናና ማንነት እንዲኖርሽ ራስሽ ላይ ስሪ ሂደቱ አድካሚ ሊሆን ይችላል ግን ያ ቀይ ዕንቊም ተወዳጅነቱን ያመጣው በታላቅ ሙቀት እና በብዙ ኃይል ተፈትኖ መሆኑን አትዘንጊ፤ በሁለቱም በኩል የተሳልሽ ሰይፍ ሁኚ በዚሁ በምሳ. ፴፩፥፳፫ የተቀመጠችውን ውድ ሴት ተመልከቻት ‹‹ባልዋ በሀገር ሽማግሌዎች መካከል በሸንጎ በተቀመጠ ጊዜ የታወቀ ይሆናል!›› እስቲ አስቢው! ካንቺ ብርታት የተነሣ የሕይወት አጋርሽ ሲመሰገን፡፡ አንቺነትሽ ውድ እንደሆነው እንደ ቀይ ዕንቊ ይሁን!
ምንጭ፡-
• ፩ https://en.m.wikipedia.org/wiki/Red diamond
• ፪ ከሩስያ ኦርቶዶክስ፣ በድጋሚ የታተመ፣ቁ.፲፮፣፳፻፲፫
• ፫ ጠርጡለስ መፅሐፍ ፪፣በሴቶች አለባበስ ዙሪያ የተፃፈ.፣ምዕ ፯)