ሊቀ ሐመር
በባሕሩ ማዕበል፣ በአውሎ ነፋሱ ውሽንፍር ጊዜ ጭምር ሕይወቱን ለተሳፋሪዎች ደኅንነት አሳልፎ ይሰጣል፤ ሊቀ ሐመር፡፡ ከመርከቡ ርቀው፣ ስፍራቸውንም ትተው ጠፍተውም እንዳይሰጥሙ ይከታተላቸዋል፡፡ እርሱ ጠባቂያቸው ነውና፡፡ ያለ ሥጋት ተጉዘው ወደ ባሕሩ ዳርቻ እንዲደርሱም በሰላም ይመራቸዋል፡፡
‹‹ቸሩ ጠባቂ እኔ ነኝ›› ያለን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወታችን መንገድ መሪ በመሆኑ በሊቀ ሐመር ይመሰላል፡፡ ከችግር እና ከመከራ አውጥቶ በጽድቁ ጎዳና ይመራናልና፡፡ (ዮሐ. ፲፥፬)
በመጽሐፈ ስንክሳር በሐዋርያው እንድርያስ ታረክ ውስጥ ጌታችን እርሱንና ደቀ መዛምርቱን በባሕር ውስጥ በሊቀ ሐመር አምሳል ተገልጾ፣ በሰላምም መርቶ ወደ ወደቡ እንዳደረሳቸው ይጠቅሳል፤ ይህም የእርሱ የመልካም መሪነት ተምሳሌት ሆኗል፡፡ (ዮሐ.፲፥፲፩፣ ስንክሳር ወርኃ ነሐሴ)
በዚያን ጊዜ እንድርያስ ጌታችንን ‹‹በመርከብህ አሳፍረን፤ ነገር ግን የምንከፍልህ የመርከብ ዋጋ የለንም›› አለው፡፡ በሊቀ ሐመር የተመሰለ ጌታችንም ‹‹ስለምን የላችሁም›› ብሎ ጠየቀው፡፡ እንድርያስም ‹‹በከረጢታችን ወርቅን ብርን እንዳንያዝ ስለአዘዘን›› ነው፡፡ ጌታችንም እንዲህ ከሆነ መርከቤ ወጥታችሁ ተሳፈሩ›› አላቸው፡፡ ያንጊዜም ወደ መርከቡ ወጥተው ተሳፈሩ፡፡
ከዚህም በኋላ ጌታችን እንድርያስንና ደቀ መዝሙሩን ከባሕሩ ማዕበል የተነሣ መታገሥ እንዲችሉ ተነሥተው እንጀራ ይበሉ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ እንድርያስም አድንቆ እንዲህ አለው፡፡ ‹‹በመንግሥተ ሰማያት የሕይወት እንጀራ እግዚአብሔር ይስጥህ፡፡›› ደቀ መዝሙርቱ ግን በባሕር ላይ ጉዞ ስለአልለመዱ ከባሕሩ ማዕበል ፍርሀት የተነሣ መብላትም ሆነ መነጋገር ተሳናቸው፡፡
ጌታችንም እንድርያስን ‹‹ደቀ መዝሙርትህን ወደ ምድር እንዲወርዱ እዘዛቸው፤ ሲፈሩ አያአአዋለሁና፤ ይህ ካልሆነ እንዳይፈሩ አንተ የእግዚአብሔር ኢየሱስ ደቀ መዝሙሩ ከሆንክ ጣዕም ባለው ቃል አስተማራቸው፤ እነሆ ከየብስ ርቀናልና›› አለው፡፡ ጌታችንም መርከቡን መቅዘፍ ጀመረ፤ እንድርያስም ማስተማርና ማጽናናት ያዘ፤ በልቡም ጸለየ፤ ያንጊዜም ከባድ እንቅልፍን አንቀላፋ፤ ስለተኙለትም እንድርያስ ደስ አለው፡፡
እንድርያስም ወደ ጌታችንም ተመልሶ እንዲህ አለው፡፡ ‹‹ዐሥራ አራት ጊዜ በባሕር ላይ ጉዞ አድርጌአለሁ፤ እንዳንተ የሚቀዝፍ አላገኘሁም፡፡›› ጌታም መልሶ እንዲህ አለው፤ ‹‹እኛስ በባሕር ላይ ስንጓዝ ሁል ጊዜ እንቸገራለን፡፡ ነገር ግን አንተ የክብር ባለቤት የእግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ እንደሆንክ ባሕሩ ስለአወቀችህ ማዕበሏን በአንት ላይ አላነሣችም፤›› እንድርያስም በታላቅ ቃል እንዲህ ብሎ ጮኸ፡፡ ‹‹የክብር ባለቤት ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ፤ ከሚያከብርህ ሰው ጋር ተገናኝቼ ተነጋግሬአለሁና፡፡››
ከዚህም በኋላ ጌታችን እንድርያስን እንዲህ አለው፤ ‹‹አንተ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነህና ንገረኝ፡፡ አይሁድ ስለምን አላመኑም፤ የሠራውን ብዙ ድንቅ ተአምርን ሰምተናል፡፡›› እንድርያስም እንዲህ አለው፤ ‹‹አዎን ወንድሜ! እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ገልጦናል፤ ቊጥር የሌላቸው ብዙ ተአምራቶችን አደረገ፡፡ የዕውራንን ዐይኖች ገልጧልና፤ አንካሶችንም በትክክል እንዲሔዱ አድርጓልና፤ ደንቆሮዎችንም አሰመቷልና፤ ዲዳዎችንም አናግሯልና ለምጻሞችንም አንጽቷልና፤ ውኃውንም ወይን አድርጓልና፤ አምስት እንጀራና ሁለተ ዓሣን አንሥቶ ያዘ ሕዝቡንም በመስክ ሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፡፡ ሣሩም እንጀራ እስኪለብስ ድርስ በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም በብዙ ቅርጫቶች አነሣን፤ ይህም ሁሉ ሲሆን አላመኑም፡፡››
ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ ‹‹ይህን ያደረገ በግልጥ ነው ወይስ በሥውር፡፡›› እንድርያስም እንዲህ መለሰ፤ ‹‹ይህንስ በግልጥ ነው ያደረገ፤ በሥውር ያደረገውም አለ፤ ግን የምትፈትነኝ መሰለኝ፤›› ጌታችንም እንዲህ አለው፤ ‹‹ወንድሜ ሆይ ልቤን ደስ ስለሚላት ነውና ንገረኝ፡፡››
እንድርያስም መናገር ቀጠለ፤ ልጄ ሆይ በጎ ሥራህን ሁሉ እግዚአብሔር ይፈጽምልህ፤ አሁንም ስማ፤ ጌታችን ያደረገውን ተአምር እኛ ዐሥራ ሁላችምን ሐዋርያቱም ከእርሱ ጋር ስንጓዝ ከሊቃነ ካህናትና ከሕዝቡ ብዙዎች አሉ፡፡ ወደ ምኵራብ ደረስን፤ ጌታችንም እንዲህ አለ፤ ‹‹በሰማይ ባላ በኪሩቤልና በሱራፌል አምሳል፤ በምድር ላይ ሰው የሠራትን ይህችን የተቀረጸች ሥዕል ታያላችሁን፡፡
ከዚህም በኋላ ወደ ሥዕሊቱ ተመልሶ ብልህ ሰው የተጠበበብሽ የሰማያውያን መልክን ያደረግሽ፤ አንቺን እላለሁ፤ ከቦታሽ ተነቅለሽ ውረጂ፤ የካህናት አለቆችንም ውቅሻቸው! እኔም ዕሩቅ ብእሲ ወይም እግዚአብሔር እንደሆንኩ መስክሪ!›› አላት፡፡ ወዲያውኑ ከቦታዋ ተነቅላ ወረደች፤ እንደሰውም በመናገር እንዲህ አለች፤ ‹‹እናንተ የደነቆራችሁ አይሁድ! የራሳችሁ መደንቆር ያልበቃችሁ ሌሎችንም ለማደንቆር የምትሹ ለድኅነታችሁ ሰው የሆነ እግዚአብሔርን እንዴት ዕሩቅ ብእሲ ትሉታላችሁ፤ አስቀድሞ ሰውን የፈጠረው በንፍሐት ልጅነትንም የሰጠው ይህ ነው፡፡
አብርሃምን የተናገረው ይስሐቅንም ከመታረድ ያዳነው ያዕቆብንም ወደ አገሩ ያስገባው ይህ ነው፤ ለሚፈሩት በረከትን የሚሰጥ ለማይታዘዙት ቅጣትን የሚያዘጋጅ ይህ ነው፡፡ እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተ ስለምትክዱት ሕጉንና ሥርዓቱንም ትለውጣላችሁና፤ ስለዚህ እነሆ፤ መስዋዕታችሁ ይሻራል፤ ምኵራቦቻችሁም በዋሕድ ወልደ እግዚአብሔር ስም አብያተ ክርስቲያናት ይሆናሉ›› ይህንንና የሚመስለውን ተናግራ ዝም አለች፡፡
እኛም የካህናት አለቆችን መልስን እንዲህ አልናቸው፤ ‹‹እነሆ ቅርጺቱ ሥዕል ተናግራ ወቀሰቻችሁ፤ ታምኑ ዘንድ ይገባችኋል፡፡›› የካህናት አለቆችና አይሁድም እንዲህ አሉን፤ ‹‹ይህ የሚናገረው በሥራይ ነው፤ አብርሃምን በወዴት አገኘው፤ ከሞተ ዘመኑ ብዙ ነውና፡፡››
ጌታችን ኢየሱስም ወደ ቅርጺቱ መለስ ብሎ እንዲህ አላት ‹‹አብርሃምን እንዳነጋገርኩት አላመኑምና ሒደሽ እንዲህ በይው፤ አስቀድሞ አዳምና የፈጠረው አንተንም ወዳጁ ያደረገህ አንተ ልጆችህ ይስሐቅና ያዕቆብን ይዘህ ተነሥ፡ ከመቃብርም ወጥተህ ወደዚህ ኑ የካህናት አለቆችን ትወቅሱአቸው ዘንድ እኔ የማውቃችሁና የተነጋገርኳችሁ መሆኔን አስረዷቸው፡፡›› ቅርጺቱም ሥዕል ይህን ሰምታ እያየናት ሔደች፡፡ ወደ አብርሃምም መቃብር ደርሳ በውጭ ቁማ ጠራቻቸው፡፡ ወዲያውኑ ከሦስቱ አርእስተ አበው ጋር ዐሥራ ሁለቱ ወጡ፡፡ ከእኛ ውስጥ ወደ ማን ነው የተላክሽ አሏት፡፡ ቅርጺቱም እንዲህ ብላ መለሰች ‹‹ወደ ሦስቱ የአባቶች አለቆች ነው፤ እናንተ ግን እስከ ትንሣኤ ሙታን ድረስ ተኙ፤ ያን ጊዜም ወደ መቃብራቸው ተመለሱ፡፡
እሊህ ሦስቱ አባቶችም የካህናቱ አለቆችና እኛ ወደ አለንበት ከቅርጺቱ ሥዕል ጋር መጥተው ወቀሷቸው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነም ነገሩአቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ጌታችን አባቶችን ወደቦታችሁ እንዲሔዱ አዘዛቸው፤ ወዲያው ተመለሱ፤ ቅርጺቱንም ወደቦታዋ እንድትመለስ አዘዛት፤ እርሷም ወደ ቀደመው አኗኗሯዋ ተመለሰች፤ ይህንንም አይተው የካህናት አለቆች አላመኑም፤ ሌላም ብዙ አለ፤ ብነግረህ መወሰን አትችልም፤ ነገር ግን ለብልህ ጥቂት ቃል ትበቃዋለች፤ ለሰነፍ ግን ቢነግሩት በቁም ነገር ላይ አይታመንም ብሎ ነገረው፡፡
ከዚህም በኋላ ጌታችን ማነጋገሩን ገታ፤ ራሱንም እንደሚያንቀላፋ አደረገ፤ እንድርያስም አንቀላፋ፤ እንድርያስንና ደቀ መዛሙርቱን እንዲሸከሙአቸውና ሊገቡበት ወደሚሹት አገር በውጭ እንዲአኖሩዋቸው መላእክትን አዘዛቸው፡፡
ከዚህም በኋላ እንድርያስ በነቃ ጊዜ ዐይኖቹን ገለጠ፤ የከተማውንም በር ተመለከተ፤ በየብስም ላይ እንዳለ አውቆ ደነገጠ፤ አደነቀም፡፡ ደቀ መዛሙሩቱንም አነቃቸውና እንዲህ አላቸው፤ ‹‹ጌታችንን በባሕር ላይ ሳለን ያላወቅነው ምን አደረገብን፤ ሲፈትነን መልኩን ለውጦ እንደሰው ሆኖ ታይቷልና፡፡››
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሊቀ ሐመር አምሳል በመገለጥ ከሚፈልጉት ዳርቻ ቢያደርሳቸውም ማንነቱን በጊዜው አላወቁትም ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ እንድርያስ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ ‹‹ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከእኛ ከባሮችህ ሩቅ እንዳልሆንክ አወቅሁ፡፡ ነገር ግን በመርከብ ላይ እኔን እንደማተምረው ሰው መስለኸኝ በድፍረት ተናግሬሃለሁና ጌታዬ ይቅር በለኝ!›› በዚያን ጊዜ የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእንድርያስ ዳግመኛ ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፤‹‹አዎን እኔ ነኝ፤ በሊቀ ሐመር አምሳል በባሕር ውስጥ የተገለጥኩልህና መርከቡን የቀዘፍኩልህ፡፡ አትፍራ፤አትደንግጥ! እኔ ከአንተ ጋራ እኖራለሁ፡፡›› ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያት በክብር ዐረገ፡፡ እንድርያስም መንገዱን ሔደ፡፡
በእኛ የሕይወት መንገድ ላይ ግን መሰናክል ሆኖ ጠላት ዲያብሎስ ከፊታችን ከተጋረጠብን ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ዓለምን በኃጢአት ማዕበል ውስጥ ዘፍቆ ብዙዎችንም እያስጨነቀም ነው፡፡ እናም ከያዘን አረንቋ አውጥቶና ማዕበሉን ቀዝፎ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ያደርሰን ዘንድ ሊቀ ሐመራችንን አጥብቀን እንፈልገው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቸር ጠባቂያችን መሪያችንም ነውና በሕይወት መንገድ ይመራን ዘንድ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንኑር፡፡ ዘመነ ማቴዎስን ከእርሱ ጋር እንጓዝ!
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ