ለአንዲት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሲኖዶስ
ለአንዲት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሲኖዶስ!
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማኅበራት ኅብረት በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ስለሚካሄደው እርቀ ሰላምና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ የሊቃነ ጳጳሳት፤ የጳጳሳት እና የኤጲስ ቆጶሳት አንድነት ጉባኤ ነው፡፡ የዚህ መሠረቱ ደግሞ ጌታ በቅዱስ ወንጌል፣‹‹ከእናንተ ሁለቱ በምድር ላይ ስለሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢተባበሩ በሰማያት ባለው አባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰባሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና፤›› (ማቴ 18፡19) የሚለው አምላካዊ ቃል ነው፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ መሠረታዊ ዓላማውም፡
- የቤተ ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና መጠበቅና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ማጽናት
- ምእመናንን በመጠበቅ የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑ ማብቃት (ዮሐ 21፥19)
- ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዲያብሎስን ውጊያ ተቋቁማ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት አገልግሎቷን እንድትፈጽም በፍቅር፣ በአንድነትና በትሕትና በመቆም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት መጠበቅ ነው፡፡
ይሁንና ላለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት በስንዴው መካከል እንክርዳድ የሚዘራው ጠላት ዲያቢሎስ የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር አንድነትን በማፋለስ በአበው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ልዩነት በመፍጠር የዶግማና ቀኖና ልዩነት ሳይኖር ሲኖዶሱን እስከ መክፈል የደረሰ አሳዛኝ ተግባር መፈጸሙ መላውን ማኅበረ ምእመናን ሲያሳዝን የኖረ ተግባር ከመሆኑም በላይ በቀደመ ታሪኳ ታላቅ በሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ጥቁር ነጥብ የጣለ ድርጊት ሆኖ በትውልድ የሚታወስ ነው፡፡
ይህ ተግባር የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በሚፈለገው ደረጃ እንዳይካሄድ፣ ቅሬታዎች እንዲነሡ፣ ምእመናን እርስ በርስ እንዳይተማመኑና አንድነታቸው እንዳይቀጥል አድርጎአል፡፡በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያኒቱ የዕውቀት ምንጭ የሆኑት የአብነት መምህራን እና ተማሪዎች መሰደድ፤ ምእመናን ወደ መናፍቃን ጎራ መቀላቀል፤ሕገ ወጥነት እና ግለሰባዊነት እንዲስፋፋና የቡድን አመራርና ጣልቃ ገብነት እንዲሰፍን አድርጓል፡፡ይባስ ብሎም በአስመሳይ አገልጋዮች የተሐድሶ ኑፋቄ መሰራጨትን አስከትሏል፡፡
በመሆኑም እኛ በቊጥር ከ100 (ከመቶ)በላይ የሆኑ ማኅበራትን የያዝን የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን የመንፈሳዊ ማኅበራት ኅብረት ሥራ አስፈጻሚዎች በቤተ ክርስቲያን በተለያየ መዋቅር ውስጥ እውቅና ተሰጥቶን የምናገለግልና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በተለያየ ሙያ የተሠማሩ አባላትን የያዝን ሲሆን በቤተ ክርስቲያን እርቀ ሰላምና በተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡
1.በአንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊት እና ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ባሉ አባቶቻችን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል የነበረው የልዩነት ግድግዳ ፈርሶ፣ይቅርታን የሚያስተምሩን አባቶቻችን ራሳቸው ይቅር ተባብለው መልካም አርዓያነታቸውን ለእኛ ለልጆቻቸው እንዲያሳዩን እንፈልጋለን፡፡ሰላምንና ይቅር መባባልን የሚሰብኩን አባቶቻችን እንዲሁም ደግሞ ራሳቸው በተግባር ኑረውት እንዲያሳዩን እኛ የመንፈስ ልጆቻቸው አጥብቀን እንሻለን፡፡ በአባቶቻችን እርቀ ሰላም ቀደም ሲል በተፈጠረው መለያየት ግራ የተጋቡትና የተበታተኑ ምእመናንን በፍቅር ለመሰብሰብ እንዲችሉ ትልቅ ተስፋ እንዳለው እናምናለን፡፡
2.በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ አባቶች ይህንን የእርቀ ሰላም ጥሪ ተቀብለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመጀመራቸው ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ይዘው የተነሡ የእርቀ ሰላም ኮሚቴ አባላትን እናደንቃለን፡፡ እኛም በቤተ ክርስቲያን በተለያየ መዋቅር አገልግሎት የምንሰጥ ማኅበራት አባላት በግልም እንደ ማኅበርም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን የተጀመረው የእርቀ ሰላም እንቅስቃሴ ከግብ እንዲደርስ በማንኛውም አገልግሎት ለመደገፍና ለእርቀ ሰላሙ ከሚጥሩ አካላት ጎን ለመቆም ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን፡፡
3. ይህንን የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ለመመለስ እና የሀገራችንን ሕዝቦች በሰላም መኖር ለማረጋገጥ የሚደረጉ ማንኛቸውንም ጥረቶች ሁሉ እንደግፋለን፤መንግሥት ይልቁንም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ረገድ እያሳዩ ያለውንም ፍላጎት እናደንቃለን፡፡
4. በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ለ፳ዓመታት ያህል ተለያይቶ የቆየውን የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች አንድ ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጉልህ እንቅስቃሴና ሐምሌ 1ቀን 2010 ዓ.ም በአሥመራ ከተማ ላይ ኤርትራዊያን ወገኖቻችን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን በደማቅ ሁኔታ በመቀበል ለኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ፍቅር የገለጹበት መንገድ እጅግ ልብ የሚነካ በመሆኑ በታላቅ ትሕትና ያለንን አክብሮት እንገልጻለን፡፡መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን በሁለቱም ሀገር ያሉ አባቶቻችን ሊቃነ ጳጳሳትም በሁለቱ ሀገር ሕዝቦች መካከል የተጀመረው ግንኙነት እና በሁለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በጋራ በምናካሄድበት ሁኔታ ላይ ጉልህ ድርሻ እንዲኖራቸው ጥሪያችንን እናስተላልፋን፡፡
5.የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሊቢያ ሰማዕትነት የተቀበሉ ኢትዮጵያዊያን እንደ ግብፅ ሰማዕታት ተገቢውን ትኩረት አግኝተው አጽማቸው በሀገራቸው በክብር የሚያርፍበትና እንደ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ተገቢው መታሰቢያ የሚደረግበት ሁኔታ እንዲኖር አበክረን ጥሪ እያስተላለፍን በዚህ ረገድ የማኅበራት ኅብረታችን የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል፡፡
6. የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን አቋምና አስተምህሮ በማይመጥን መልኩ የሚካሄዱትን አድሏዊ አሠራሮች፣ የሙስናና ብልሹ አሠራርን ለማስወገድ ቋሚ ሲኖዶስና ቅዱስ አባታችን የጀመሩትን በተለይም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ የተደረገውን ጅምር አስተዳደራዊ ለውጥ እንዲሁም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የተናገሩትን ተስፋ ሰጪ ቃላት እንደግፋለን፡፡ በቀጣይም ከችግሮች ውስብስብነት አንጻር በአስተዳደር በኩል ያለውን ክፍተት አባቶቻችን በቅዱስ ሲኖዶስ መክረውበት የማያዳግም ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚያመጡ የምናምን ሲሆን እኛ የኅብረቱ አባላት በሙያም ይሁን በሌላ አስፈላጊ በሆነ መልኩ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን፡፡
7. በአጠቃላይ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንም ይህ የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ጥረት በምንም ምክንያት ወደኋላ እንዳይመለስ በጸሎትም በሐሳብም የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
8.በዚሁ አጋጣሚ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም የተቋቋሙ የተለያዩ የአገልግሎት ማኅበራት ሁሉ የጋራ መናበብ እና እቅድ ኖሯቸው ተጨባጭ ለውጥ በሚያመጡበት ስልት ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያናችን እድገት በጋራ እንዲያገለግሉ ጥሪአችንን እናስተላልፋለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን የመንፈሳዊ አገልግሎት ማኅበራት ኅብረት
ሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ