ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ ብቁ ዜጋ ለማፍራት በልዩ ትኩረትና በንቃት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ!
ሀብቴ ብርሃኑ
ታኅሣሥ ፲፯፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
የማኅበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማእከል ለትውልድ ማእከል ግንባታ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ በታኅሣሥ ወር ፳፻፲፯ ዓ.ም. ባካሄደው ልዩ መርሐ ግብር ላይ በመሪጌታ ባሕረ ጥበብ ሙጬ “የሉላዊነት ተጽዕኖ በኦርቶዶክስ ላይ” በሚል ርእስ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ ብቁ ዜጋ ለማፍራት በልዩ ትኩረትና በንቃት መሥራት እንደሚገባ የሚያመለክት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የየካ አባዶ የደብረ ልዕልት ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት የመሪጌታ ባሕረ ጥበብ የዳሰሳ ጽሑፍ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ለዚህ ተልእኮ መፈጸም አስቀድሞ ችግሩን በመረዳት መፍትሔውን ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
በውይይቱም “የዳሰሳ ጽሑፉ መሠረታዊ ዓላማ ግሎባላይዜሽን በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ላይ እያደረሰ የሚገኘውን ጫና በመከላከል ረገድ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ነው” በማለት መሪጌታው አስረድተዋል።
መሪጌታ ባሕረ ጥበብ አያይዘውም ማኅበረ ቅዱሳን በደርግ ዘመን የኮሚኒዝም አስተሳሰብ የነበረውን ሃይማኖት አልባ ትውልድ የመፍጠር ዓላማ ለማክሸፍ የአንበሳውን ድርሻ እንደተወጣ አስታውሰው “በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ማእከላትን መገንባትና ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ማስፋፋት አለበት” ብለዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት በችግሮች ዙሪያ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
የቤተ ክርስቲያን አገልጋይነት ሚናቸውን ለመወጣት ወጣቶችን የማስተማርና የማሠልጠን ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ የገለጹት መሪጌታ ባሕረ ጥበብ ወጣቶች ዓይኖቻቸውን በእግዚአብሔር ጥበብ እና በአባቶቻቸው ሕይወት ላይ በመመሥረት ዓለምን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ መነጽር በመምራት ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።