ለሲኖዶሳዊ ልዕልና መከበር የምእመናን ድርሻ ከፍተኛ ነው!

ክፍል ሦስት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

መስከረም ፲፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

 ፬.፩. የቅዱስ ሲኖዶስ መሪነት አለመከበርና ውጤቱ፡-

ሲኖዶስ መሪ ነው፡፡ ሲኖዶስ የሕግ ሁሉ መገኛና የበላይ ባለ ሥልጣን ነው፡፡ ሲኖዶስ ሲኖዶስ ሆኖ ካልቀጠለ መሪነቱን ከተነጠቀ ውጤቱ ከባድ ነው፡፡

አጥር የሌለው ውብ የአትክልት ቦታ ነገር ግን ሁሉም የሚረማመድበት ይሆናል፡፡ ከጊዜ በኋላ ውበቱም ድምቀቱም ይጠፋል፤ ተወዳጅና ማራኪ ሆኖ መቀጠል አይችልም፡፡ ማንም የጎበዝ አለቃ እየተነሣ ቤተ ክርስቲያን እመራታለሁ፤ አዝባታለሁ፤ እኔ ብቻ ነኝ ትክክልና ተወካይ ነኝ የሚሉ እንዲበዙባት ያደርጋል፡፡ መሪና ተመሪ እንዳይኖር፣ የሥልጣን ተዋረድ እንዳይጠበቅ፣ ራሳቸውን የቤተ ክርስቲያን ተጠሪና ተወካይ የሚያደርጉ እንደዘመናችን ፖለቲካ ተወካይና ተቆርቋሪ ነኝ ባይ ይበዛባታል፡፡ ይህ ደግሞ መዋቅራዊና ማእከላዊነቷን አደጋ ላይ ይጥለዋል፡፡ ምእመኑን የሚካፋፍሉትና ሐሳቡንም ገንዘቡንም፣ ጉልበቱንም የሚበዘብዙ፣ አልፎ ተርፎ እምነቱንም የሚያደበዝዙ አካላት እንዲበራከቱ ያደርጋል፡፡ አንድነቷ እንዲሸረሸርና ለውጭ ጣልቃ ገብነት ተጋላጭነቷን ያሰፋዋል፡፡

ይህ ደግሞ መንግሥት ከሲኖዶሱ ይልቅ ግለሰቦችና ቡድኖችን ይዞ እንዲጓዝና የቤተ ክርስቲያን ውክልና ለእነርሱ በመስጠት ፕሮፖጋንዳ ሊሠራበትና ሲኖዶሱን ሙሉ በሙሉ እንዲሸፍኑት የሚያደርግ የሴራ ሥራ ለመሥራት ዕድል ይሰጠዋል፡፡ አሁንም እየተደረገ ያለው ይህ ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ የመሪነቱን ሚና ካላስከበረ

  • ግለሰቦችና ቡድኖችን ያገዝፋል፤
  • ምእመኑ ከአባቶቹ ይልቅ እነርሱን የመስማትና የመከተል ነገር ይከሰታል፤
  • እነዚህ አካላት በመንግሥትና በሌሎች አካላት ተጠልፈው ቤተ ክርስቲያንን አደጋ ላይ እንድትወድቅ እድል ይፈጥራል፤
  • ተከታዮቻቸውን ምእመናንን ለራሳቸው ክብር፤ ዝናና ጥቅም ሲሉ ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጭ ይመራሉ፤
  • መዋቅራዊ አንድነትና የሥልጣን ተዋረድ እንዳይኖር ያደርጋል፤
  • የሕግ አውጭ፤ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚውን አካል እንዲደባለቅ ያደርጋል፤
  • የውጭ አካለት ጣልቃ ገብነትን ይጨምራል፤
  • ቤተ ክርስቲያን ከምመናን፤ ምእመናንን ከሲኖዶስ የሚለይ አደጋ ይሆናል፤
  • ከፍተኛ የሥርዓት አልበኝነት ያስከትላል በጥቅሉ የቤተ ክርስቲያንን ዕድል ፈንታ በግለሰቦችና ቡድኖች እጅ ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል፡፡ ከሐዋርያት ተሳስሮ የመጣው ክህነትና ትምህርትም ቀጣይነቱ ስጋት ውስጥ ይገባል፡፡

፬.፪. የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ባለመከበሩ የሚጎዳው ማን ነው፡-

የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ካልተከበረ ውሳኔዎቹ ካልተፈጸሙ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ያመጣል፡፡ ጉዳቱ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ብቻ ሆኖ አይቀርም፡፡

፬.፪.፩. ቤተ ክርስቲያናችን ትጎዳለች

ሲኖዶሱ የቤተ ክርስቲያን ሁሉ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የሕጓ ምንጭ፣ የክህነት እንዲሁም የቀኖና/ሥርዓት/ መገኛ ነው፡፡ እነዚህን ብቻ እንኳ ወስደን ብናይ ሲኖዶስ ከሌለ ሕግ የለም፤ ሕግ ከሌለ ደግሞ መሪና ተመሪ አገልግሎትና አገልጋይ፣ ሁሉም የለም፡፡ ምክንያቱም ያለ ሕግ ሕይወት የሚኖረው ተቋም አይኖርም፡፡ ቀኖናውንም ብንወስድ ሕጉ/ዶግማው/ሊቀጥል፣ ሊፈጸም የሚችለው ሕይወት ኖሮት ሊዳሰስ ሊጨበጥ የሚችለው በቀኖናው አማካኝነት ነው፡፡ ሥርዓት አልበኝነትን አጥብቆ ከጅምሩ መዋጋት፣ የሥልጣን ተዋረድን ማስጠበቅ፣ ሲኖዶሳዊ ልዕልናን ከፍ ማድርግ ይገባል፡፡ ‹‹ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጿቸው›› (፲፮/፩ተሰ. ፭፥፲፬) እንዳለ ሐዋርያው ማለት ነው፡፡

አሁን ላይ ያለ ሥርዓት የሚሄዱ በቤተ ክርስቲያን ስም መዋቅር እያፈረሱ የሲኖዶሱን መሪነት የማይቀበሉ፣ በማኅበር ስም፣ በአጥማቂ ስም፣ በባለ ራእይ ስም፣ በብሕትውና ስም፣ ሲኖዶሳዊ ልዕልናን እያጣጣሉ አባቶችን እየዘለፉ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ሁሉ ሥርዓት ማስያዝ ይገባል፡፡ ክብረ ክህነት እንዳይጠበቅ፣ የቤተ ክርስቲያን የሥልጣን ተዋረድ እንዳይከበር፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባትና ዝርው የሆነች መሪና ተመሪ የማይገናኙባት ትሆንና ቤተ ክርስቲያን ተጎዳለች፡፡

፬.፪.፪.ተጎጅ የምትሆነው ሀገር ናት፡፡

ሀገር ሁሉ ነገር ናት፤ ሰው ለሀገር ነው፤ ሀገርም ለሰው ነው፤ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ሰዎች ነን፤ ከሰውም በላይ ክርስቲያኖች ነን፡፡ ክርስትናችን ከሰውነታችን ሰውነታችን ከሀገራችን ነጣጥለን አይተን አናውቅም፡፡ አባቶቻችን ክህነትንም ንግሥናንም ገንዘብ አድርገው ኩሩና ባለብዙ ጸጋ የታፈረችና የተከበረች፣ ለጠላቶቿ እንቆቅልሽ ለወዳጆቿ ቅኔ የሆነች አገር አስረክበውናል፡፡ ስለዚህ የዚች ሀገር ክብር፣ ውበት፣ ጥበብ፣ ሀብት  የቤተ ክርስተያን ገጸ በረከት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ፈጣሪውን የሚፈራ ሰውን የሚያከብር ትሑትና ኩሩ ማኅበረሰብ ጭምር አስረክባለች፡፡

ፊደል ቀርጻ ቀለም በጥብጣ ብራና ዳምጣ ወገን ሳትለይ ትውልድ ስትቀርጽ ሀገር ስትገነባ የኖረችው፣ ሀገርን ከቤተ ክርስቲያን ነጥላ ስለማታይ ነው፡፡ ለዚህም ሊቃውንቱ ካህናቱ፣ ጳጳሳቱ፣ መነኮሳቱ ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ በምግባር የታነጸ ባልደከመበት መበልጸግ የማይሻ አገሩን የሚወድ፣ ታላቆቹን የሚያከብር፣ ለሰዎች የሚራራ ትውልድ በመገንባት፣ ለሞራልና ለሕግ ተገዥ የሆነ በመቻቻልና በአብሮነት የሚያምን ትውልድ ያስረከከበች ናት፡

ከጊዜ ወዲህ ግን በዘመናዊነት ስም ቤተ ክርስቲያን ተገፋች፤ ትውልዱ ቤተ ክርስቲያንንና አባቶቹን እንዳያውቃቸው፣ በትምህርታቸው በሕጋቸው እንዳይኖር ተሰበከለት/ተተረከለት/፤ ሃይማኖተኝነት እንዳለመሰልጠን እንደኋላ ቀርነት ተቆጠረ፡፡ በሁሉ የበለጸገችውን ቤተ ክርስቲያን  በሀብቷ እየኖሩ በቅርሶቿ እየከበሩ የድህነት ምክንያት ናት ብለው ትውልዱን አሳሳቱት፡፡ አባቶቹን እንዲንቅ እንዲያቃልል ቃላቸውን እንዳይሰማ እራሱን እንደ አዋቂ እንዲቆጥር ከሥሩ የተነቀለ ተክል፣ ውኃ የሌለው ጉድጉድ፣ በድንቁርናው የማያፍር ንቅል ብኩን ትውልድ ፈጠሩ፤ ስለዚህ ሀገር ተጎጅ ናት፡፡

፬.፪.፫.ዓለም ትጎዳለች

የአንድ ነገር ውበቱ የሚመነጨው ከተቃርኖው/ከልዩነት/የተነሣ ነው፡፡

ዓለም አሁን ወደ አንድ ቅርጫት ገብቶ ተከማችቷል፡፡ ሁሉም አንድ ዓይነት ከሆነ ማነጻጸሪያ የልዩነት ማሳያ ስለማይኖረው አያምርም፡፡ ማንም ተመሳሳይ ነገርን ሊያደንቅ ብርቅ ድንቅ ሊል አይችልም፡፡ ብርሃን መደነቁ በጨለማ መኖር ነው፡፡ ቀን መወደዱ ሌሊት ማነጻጸሪያ ሆኖት ነው፡፡  ቤተ ጣዖት እንዴት አስቀያሚ መሆኑን ስናስብ ለቤተ እግዚአብሔር ያለን ፍቅር እጥፍ ድርብ ይሆንልናል፡፡

ዓለም በግለሰብ የበላይነት ሰብሳቢነት ትመራለች ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ሰብሳቢነት ትመራለች፡፡

ዓለምን ሥጋውያን ይመሯታል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳውያን ይመሯታል፡፡

ዓለም የሞት ማእከል ናት ቤተ ክርስቲያን የሕይወት ምንጭ ናት፡፡ ዓለም በመንኮራኩር ስለመምጠቅ ይደነቃል ቤተ ክርስተያን በነፋስ ትክሻ በእሳት ሰረገላ ስለመምጠቅ ታስተምራለች፡፡

ዓለም መቶ ዓመት ስለመኖር ይሠራል፤ ቤተ ክርስቲያን ሕያው ሆኖ ዘለዓአለም ስለመኖር ታስተምራለች፡፡ ዓለም ሞትን ትደግሳለች፤ ቤተ ክርስቲያን ሕይወትን ትመግባለች፤ ዓለም ወደ ጨለማው ስትጎትት ቤተ ክርስቲያን ወደ ብርሃን ትስባለች፤ ቤተ ክርስቲያን ስንል ደግሞ ባላደራው የመንጋው ጠባቂ ለግድግዳዋ መሠረት ለጣራዋ ጉልላት ሆኖ የሚሠራላትን  ሲኖዶስ ከቤተ ክርስቲያን አይለየውም፡፡ ስለዚህ ሲኖዶሳዊ ልዕልና ከሌለ ዓለም ጌጧን አጣች ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስተያን ለዓለም ያበረከተችውን መዘርዘር መድከም ነው፡፡

፬.፬. ማጠቃለያ

የዚህ ጽሑፍ ትኩረቱ ሲኖዶሳዊ ልዕልና እንዲከበር ምእመናን ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ማጉላት ነው፡፡ አሁን ላይ በቤተ ክርስቲያን በየደረጃው የምእመናንን የአገልግሎት ተሳትፎና ባለ ድርሻ አካልነት የዘነጋና ምእመናንን ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ብቻ የመፈለግ ዝንባሌም ይታያል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ክብሩ፣ ልዕልናው፣ መታፈሩና መከበሩ እየቀነሰ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች እየተተበተበች መምጣቷ ክብረ ክህነት እየደበዘዘ፣ ዘላኖች የበዙባት ቤት ጥርስ አልባ አንበሳ እየሆነች መሆኑን ማመን ይገባል፡፡ ችግሩ ይቀረፍ ዘንድ፣ ሲኖዶሳዊ ልዕልና ይመጣ ዘንድ፣ መልካም አስተዳደር በቤተ ክርስቲያን የሠፍን ዘንድ ምእመናን የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸውና ድርሻ እንዲኖራቸው መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ምእመናኑ መንፈሳዊ እውቀታቸው እያደገ መጥቷል፡፡  በተለይ ወጣቱ ትውልድ አንጻራዊ መንፈሳዊ እውቀት በንባብም በትምህርትም በልዩ ልዩ መንገድ ያገኘበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ማለት ሥርዓት ሲጣስ ዶግማ ሲፋለስ፣ መንግሥትና ሌሎች አካላት ቤተ ክርስቲያን ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ሲኖዶሱ መልስ ባለመስጠቱ ከፊት ለፊት ግንባር ቀደም ሆኖ ባለመገኘቱ፣ ምእመናን ያዝናሉ የበለጠ እንዲርቁ ምክንያት ይሆናል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ምእመናን ከሲኖዱሱና ከአባላቱ ብዙ ይጠብቃሉ፡፡

ለምሳሌ ጥርሱ እንደወለቀው፣ ጺሙ እንደተነጨው ፊቱ እንደተጸፋው እንደ ዲዮስቆሮስ፣ በፓትርያሪክነት ዘመኑ አምስት ጊዜ እንደተጋዘው አትናቴዎስ፣ ንግሥቲቱን በመዝለፉ፣ ሥርዓት አልበኛ ካህናትና ጳጳሳትን ከሹመታቸው በመሻሩ በስደተና በመከራ ሕይወቱ እንዳለፈው እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ (የሃይማኖታ አበው መቅድም/ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ) እንዲሆኑለት፣ ሐሰትን ሐሰት እውነትን እውነት እንዲሉ አመጸኞችና ግፈኞችን እንዲቃወሙላቸው፤ ይጠብቃሉ፤ ያነጻጽራሉ፤ በእነርሱ ሚዛን ይመዝኗቸዋል፡፡

ስለሆነም አባቶቻችን ሊቃነ ጳጳሳት እራሳቸውን የሚያከብሩ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያከብሩና የሚያስከብሩ እንዲሆኑ፣ ለወዳጅ ኩራትን ለጠላት ፍርሃትን የሚሠጥ ሁሉ የሚገዛለትና የሚታዘዘው፣ ግርማ ያለው ሲኖዶስ እንዲሆን የምእመናንን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ማመን እና አሠራር መዘርጋት ይገባል፡፡

 ተፈጸመ