ለማእከላት ጸሐፊዎችና ለማስተባበሪያ ሓላፊዎች ሥልጠና ተሰጠ
ሰኔ 13 ቀን 2005 ዓ.ም.
ታመነ ተ/ዮሐንስ
ሰኔ 1 እና 2 ቀን 2005 ዓ.ም በማኅበሩ ሥራ አመራርና አስፈጻሚ አካላት አወያይነት የማእከላት መደበኛ ጸሐፊዎች፣ መደበኛ መምህራንና የስድስቱ ማእከላት የማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሓላፊዎችን ያሳተፈ ሥልጠናና ውይይት ተካሔደ፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን የሀገር ውስጥ ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ዋና ሓላፊ የሆኑት ዲ/ን አንዱአምላክ ይበልጣል በስልጠናው መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ በሰጡት ማብራሪያ ተሳታፊዎቹ ለማኅበሩ አገልግሎት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው በመሆናቸው በማኅበሩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን ዙሪያ ማወያየት ለአገልግሎቱ መቃናት አጋዥ የሆነ ሥልጠና መስጠት ተገቢ ሆኖ እንደተገኘ ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት በሙያው ልምድ ባላቸውና የማኅበሩ የልማት ተቋማት አስተዳደር ቦርድ አባል በሆኑት በአቶ መንክር ግርማ “Communication & team development” በሚል ርዕስ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን አባላቱ በቀጣይ የአገልግሎት ቆይታቸው ችግሮችን በምን ዓይነት ሁኔታ መፍታት እንዳለባቸው ግንዛቤ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም ማኅበሩ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ ማእከላቱ እንዲረዱ በማድረግ በዋነኝነት ያለባቸው የሥራ ሓላፊነት የስብከተ ወንጌል ማስፋፋትና ማጎልበት ስለሆነ ሰፊውን ጊዜ በስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ ላይ ያሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ውይይትና የልምድ ልውውጥ ተካሒዷል፡፡
በስልጠናው ላይ ከስድስቱ ማስተባበሪያ ማእከላት ሠላሳ አምስት ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡