ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ ድጋፍ ተጠየቀ
ደረጀ ትዕዛዙ
በሲዳማ ጌዴኦ አማሮና ቡርጁ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት የሚገኘው የተፈሪ ኬላ ደብረ ስብሐት ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን በእርጅና ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ላይ በመሆኑ አዲስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማነፅ ለተጀመረው ጥረት የድጋፍ ጥሪ ቀረበ፡፡
ባለፈው የጌታችን መድኃታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በተከበረበት ዕለት በቤተ ክርስቲያኑ በተከናወኑ ጉባኤ ላይ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰብስቤ ካብት ይመር እንደገለፁት፤ ከአርባ ዓመት በላይ የሆነው ይህ ቤተ ክርስቲያን ያለ መሠረት የታነፀ ከመሆኑ በላይ በምስጥ እየተቦረቦረ ለመፍረስ እየተቃረበ ነው፡፡ በመሆኑም አዲስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማነፅ ባለፈው ዓመት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ተዋቅሮ ገንዘብ የማሰባሰቡ ሥራ እየተካኼደ መሆኑን የገለፁት ሰብሳቢው፤ እስካሁን ሰማንያ ሺሕ ብር ከምእመናን ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የአዲሱን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ዲዛይን ማኅበረ ቅዱሳን ሠርቶ ለኮሚቴው ያስረከበ መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢው፤ ሥራውን ለመጀመር በሚደረገው ጥረት በሀገር ውስጥና ውጪ ያሉ ምእመናን እንዲሁም በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ማኅበራት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ በባንክ መላክ የሚፈልጉም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲላ ቅርንጫፍ የባንክ ሒሳብ ቁጥር 15664 እንዲጠቀሙም ገልፀዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ተሾመ ወሰን በበኩላቸው፤ ሰበካ ጉባኤው፣ ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴውና የወረዳው ቤተ ክህነት ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት በብርቱ እንቅስቀሴ ላይ ናቸው፡፡ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት የአካባቢው ሕዝብ አቅም ባይኖረውም ተሠርቶ የማየት ከፍተኛ ጉጉት እንዳለው አስተዳዳሪው ጠቅሰው በእስካሁኑ ሂደት ጥሩ ትብብር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚሁ በዓለ ንግሥ ዕለት ምእመናኑ ሃያ ሰባት ሺሕ ብር ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡