‹‹ለሁሉም ጊዜ አለው›› (መክብብ ፫፥፩)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሚያዝያ ፳፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? የትንሣኤን በዓል ወቅት (በዓለ ኀምሳን) እንዴት እያሳለፋችሁ ነው? በሰንበት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እያስቀደሳችሁ እንደሆነ ተስፋችን እሙን ነው! የአካዳሚ (ዘመናዊ) ትምህርትስ ጠንክራችሁ እየተማራችሁ ነውን! የዓመቱ ትምህርት የሚያበቃበት ጊዜ እየደረሰ ነው! አንዳንዶች ፈተና የምትፈተኑበት ጊዜው በጣም ደርሷል፡፡ በርትታችሁ በመማር፣ በማጥናት ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ አለባችሁ፡፡
ልጆች! ያላችሁበት ወቅት ዓለማችን ከብዙ ሥልጣኔ ደረጃ የደረሰችበት ነው። ታዲያ እናንተም ከዚህ እኩል እንድትራመዱ በርትታችሁ በመማር ችግር ፈቺ፣ መፍትሔ አምጪ መሆን አለባችሁና በርቱ! ባለፈው ትምህርታችን ስለ ሰላም ተምረን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለ “ጊዜ” እንማራለን! መልካም!
ጊዜ ማለት የተለየ፣ የተወሰነ ሰዓት፣ ዕለት፣ ወርኀ፣ ዓመት፣ ዘመን፣ ዕድሜ፣ ሰው በምድር ላይ ኑሮ እስኪሞት ድረስ (ተሸሞ እስኪሻር) የሚኖርበት፣ የሚያርፍበት፣ የሚሠራበት ሌሊትና ቀን ሃያ አራት ሰዓት ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፫፻፯)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቅዱስ መጽሐፍ ስለ ጊዜ አጠቃቀም ሲናገር ለሁሉም ነገር ጊዜ እንዳለው ተጽፎልናል፤ ‹‹…ለሁሉ ዘመን አለው፤ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው…፡፡›› (መጽሐፈ መክብብ ፫፥፩) በጊዜ እንድንመራ ሥርዓትን የሠራልን ደግሞ እግዚአብሔር ነው፡፡
ውድ ልጆች! እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ የሚቻለው የሚሳነው ነገር የሌለው ነው፤ ነገር ግን ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ግን ጊዜ አለው፡፡ ፍጥረታትን ሲፈጥር በአንድ ጊዜ ማድረግ ሲቻለው በጊዜ ሂደት ነው፤ ለእኛ አብነት ሲሆነን ሁሉን በጊዜ ፈጠረ፤ በዕለተ እሑድ ጀምሮ በዕለተ ዓርብ ፍጥረትን ፈጥሮ አበቃ፡፡
ውድ ልጆች! እግዚአብሔር ፀሐይን፣ ጨረቃን፣ ከዋክብትን በዕለተ ረዕቡ ከመፍጠሩ በፊት በዕለተ ሰኑይ (ሰኞ) አስቀድሞ ሰማይን ( ጠፈርን) ፈጠረ፤ አያችሁ ሁሉን በሂደት በጊዜው ነው የፈጠረው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ መክብብ ‹‹ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው›› እንደተባለው ማለት ነው፡፡ (መጽሐፈ መክብብ ፫፥፲፩)
አያችሁ አይደል! ለምናከናውነው ( ለምንሠራው ) ሥራ ሁሉ ጊዜ አለው ማለት ነው፡፡ አንድን ነገር ያለጊዜው እናድርገው፣ እንፈጽመው ብንል ይበላሻል፤ የፈለግነውን ነገር ማግኘት አይቻለንም፤ ስለዚህ በሕይወታችን ለምንሠራቸው ነገሮች ሁሉ በራሳቸው ጊዜ ሲደርስ መፈጸም አለባቸው እንጂ ቸኩለን ብናደርጋቸው ለጉዳት ይዳርጉናል፡፡
ለምሳሌ ብንወስድ የዶሮ ጫጩት የምትፈለፈለው ከእንቁላል ነው፤ እንቁላሉ ምቹ ቦታ ይደረግና ሴቷ ዶሮ ታቅፋው ትቀመጣለች፤ ልክ ሃያ አንድ ቀን ሲሞላው ዕንቁላሉን ስትሰብረው ጫጩቶቹ ይወጣሉ፡፡ አያችሁ ልጆች! ከቀኑ ቀድማ እንቁላሉን ብትሰብረው ግን ጫጩት አይሆንም ይበላሻል፡፡ እኛም በልጅነታችን መሆን ያለብን፣ ማድረግ ያለብን፣ ማወቅ ያለብን ነገሮች አሉ፡፡ ዕድሜያችን ከሚፈቅደው ውጪ ያለ ጊዜያችን መከወን (መፈጸም) የሌለብንን ነገር እናድርግ ብንል ለጉዳት ይዳርገናል፤ መሆን ያለብንን ነገር ከመሆን ይቸግረናል፡፡ ስለዚህ ለሁሉ ጊዜ አለው፡፡ ለምሳሌ እኛ ያለንበት ጊዜ አብዛኛውን ልንፈጽመው፣ ልናደርገው ከሚገቡን ነገሮች ዋናው ነገር አንደኛ መማር፣ ሁለተኛ. መማር፣ ሦስተኛም መማር ነው፡፡ ምክንያም በእኛ ዕድሜ ጊዜው መማር ነው፡፡
ታሪክ
በእስራኤል አገር ሳኦል የተባለ ንጉሥ ነበር፡፡ አንድ ቀን ነቢዩ ሳሙኤል ወደ አንተ እመጣለው ብሎ ቀጠረው፤ ሳኦል ግን ነቢዩ ሳሙኤል የቆየበት መሰለውና ቸኩሎ ያለጊዜው ሳይፈቀድለት መሥዋዕት መሠዋት ጀመረ፡፡ በዚህን ጊዜ ነቢዩ ሳሙኤል መጣ ንጉሥ ሳኦልን ምንድን ነው ያደረከው ብሎ ጠየቀው፤ ንጉሡም ስትቆይብኝ መሥዋዕቱን ሠዋሁኝ ብሎ ተናገረ፡፡ በእርሱ መቸኮል ነቢዩ ሳሙኤልን የዘገየ መሰለው ፤ታዲያ በዚህ ጊዜ ነቢዩ ሳሙኤል አላበጀህም ( ልክ አላደረክም) በማለት ገሠፀው (ወቀሰው)፡፡
ንጉሥ ሳኦል በችኮላ ባቀረበው መሥዋዕት ተወቀሰበት ሥልጣኑንም ለማጣት ምክንያት ሆነው፡፡ (መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ፲፫፥፰) ልጆች! ምንም ነገር ቢሆን ቸኩለን ያለጊዜው እንዲሁም በማይመለከተን ነገር ገብተን ብንተገብረው (ብንሠራው) መጨረሻው ጥፋት፣ ውጤቱም ደግሞ ቅጣት ነው የሚያመጣብን፡፡ ሳንታዘዝ እንዲሁም በችኮላ (ያለጊዜው )፣ደግሞ እኛ ማድረግ (መሥራት) የሌለብንን ነገር መፈጸም ምንም ዋጋ አይኖረውም፤ ነገሮችን በትዕግሥት እና በጊዜው ማድረግ አለብን፡፡
ታሪክ
ቢታንያ በሚባል አገር ማርያም፣ ማርታ እና አልዓዛር የሚባሉ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ በቤታቸው እንግዶችን ያስተናግዱ ነበር፡፡ ጌታችን ቢታንያ በሚባለው አገር ሲመጣ በእነርሱ ቤት ገብቶ ያስተምራቸው ነበር፡። እነርሱም በቤታቸው ያስተናግዱት ነበር፡፡ ታዲያ በአንድ ወቅት አልዓዛር ታመመ፡፡ እኅቶቹ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመጣና ወንድማቸውን እንዲያድንላቸው መልእክት ላኩበት፤ ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛር መታመሙን ማንም ሳይነግረው ቢያውቅም የአልዓዛር እኅቶችም የላኩለትን መልእክት አውቋል፡፡ ግን ወደ ቢታንያ አልሄደም፤ አልዓዛር በጠና ታሞ ስለነበር ሞተ (ዐረፈ)፡፡ ከዚያም ተቀበረ፤ አልዓዛር ሞቶ ከተቀበረ ከአራት ቀን በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን አስከትሎ መጣ፤ ማርያም እና ማርታ ጌታችን መምጣቱን ሲሰሙ እያለቀሱ ‹‹ጌታ ሆይ አንተ እዚህ ሆነህ ቢሆን ኑሮ ወንድማችን ባልሞተም ነበር አሉት፤ ጌታችንም የሞተውን ወንድማቸውን አስነሣላቸው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን አልዓዛር በታመመ ጊዜ እያወቀ ለምን አልመጣም ቢባል ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ጊዜ አለው፡፡ ጌታችን አልዓዛር ታሞ ሳይመጣ ሞቶ ከተቀበረ አራት ቀን በኋላ መምጣቱ አልዓዛርን ከሞት አስነሥቶ አምላክ እንደሆነ ለመግለጽ ነው፡፡ ካለበትም ቦታ ሆኖ ማዳን ይቻለዋል እርሱ ግን ሁሉን በጊዜው ይሠራልና ዝም አለ፤ ታገሠ፤ ጊዜው ሲደርስ ግን የሞተውን አልዓዛር አስነሥቶ አምላክነቱ እንዲያምኑ አደረገ፡፡ (የዮሐንስ ወንጌል ፲፩፥፩-፶፫)
እንግዲህ ስለ ጊዜ በአጭሩ ተመለከትን፡፡ እኛ በቀን ውስጥ ያለውን ሃያ አራት ሰዓት፣ በሳምንት ውስጥ ያሉትን ሰባት ቀናት፣ በዓመት ውስጥ ያሉትን ዐሥራ ሁለት ወራት ወይም ደግሞ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀናት እንዴት እንጠቀምበት ይሆን?
ልጆች እንደመሆናችን አብዛኛው ጊዜያችንን በትምህርት ላይ ማሳለፍ ይኖርብናል፡፡ ትምህርት ቤት የምንማርበት፣ የቤት ሥራ የምንሠራበት፣ የተማርነውን ተጨማሪ መጻሕፍትን በማመሳከር የምናጠናበት ጊዜያትን በአግባቡ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡
ሌላው ዋናው የትምህርታችን መልእክት ማንኛውንም ነገር ዕድሜያችን በሚፈቅደው መጠን ማድረግ እንዳለብን ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ‹‹..ልጅ ሳለው እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅም አስብ ነበር፤ እንደ ልጅም እቆጠር ነበር …›› ተብሎ እንደተጻፈልን በልጅነታችን እንደ ልጅነታችን ብቻ ማሳብና መኖር፣ ነገሮችን ማድረግ አለብን፡፡ (፩ኛ ቆሮንቶስ ፲፫፥፲፩)
ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ! ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!