“ሆሣዕና በአርያም” (ማቴ.፳፩፥፱)
በቃሉ እሱባለው
ሚያዝያ ፪፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “እንደ ዕውሮች ወደ ቅጥሩ ተርመሰመስን፥ ዓይን እንደሌላቸው ተርመሰመስን፤ በቀትር ጊዜ በድግዝግዝታ እንዳለ ሰው ተሰናከልን፥ እንደ ሙታን በጨለማ ስፍራ ነን” እንዳለ በኃጢአት መረብ ተጠልፈን፣ ከእግዚአብሔር መንገድ ወጥተን፣ ለፈቃዳችን የተጣልን በሆንንበት ዘመን እግዚአብሔር በልባችን መደንደን፣ ወደ እርሱም የሚቀርብ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው በመጥፋቱ፣ ለድኅነት የሚማልድ በማጣቱም ተደነቀ። ጥፋታችንን የተመለከተው ደግ አባት ያድነን ዘንድ ይሻልና የገዛ ክንዱን መድኃኒት አድርጎ ላከልን። (ኢሳ. ፶፱፥፲፣ ፶፱፥፲፮)
የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ በደለው፣ በኃጢአትም ወደ ወደቀው የሰው ልጅ በተመለከቱ ጊዜ፣ የሰውም የመዳኑ ተስፋ እንዲፈጸም ጊዜው በደረሰ ዘመን እግዚአብሔር አንድያ ልጁን መድኃኒት አድርጎ ሰው ሆኖ እንዲወለድ ፈቃዱ ሆነ። ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች የመወለዱን ምሥጢር ሲያስተምር እንደሰማነው። “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፡፡” (ገላ.፬፥፬)
ባሕርየ ሰብእን ገንዘብ አድርጎ በእኛ ሥጋ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ ስሙ መድኃኒት ነው። ኃጢአተኞችን ከዘለዓለም ደዌ የሚፈውስ በሰማይ ያለ መድኃኒት፤ ይህንን ምሥጢር የሰማነው በምድር ካለ ሥጋዊ ሰባኪ አይደለም፤ ከንጹሓን መላእክት ወገን ከሆነ ከመጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤል እንጂ። የመወለዱን ብሥራት በዐወጀበት ሰዓት መድኃኒትነቱን ነገረን። “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” እንዲል፡፡ (ሉቃ ፪፥፲፩)
ከእኛ በላይ ስለ እኛ የሚስብ እግዚአብሔር ኃጢአታችን እንደ ጎርፍ ሞልቶ በፈሰሰ ዘመን ተገልጦ በምድር የጠፋችን ሥርዓት እየሠራ በመሰላል ደረጃ በደረጃ ከፍ ያለ ቦታን እንዲወጡ፣ ከሕገ ሥጋዊ ወጥተን በሰማይ ያለችን ሥርዓት እንድንተባበር፣ ከአባቱ ጋር በአንድነት ካለች ቅድስናም በቅድስናችን እንድንመስለው፣ ሕገ ሰብእን እየሠራ፣ እያስተማረን፣ እየተረጎመልን ወደ ላይ መውጣትንም እያለማመደን ሠላሳ ሦስት ዓመት በዚህች ምድር ኖረ።
በመቅደስ፣ በተራራ በባሕር ላይ እንዲሁም በባሕር ዳርቻ የምሥራቹን ካስተማረባቸው ቦታዎች ውስጥ ናቸው። ይህን የማዳኑን ትምህርት በይሁዳ፣ በኢየሩሳሌም፣ በቅፍርናሆም፣ በገሊላም አውራጃ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። በአንድ ወቅት (የአይሁድ ፋሲካ ከመድረሱ በፊት በስድስተኛው ቀን) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ አውራጃ ተነሥቶ ከሙታን ለይቶ ወደ አስነሣው ወደ አልዓዛር መንደር ወደ ቢታንያ አውራጃ ሊገባ ወደደ። (ማቴ.፳፩፣ ዮሐ.፲፪፣ ማር. ፲፩፣ ሉቃ ፲፱)
ከደቀ መዛሙርቱም ሁለቱን ልኮ ቤተ ፋጌ ከምትባል ቦታ አህያ እና ውርንጫ አስመጥቶ በእነርሱም ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ገባ። በዚያን ሰዓት ከይሁዳ አውራጃዎች ሁሉ የፋሲካን በዓል ለማክበር የተሰበሰቡት ሁሉ የኢየሱስን ወደ ኢየሩሳሌም መምጣት ሰምተው በእልልታ እና በዝማሬ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።” (ማቴ.፳፩፥፱)
ሆሣዕና በዕብራይስጥ ቋንቋ ሆሺያና ማለት ሲሆን መድኃኒት፣ ጌታ ሆይ አሁን አድን፣አሁን ታደግ የሚል ትርጉም አለው። እንደ ልቤ ብሎ የጠራው ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ እንዲታደግ “አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና” እያለ ሲማጸን እንሰማዋለን።(መዝ.፻፲፰፥፳፭)
በቤተ መቅደስ አገልግሎት የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ፣ የእርሱንም የምሕረት ዐዋጅ የሚጠባበቁ ሁሉ አቤቱ አድነን፣ አቤቱ አሁን ታደገን እያሉ ይማጸኑ ነበር። ለዚያ ነው ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ሲገባ “አቤቱ የዳዊት ልጅ ሆይ ማረን፥ በሰማይ ያለህ መድኃኒት ሆይ አሁን ታደገን” እያሉ ልብሳቸውን እያነጠፉ፣ ዘንባባ እየጎዘጎዙ ሊቀበሉት ወጡ። በዚያ በድንኳኑ አገልግሎት ውስጥ የማዳኑን ተስፋ እየተጠባበቁ የነበሩ ሁሉ የመምጣቱን ዜና በሰሙ ሰዓት ሆሣዕና በአርያም ‘በሰማይ ያለ መድኃኒት’ እያሉ ሊቀበሉት ወጡ። ከሕፃናት እስከ አዕሩግ ድረስ፣ የቢታንያ ድንጋዮች ሳይቀሩ ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት እያሉ አመሰገኑ። (ማቴ.፳፩፥፩-፲፩)
በርካታ በሽተኞች ከደዌያቸው ብዛት ነፍስና ሥጋቸው እጅግ በደከመች ሰዓት ተገልጦ ዕረፍትን ሲሰጥ ያዩ፣ የሰሙ የእነርሱን ቀንም በተስፋ ይጠባበቁት ነበር። አንዳንዶቹ ከሥጋ ደዌ፣ ከነፍስ ሕማም ይፈወሱ ነበር። ሌሎቹ ደግሞ እንዲህ ለትምህርት በሄደበት ቦታ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የናፈቋትን የሰማይ ርስት ለመውረስ፣ የተጠሟትን የጽድቅ ሕይወት፣ የተራቡትን የሕይወት ቃል ለመስማት ያገኙትን መልካም ዕድል ተጠቅመው የመጎብኘት ዘመናቸውን በምስጋና ይጀምሩ ነበር። ያች ዕለት የጌታ የስቅለቱ ደብዳቤ የመጨረሻ ሐረግ ነበረች። አይሁድ ሊገድሉት ምክንያት ይሹ ነበርና ዛሬም “እባክህን ደቀ መዛሙርትህን ገሥፃቸው” እያሉ ይጮሑበት ጀመሩ። ጌታ ግን እንዲህ አላቸው፤ “እላችኋለሁ፥ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ።” (ሉቃ.፲፱፥፵)
በዚያ በኢየሩሳሌም ከተማ የሆነውን የአይሁድ ቅናት ትተን ወደ ጠቃሚ ሐሳቦች፣ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ከአላቸው ነፍሳት ጋር ሆሣዕና በአርያም እያልን አብረናቸው እንራመድ። ዘይፄዓን ዲበ ኪሩቤል ‘በኪሩቤል ላይ የሚጫን’ እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም በረቡዕ ውዳሴ ማርያም ላይ በኪሩቤል ጀርባ ላይ የሚጫን ጌታ በተናቀች አህያ ጀርባ ላይ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ሰማይ ዙፋኑ የሆነ ጌታ አህያ ዙፋኑ ሆነች። ለዚያም ክብር “እንኳን ለአንተ አንተን ለተሸከመች አህያ ክብር ይገባል” እያሉ ልብሳቸውን አውልቀው አነጠፉለት፤ የወይራ ዝንጣፊ ጎዘጎዙለት። ከታሰሩበት ሊፈቱ የናፈቁ ነፍሳት ጌታቸውን በእልልታ “አዳኛችን ሆይ በሰማይ ያለህ መድኃኒታችን ዛሬ አድነን” እያሉ አመሰገኑት። ጌታችንም የተናቁትን ሊያከብር፣ የጠፉትን ሊፈልግ፣ የተገፉትን ሊያቀርብ፣ የተናቁትን ከፍ ከፍ ሊያደርግ የመጣ አምላክ ነውና የተናቀችዋን “አህያ ከነ ውርንጫዋ ፈትታችሁ አምጡልኝ” ብሎ በእርሷ ተጭኖ ወደ መቅደስ ገባ።
ስለ ጌታ ትሕትና ተናግረን ለመጨረስ ብንሞክር የሚቻል አይደለም፤ እንኳንስ ስለ እርሱ ይቅርና ስለ ቅዱሳን ትሕትና ለመናገር የሚቻል አይደለም። ይደነቃል እንጂ። ጌታ በየዋሃን ልቡና ማደር ያስደስተዋል። ለዚያ ነው ከተናቁት፣ ከኃጢአተኞች፣ ወገን ዘመድ ከሌላቸው ጋር የምናየው። እነዚያ አህዮች መላ የሰው ልጆችን ሁሉ ይወክላሉ። እነዚያ አህዮች በምድረ በዳ የታሰሩ ነበሩ። ጌታቸው ሲፈልጋቸው ግን ፈትተው አመጡለት።
ክብራቸውን ጥለው ተዋርደው የነበሩት እስራኤል ዘሥጋ በእነዚያ አህያዎች ይመሰላሉ። ጌታቸው በመጣ ጊዜ ግን የአህዮች ባለቤት ከእስራት ፈትቶ ወደ ጋጣቸው ያስገባቸዋል። እስራኤል ዘነፍስ የሆንን እኛም ሁሉ በናቀን፣ ሁሉ ክብርን በነፈገን፣ በተገለልን ሰዓት “መድኃኒት ክርስቶስ ሆይ ዛሬ አቅናን፥ አዳኛችን ሆይ ክብራችን በፊትህ ከፍ ከፍ ይበል” ብንለው በተናቀ ቦታ ከወደቅንበት አንሥቶ በክብሩ አደባባይ ያቆመናል። ሰማያዊ እልልታና ዝማሬ ወዳለበት መንጦላዕት ያስገባናል።
የመሥዋዕታችንን ዘይት ይዘን “አቤቱ አንተ በልባችን ያለውን የጠፋ መብራት አብራ” እያልን በፊቱ ለምስጋና እና ለለቅሶ ብንቆም የምሕረቱን ጠል ያርከፈክፍልናል። እንደሚያጅቡት ሕዝቦች ሆነን ሳይሆን የተጨነቀች ነፍሳቸውን ያሳርፉ ዘንድ የሻቱትን ሆነን፣ “እንደ ምኩራብ አለቆች የምስጋናን አፍ አዘጋ” እያልን ሳይሆን “ለዳዊት ልጅ ምስጋና ይገባል፤ ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት” እያልን፣ በመካከላችን ያለውን የመቃቃር ልብስ እያወለቅን መድኃኒታችን ሆይ አሁን አድነን፤ አቤቱ፥ ኃጢአታችን ብዙ ነውና፥ በአንተም ላይ ኃጢአት ሠርተናልና ኃጢአታችን ይመሰክርብናል፤ ነገር ግን ስለ ስምህ ብለህ አድርግ። አንተ የእስራኤል ተስፋ ሆይ፥ በመከራም ጊዜ የምታድነው፥ በምድር እንደ እንግዳ፥ ወደ ማደሪያ ዘወር እንደሚል መንገደኛ ስለ ምን ትሆናለህ? እንዳንቀላፋ ሰው፥ ያድንም ዘንድ እንደማይችል ኃያል ስለ ምን ትሆናለህ? አንተ ግን፥ አቤቱ፥ በመካከላችን ነህ፤ እኛም በስምህ ተጠርተናል፤ አትተወን” እንበለው፤ መሐሪ ነውና ይምረናል። (ኤር.፲፬፥፯-፱)
ክርስቲያኖች ሆይ! ይህች የምስጋና እና የውዳሴ ቃል በአይሁድ ማኅበር ፊት ምን ያህል ቁጣን እንደቀሰቀሰች አስተውሉ! እነዚያ የምኵራብ አለቆች እጅጉን ቀናተኞች ነበሩ፤ ነገር ግን ቅናታቸው የጠቀማቸው አልነበረም። የቁጣቸውንም ኃይል በዚህ ዐውቀናል፤ “መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው” እያሉ ይጮሁ ነበርና። (ሉቃ.፲፱፥፴፱) እነዚያ የአይሁድ ማኅበርተኞች ግን “ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ” የሚለውን የመጽሐፍ ቃል አላስተዋሉም ነበር። (መዝ.፰፥፪) እነዚያ “ለመቅደሱ አገልግሎት እንቀናለን” የሚሉት የምኵራብ አለቆች ምን ያህል በሌሎች የመዳን መንገድ ላይ እንደቆሙ አያችሁን?
እስኪ የእኛን መንገድ ቆመን እናስተውል! በሌሎች ሰዎች የመዳን ሕይወት ላይ አደናቃፊ የሆንባቸው ሰዎች የሉምን? “ስለ መቅደሱ አገልግሎት እንቀናለን” ብለን በማይጠቅም ቅናት የተለበጠ አገልግሎት ያለን ሰዎች የለንምን? በእንዲህ ዓይነት ቅናት የምስጋናችን መሥዋዕት የሰማያትን በር የሚከፍት ይመስለናልን? አይደለም። በነቀፌታ ውጊያ ውስጥ ተጠምደን ለመዳን የተሰጠንን የሕይወት ዕድል ስለምን እናባክናለን? ወደ ውስጣችን፣ ወደ ራሳችን መቅደስም ውበት እንመልከት እንጅጂ በሌለን እና በማንኖርበት የሕይወት ፍልስፍና ለመድከም አንሞክር!
የምንቀናለት አገልግሎት እኛ ብቻ የምንሠራው ይመስለናልን? አይደለም። እግዚአብሔር እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን ከቤተ መቅደሱ እየጠራረገ ማስወጣት ያውቅበታል። በመጠንቀቅ ሕይወት መኖር፣ “ሆሣዕና” እያሉ እንዳመሰገኑት ለእግዚአብሔር በጎ ቅናትን እንደቀኑት በመቅደሱ አገልግሎት በመባረክ መኖር ይሻለናል። በዚያም ኑረን በሕይወት ቆመን እንድንኖር ያድለን።
የቁስላችን መድኃኒት ሆይ ከአይሁድ ኅብረት ያይደለች፣ በትሕትናህ ከተደነቁ የነፍሳቸውን አርነትም ከናፈቁት ወገን የመሆኛውን ጥበብ እና ምሥጢር ይዘን እንድንቀርብ የምታስችለን ትንሽ የትሕትና እና ራስን የመግዛት ጥበብ ጨምርልን። ከብልቃጡ ሲወጣ ለሰው ሁሉ መልካም መዓዛ ያለው ሽታ እንዲወጣ ሽቱ ከእኛ ሲወጣ የጌትነትህን ክብር በአሕዛብ እና በሕዝብ ዘንድ እንዲጣፍጥ የሚያደርግ የሕይወትን ቃል የሚናገር የተገራ አንደበት ስጠን፥ እኛ እንደነዚያ የአይሁድ ሽማግሌዎች እንዳንሆን ብዙ የሕይወት ቋጠሮ አለብን እና መድኃኒታችን ሆይ ዛሬ አቅና፥ ዛሬ አድነን፤ አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን!