ሆሣዕና በአርያም
በዲያቆን ሚክያስ አስረስ
መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ሰውን ከወደቀበት የበደል ጉድጓድ ያወጣው ዘንድ እግዚአብሔር ክንዱን ወደ ዓለም ላከ፡፡ ሰው ኾኖ የተገለጠው የእግዚአብሔር ክንድ በትሕትና ሁለተኛ አዳም ኾኖ በለበሰው ሥጋ በጉድጓድ ተጥሎ፤ በሥጋ፣ በነፍስ፣ በውስጥ፣ በአፍአ ቈስሎ የነበረ አዳምን ከሞተ ነፍስ አድኖታል፡፡ ከእርሱ አስቀድሞ ሰውን ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከባርነት ወደ ነጻነት የሚያመጣ ባለመኖሩ ዅሉን የፈጠረ፣ ዅሉን የሚያኖር እግዚአብሔር በለበሰው ሥጋ ሞቶ ለሰው ልጅ መድኃኒት ኾነ፡፡ በዚህም ‹‹መድኃኒተ ፈነወ እግዚአብሔር ለሕዝቡ፤ እግዚአብሔር ለሕዝቡ መድኃኒትን ላከ፤›› ተብሎ በነቢዩ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ (መዝ. ፻፲፥፱)፡፡
ክርስቶስ ባለ መድኃኒት ኾኖ በኃጢአት ለታመሙ ደቂቀ አዳም ዅሉ ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡ በምድራዊ ሥርዓት እንደምናየው መድኃኒትና ባለ መድኃኒት እንደሚለያዩት አይደለም፡፡ እርሱ በመምጣቱ (ሰው በመኾኑ) ሁለቱንም ፈጸመ እንጂ፡፡ መድኃኒት አድርጎ ሥጋውን ደሙን የሰጠ እርሱ ነው፡፡ በካህናት አድሮ ሰው በንስሐ ሲመለስ መድኃኒት ወደ ኾነው ወደ ራሱ የሚመራም እርሱ ነው፡፡ በእመቤታችን ማኅፀን የተጀመረው የክርስቶስ መድኃኒትነት እና ፍቅሩ ፍጻሜውን ያገኘው በሕማሙ እና በሞቱ ነው፡፡ መሐሪ ንጉሥ እርሱ መኾኑን ይገልጥ ዘንድም በፈቃዱ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡
ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ከመግባቱ አስቀድሞ ከኢየሩሳሌም ፲፮ ያህል ምዕራፍ በምትርቀው በቤተ ፋጌ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ነበር፡፡ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለቱን ማለትም ጴጥሮስን እና ዮሐንስን ‹‹በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሒዱ፤ ወደ እርሷ ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበትን ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ፤›› በማለት አዘዛቸው (ማር. ፲፩፥፪)፡፡ ሰው ወዳልገባባት የተዘጋች የምሥራቅ ደጅ ወደ ምትባል ወደ ድንግል መጥቶ ዘጠኝ ወር ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ እንደ ኖረ፤ ማኅየዊት ከምትኾን ሕማሙ በኋላም ሰው ባልተቀበረበት መቃብር እንደ ተቀበረ፤ አሁንም ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት ማንም ሰው ያልተቀመጠባቸውን፣ አህያንና ውርንጫን እንዲያመጡ ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ፡፡
የፍጥረት ዅሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ እስትንፋሷን የገበረችለትን አህያ አሁን ደግሞ በፈቃዱ ስለ ሰው ዅሉ ሊሞት ሲል ንጉሥነቱን ሊያስመሰክርባት ወደደ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ካለው ፲፮ ምዕራፍ ዐሥራ አራቱን በአህያ ላይ ሳይቀመጥ በእግሩ ተጓዘ፡፡ ከዚያም ሁለቱን ምዕራፍ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ከሔደ በኋላ የኢየሩሳሌምን መቅደስ ሦስት ጊዜ በውርጫዋ ላይ ኾኖ ዞረ፡፡ በዚህም ሕግ በተሰጣቸው አይሁድ እና ሕግ ባልተሰጣቸው አሕዛብ ላይ እኩል ቀንበርን መጫን እንዳይገባ አጠየቀ፡፡
ወደ ኢየሩሳሌም ሲሔድም እርሱን የሚከተሉት ሰዎች ‹ሆሣዕና በአርያም› እያሉ ያመሰግኑት ነበር፡፡ ይኸውም ‹በሰማይ በልዕልና ያለ፤ ከሰማይ የመጣ መድኃኒት› ማለት ነው፡፡ ብዙ ሰዎችም ልብሳቸውን እና ቅጠሎችን በመንገድ ላይ አነጠፉ፡፡ ‹‹ሆሣዕና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው›› እያሉም ጌታችንን አመሰገኑ (ማር. ፲፩፥፰-፲)፡፡ ዛሬም እኛ ክርስቲያኖች ‹‹ቡሩክ ስሙ ለእግዚብሔር ወቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ስሙ ምስጉን ነው፡፡ ‹እግዚአብሔር ነኝ› ብሎ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ እርሱ ክርስቶስም ምስጉን ነው፤›› በማለት የአብ እና የወልድ መለኮታዊ አንድነትን ገልጸን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡
በክርስቶስ ሕማም እና ሞት የእግዚአብሔር ፍቅሩ እና መሓሪነቱ ተገልጧል፡፡ ክርስቶስ የተቀበለው መከራም የእርሱን አምላክነት እና ንጉሥነት አልሸሸገውም፡፡ እንዳውም ዙፋኑን መስቀል በማድረግ ንጉሥነቱን በመድኃኒትነቱ ገልጿል እንጂ፡፡ በማእከለ ምድር ተሰቅሎ በመድኃኒትነቱ ንጉሥነቱን መግለጡንም ነቢዩ፡- ‹‹እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማእከለ ምድር፤ እግዚአብሔር ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድር መካከልም መድኃኒትን አደረገ፤›› በማለት የተናገረው ቃል ያመለክታል (መዝ. ፸፫፥፲፪)፡፡ በሌላ የመዝሙር ክፍልም፡- ‹‹አንሰ ተሰየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ በጽዮን በደብረ መቅደሱ፤ እኔ በተቀደሰው ተራራ ላይ ንጉሥ ኾኜ ተሾምኹ፤›› በማለት ነቢዩ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መንገሡን ተናግሯል (መዝ. ፪፥፮)፡፡ ይህንም ‹‹እነርሱ (አይሁድ) ‹ሰቀልነው፤ ገደልነው፤ በኋላ ፈርሶ፣ በስብሶ ይቀራል፤› ይሉኛል እንጂ እኔስ ደብረ መቅደስ በሚባል መስቀል ላይ ነግሻለሁ›› ብለው ኦርቶዶክሳውያን አበው ይተረጕሙታል፡፡
የጌታችን ሕማሙ እና ሞቱ ንግሥናው፣ ክብሩ የተገለጠበት ምሥጢር እንጂ ክብሩን የሚሸሽግ ውርደት አይደለም፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- ‹‹ይትባረክ እግዚአብሔር ዘሰመየ ሕማማተ ወልዱ ክብረ ወስብሐተ፤ የልጁን ሕማማት ክብርና ምስጋና አድርጎ የሰየመ እግዚአብሔር ይመስገን!›› ያለውም ስለዚህ ነው፡፡ የክርስቶስ ሕማሙ እኛን ያከበረበት በመኾኑ ክብርና ምስጋና እንደ ተባለ እናስተውል፡፡
ከጌታችን በስተቀኝ በኩል ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴም፡- ‹‹አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ?›› በማለት ንጉሥነቱን መስክሮለታል (ሉቃ. ፳፫፥፵፪)፡፡ ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም በምስጋና መግባቱ መድኃኒትነቱን እና ንጉሥነቱን ያሳያል ማለታችንም ስለዚህ ነው፡፡ ዳግመኛም ዅሉን የያዘ ጌታ በአህያ ላይ መቀመጡ ትሕትናውን ያስረዳል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ፡- ‹‹ዘይነብር ዲበ ኪሩቤል ዲበ ዕዋለ አድግ ነበረ›› በማለት ሰማያዊው አምላክ ልዑል እግዚአብሔር በትሕትና በአህያ ጀርባ እንደ ተቀመጠ ተናገረ፡፡
ጌታችን በመድኃኒትነቱ ድንቅ የኾኑ ተአምራትን ለሰዎች አሳየ (ገለጠ)፡፡ ‹‹እምሆሣዕናሁ አርአየ ተአምረ ወመንክረ›› እንዳለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በቅዳሴው፡፡ ይህም ክርስቶስ በአህያ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ አእምሮ፣ ጠባይዕ ያልቀናላቸው ሕፃናት ዕውቀት ተገልጾላቸው ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› እያሉ ማመስገናቸውን ያጠይቃል፡፡ መናገር የማይችሉ ድንጋዮች እርሱ በከሃሊነቱ ዕውቀት ሰጥቷቸው መናገር ችለው ጌታችንን አመስግነዋልና፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መኾኑን፤ ቀድሞ በአዳም በደል ምክንያት ለሰው ከመገዛት ውጪ የነበሩ ፍጥረታት የሰውን ሥጋ ለብሶ በተገለጠው በክርስቶስ አማካይነት ዳግመኛ ለሰው መገዛታቸውን ከዚህ ምሥጢር እንረዳለን፡፡
ዳግመኛም ጌታችን በመድኃኒትነቱ የሥላሴ ልጅነት ማግኘትን እና ተአምራት ማድረግን ገለጠ፡፡ ‹‹እምሆሣዕናሁ አርአየ ጸጋ ወኃይለ›› እንዲል (ቅዳ. ጎርጎ. ዘኑሲስ)፡፡ የእርሱ የማዳን ሥራ ከሰው ተወስዶ የነበረውን የጸጋ ልጅነት እንዲመለስ ከማድረጉ ባሻገር በልጅነት ላይ ተአምራትን ለማድረግ አስችሏል፡፡ ይኸውም እርሱ በረድኤት አድሮባቸው ድንቅ ተአምራትን ለሚያደርጉ ቅዱሳን መሠረት ነው፡፡ በተጨማሪም የበደሉትን ያከብራቸው ዘንድ፤ ኃጥአንን ከኃጢአታቸው ያነጻቸው ዘንድ፤ እንደዚሁም የሳቱትን ይመልሳቸው ዘንድ ለንስሐ የሚኾን ዕንባን ሰጠ፡፡ ‹‹እምሆሣዕናሁ ወሀበ ፈልፈለ አንብዕ ለኃጥአን›› እንዲል (ቅዳ. ጎርጎ. ዘኑሲስ)፡፡
በተመሳሳይ ምሥጢር ጌታችን በመድኃኒትነቱ ለዕውራን ብርሃንን ሰጥቷል፡፡ ይኸውም ለጊዜው በዐይነ ሥጋ የታወሩትን በመፈወስ ዐይናቸውን እንዳበራላቸው፤ ለፍጻሜው ግን ዕውቀትን ከማጣት የተነሣ ታውረው ለነበሩ ዅሉ ዕውቀትን፣ ጥበብን ማለትም አንድነቱን፣ ሦስትነቱን፣ አምላክነቱንና የዓለም መድኃኒት መኾኑን የሚረዱበትን ጥበብ እንደ ገለጠላቸው የሚያመለክት ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡